የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 12 ሐምሌ 2014
በመቅደስ ደምስ
ፀጋዬ ታደሰ በ1922 በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ፡፡ በልጅነቱ በቄስ ትምህርት ቤት ከፊደል እስከ ዳዊት ንባብና ቅኔ ተምሯል፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ከዚያም የአየር ኃይል አብራሪ ለመሆን የነበረው ፍላጎት ባለመሳካቱ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገባ፡፡ ከተቋሙ ከተመረቀ በኋላ ኢሉባቦር፣ ጎሬ ከተማና ሸዋ ውስጥ አዲስ ዓለም ከተማ፣ እንዲሁም ደብረብርሀን ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግሏል፡፡
ፀጋዬ በመምህርነት ሙያው ላይ እያለ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣን ያለማቋረጥ ያነብ ነበር፡፡ አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት፣ አንባቢነትና ለዜና የነበረው ፍቅር ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሳብ አድርጎታል፡፡ ከአንባቢነቱም አልፎ ለሄራልድ መጣጥፎችን ያበረክት ነበር፡፡
በኋላም ፀጋዬ ምኞቱ ሰምሮ በ1953 በዚያን ወቅት በአሜሪካዊው ዶ/ር ዴቪድ ታልቦት አርታኢነት ይመራ በነበረው የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ጀማሪ ዘጋቢ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ከፍተኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታውና አንባቢነቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የጋዜጣው ቀዳሚ የፓርላማ ዘጋቢ ለመሆን አብቅቶታል፡፡ የጋዜጠኝነት ትምህርት ባልነበረባት የያኔዋ ኢትዮጵያ ጋዜጣው ለፀጋዬ የሙያ ትምህርት ቤቱ ነበር፡፡
ምሰል አንድ: ፀጋዬ ታደሰ በኢትዮጵያ የሮይተርስ ዜና አገልግሎት ወኪል ዜና ዘጋቢ
ፀጋዬ የጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ተሞክሮውን ባገኘበት በኢትዮጵያን ሄራልድ የሰራው ለስድስት ዓመታት ነበር፡፡ በኋላም በ35 ዓመታት ቆይታ ወደ ሙያ ልህቀት በተጓዘበት ሮይተርስ የዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ ወኪል ዜና ዘጋቢ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የውጪ ወኪል ዜና ዘጋቢ ያደርገዋል፡፡
ፀጋዬ ታደሰ በምክር ቤት፣ በፍርድቤትና በአፍሪካ ህብረት ዘጋቢነቱ ሙያዊ አክብሮት ከማግኘቱም በላይ ከፍ ባለ የአርታኢነት ሙያዊ ክህሎቱም የተመሰገነ ነበር፡፡ የረጅም ዘመን አገልግሎቱም በበርካታ ታሪካዊ ሁነቶች ውስጥ አልፎ ከፍ ያለ የዜና እሴት ያላቸውን ሁነቶችና ክስተቶችን ለመዘገብ እድል ሰጥቶታል፡፡ ፀጋዬ በ1955 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ሲመሰረት የህብረቱን ምስረታ በዓይናቸው አይተው ለዓለም ከዘገቡ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ አገዛዝ የመጨረሻዎቹ ዓመታት ጀምሮ ተከስተው የነበሩ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና አሰቃቂ ታሪካዊ ሁነቶችን ዘግቧል፡፡ የ1965 የሰሜን ኢትዮጵያ አስከፊ ረሀብ፣ የ1966 አብዮትን፣ የደርግን መነሳትና የኃይለሥላሴን መውደቅ፣ በተከታታይ የተከሰቱ ጦርነቶችንና ግጭቶችን ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አገር ጥለው ሲወጡ በኢትዮጵያ ቦሌ አየር ማረፍያ ተገኝቶ በማየት ለውጭ መገናኛ ብዙሀን ያሳወቀ የመጀመርያው ጋዜጠኛም ነበር፡፡ በወቅቱ ቤተ መንግስት አካባቢ ከሚያውቀው አንድ ባለስልጣን የፕሬዝዳንቱን ሀገር ለቆ የመውጣት ዝግጅት በሚመለከት መረጃ ደርሶት ስለነበር የሰውዬውን እንቅስቃሴ ተከታትሎ ከየትኛውም ጋዜጠኛ በፊት የክስተቱን ዘገባ ለህዝብ አድርሷል፡፡ ከፍተኛ የዜና እሴት ያለውን ሁነት ቀድሞ በመዘገብ ላሳየው ሙያዊ ብቃት ሮይተርስ ሸልሞታል፡፡
ጸጋዬ ድህረ 1983 በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የታዩ አዎንታዊና አሉታዊ ሁነቶችንም ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያን ባህል፣ የተፈጥሮ መስህቦችና ታሪክ ለሌላው ዓለም በማሳወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ምስል ሁለት፡ ፀጋዬ ታደሰ ከግራ ወደ ቀኝ ከፊትለፊት ሁለተኛው
ፀጋዬ ዜናን በማነፍነፍና ፈጥኖ በመዘገብ ክህሎቱ በሙያ ባልደረቦች ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል፡፡ ረጋ ያለው ጠባዩ ጭምት ቢያስመስለውም የስራ ባልደረቦቹና በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ተግባቢና ጨዋታ አዋቂ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለሰላሳ አምስት ዓመታት የሰራበት ሮይተርስ ዜና አገልግሎት በብዙ ኢትዮጵያውን ዘንድ ‹‹ፀጋዬ ሮይተርስ›› የሚል መጠሪያ ላተረፈው ፀጋዬ ታደሰ የስራ ፍቅር፣ ሙያዊ ብቃት፣ በተለይም ዜናን በተዓማኒነትና በፍጥነት ስለመዘገብ ክህሎቱና ለተቋሙ አስተማማኝ ባለሙያ ስለመሆኑ ‹‹በከፍተኛ የሙያ ብቃትና የሥራ ፍቅር ከኢትዮጵያ ስለተሰጠ የዜና ሽፋን›› የሚል ምስክርነቱንና እውቅናውን ሰጥቷል፡፡
የሙያ ባልደረቦቹ ‹‹ዜና ሲዘግብ እንግሊዝኛ ቋንቋ ይታዘዝለታል›› የሚሉት ፀጋዬ ታደሰ፤ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች ማኅበርን ለዓመታት በመምራት የመሪነት ክህሎቱንም አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀንን ለማሻሻል ያበረከተው አስተዋጽኦም ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም መካከል ኢትዮጵያውያን ወጣት ጋዜጠኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሰማሩ፣ የውጭ ቋንቋ ክህሎታቸውን አሳድገው ዓለምአቀፍ ጉባዔዎችን በመዘገብ እንዲሳተፉ በማበረታታት ያደረገው ጥረት አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያን በተመለከተም ፀጋዬ በሮይተርስ የዜና አገልግሎት የኢትዮጵያን ባህል እና ወቅታዊ ሁኔታ በመዘገብ አገሩን በበጎ ማስተዋወቅ የቻለ የባለብዙ እውቀት ባለቤት ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ዘርፍ የ6ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚና የ10ኛው ዙር የሽልማት እጩ ነበር።
ፀጋዬ ታደሰ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ መምህርና የግል ማስታወቂያ ድርጅት ባለቤት ነበር፡፡ በትዳር አጋሩ፣ በስምንት ልጆቹና በሦስት የልጅ ልጆቹ ለቤተሰባዊ ስኬት የበቃው ይህ አንጋፋ ጋዜጠኛ በ92 ዓመቱ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም አረፈ።
ምንጮቻችን፡
Comments