የግል መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ

የግል መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/16 ነሀሴ 2014

በመቅደስ ደምስ

መስከረም 30 ቀን 1972 ዓ.ም ከሳህል ተራራ ስርጭት የጀመረው ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬዲዪ ለፋና ሬዲዮ መሰረት ሆነ፡፡ በአመቱ የትግራይ አብዮት ድምጽ ተብሎ ከትግርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አማርኛ ስርጭት ጀመረ፡፡ ሐምሌ 8 ቀን 1978 ከነበረበት ቦታ ወልቃይት ማይሙሴ ወደሚባል ስፍራ ተዘዋውሮ አገልግሎቱን ቀጠለ፡፡ በ1981 ዓ.ም ደርግ አካባቢውን በአውሮፕላን መደብደብ ሲጀምር ጥቃቱን ሽሽት ወደ ጸገዴ ተራራ አቀና፡፡

በጸገዴ ተራራ ከሶስት ወራት በላይ አልተቀመጠም፡፡ 4 ሺ 600 ሜትር ሽቅብ ወደራስ ዳሽን ተራራ ወጥቶ ‹‹ሃይ›› የሚባል ቦታ ከተመ፡፡ የደርግ ማሳደድ ግን የሚገታ አልሆነም፡፡ በ1982 ከዳሽን ወደ ተንቤን ሀገረ ሰላም አጋብር ተቀየረ፡፡ በእዚያ ስፍራ ከትግርኛና አማርኛ ተጨማሪ ‹‹የሰፊው ኦሮሞ ህዘብ ደምጽ›› በሚል በኦሮምኛ ቋንቋ ስርጭት ጀመረ፡፡

ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢህአዴግ ስልጣን ሲቆጣጠር ጣቢያው ለሶስት ወራት በመቀሌ ቆይቶ በስተመጨረሻ ወደአዲስ አበባ ተዘዋወረ፡፡ በዚህ ጊዜ የጣቢያው ስያሜ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝቦች የሰላም የዴሞክራሲና የነጻነት ድምጽ (ኢህሰዴነድ)›› የሚል ነበር፡፡ በ1985 ዓ.ም. የወጣው የፕሬስ ነጻነት አዋጅ በስርጭት ላይ የነበሩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ መፍቀዱን ተከትሎ ሬዲዮ ጣቢያው በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡ እናም ለሁለት አመታት ጥናቶችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይቶ በ1987 ዓ.ም ‹‹ሬዲዮ ፋና›› በሚል መጠሪያ በአዲስ መክ ወደስራ ገባ፡፡

ፋና የሚለው መጠሪያ የተመረጠው በኦሮምኛና አማርኛ ቋንቋዎች ትርጉም ያለው ሆኖ በመገኘቱ መሆኑ ይነገራል፡፡ ፋና ማለት በአማርኛ ፈለግ፣ ብርሃን ማለት ሲሆን በአፋን ኦሮሞ ደግሞ ተከተለኝ፣ አብረን እንሂድ እንደማለት ነው፡፡

ሬዲዮ ፋና ስርጭቱ የተቃና፤ ይዘትና አቀራረቡ የተመቸ እንዲሆን ከአንጋፋው ኢትዮጵያ ሬዲዮ የቴክኒክ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በርካታ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ጋዜጠኞቹም ስልጠና ያገኙት ከእዚሁ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ አንጋፋ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እናም በአነስተኛ የሰው ሃይልና በኋላ ቀር የስርጭትና የስቱዲዮ መሳሪያዎች በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋዎች የሬዲዮ ስርጭቱን እንደ አዲስ ጀመረ፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ህብረተሰብ ተኮር ዝግጅቶችን በማሰናዳት ወደአድማጮቹ ያደርስ ጀመረ፡፡ በሂደትም አደረጃጀቱንና የፕሮግራም ይዘቱን እያሻሻለና ችግሮቹን እየቀረፈ ስርጭቱን ቀጠለ።

መጋቢት 14 ቀን 1990 እና 1991 ዓ.ም የአፋርኛ እና የሶማልኛ ቋንቋዎችን በመጨመር የአገልግሎት ቋንቋዎቹ ወደአራት እንዲያድጉ አደረገ፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው እስከ 1999 ዓ.ም ለአድማጮቹ ይደርስ የነበረው በአገር አቀፍ ደረጃ በመካከለኛና አጭር ሞገድ ነበር፡፡ ከመጋቢት 1 ቀን 1999 ዓ.ም ፋና ኤፍ ኤም 98.1ን በማስመረቅ ስርጭቱን ማዘመን ቻለ፡፡ ቀስ በቀስም ሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎችን ከፈተ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በ11 የክልል ከተሞች ባቋቋማቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች አማካኝነት የኤፍ ኤም ስርጭቱን በማስፋፋት በመላው ኢትዮጵያ ባሉት 12 የኤፍ̣.ኤም ጣቢያዎች ቀደም ሲል ከነበሩት ሶስት ቋንቋዎች ባሻገር ትግርኛ፣ ወላይታኛ እና ሲዳምኛ ቋንቋዎችን በማከል ተደራሽነቱን ማስፋት ቻለ፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው ከተቋቋመ ከ16 አመታት በኋላ ማለትም በጥር 2003 ዓ.ም ተቋሙ ‹‹ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት›› የሚል ስያሜን ያዘ፡፡ ተቋሙ ለበርካታ አመታት በሬዲዮ ዘርፍ ከቆየ በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አለ፡፡ ፋና ቴሌቪዥን ከወራት የሙከራ ስርጭት በኋላ ጥር 2010 ዓ.ም. በኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በይፋ ተመርቆ በሙሉ አቅሙ በአማርኛ ቋንቋ ወደ ስርጭት ገባ። ቀስ በቀስም የሚጠቀምባቸውን ቋንቋዎች በማብዛት በአሁኑ ወቅት በአማርኛ፣ አፋርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ እንግሊዘኛ እና አረብኛ ቋንቋዎች ዜናና የተለያዩ ዝግጅቶችን ያሰናዳል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው በሚያቀርባቸው ፋና ላምሮትና ጥበብ በፋናን የመሳሰሉ የመዝናኛ ዝግጅቶችና የተሰጥኦ ውድድሮች በተመልካች ዘንድ መወደድን ማግኘት የቻለ ሲሆን በሀገሪቱ በርካታ ተመልካቾች ካሏቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በቀን የ24 ሰአታት ስርጭት አለው፡፡

ዘመኑ በሚጠይቀው የኦንላይ ሚዲያ ዘርፍም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች በድረገፅ በኩል በኢትዮጵያ፣ አፍሪካና በመላው አለም ለሚገኙ ተመልካቾቹ ዝግጅቶቹን  ያሰራጫል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚጠቀሟቸው የማህበራዊ ትስስር ገፆች ዝግጅቶቹን በፅሁፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ እና በድምፅ ዝግጅቶቹን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ባለ 11 ወለል የሚዲያ ኮምፕሌክስ ባለቤት የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሙሉ በሙሉ ኤች.ዲ /HD/ የሆነ የቴሌቪዥን ስቱዲዮ በመገንባት በሀገሪቱ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ኤች.ዲ የሆነ የቴሌቪዥን ስርጭት በመጀመር ፈር ቀዳጅ መሆኑን ይናገራል፡፡

ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም የሚዲያ ተቋም የመሆን ህልም ያነገበው ተቋሙ ከአንድ ሺህ በላይ በሚሆኑ ባለሙያዎቹና ዘመኑ በደረሰባቸው ዘመናዊ መሳሪያዎች ዝግጅቶቹን ለአድማጭ ተመልካቾቹ በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሬዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎቱ ባሻገር የራሱን የቴክኖሎጂ፣ ጋዜጠኝነትና ኮሙዪኒኬሽን የስልጠና ማዕከልን በማቋቋም የስልጠናና ማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

 

ምንጮቻችን፡-

https://www.fanabc.com

አለም አቀፍ የሬዲዮ ቀንን በማስመልከት የካቲት 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያሳተመው መጽሄት

‹‹ሬዲዮ ትናንትና ዛሬ›› የካቲት 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያሳተመው መጽሄት

 

ማሞ ውድነህ – ደራሲው ጋዜጠኛ

Previous article

ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን)

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply