የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ጳውሎስ ኞኞ፡ ራሱን በራሱ በማስተማር በሙያ ከፍ ያለ ጋዜጠኛ

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 14 ሐምሌ 2014

በመቅደስ ደምስ

ጳውሎስ ኞኞ ኅዳር 11 ቀን 1926 ምዕራብ ሐረርጌ፣ ቁልቢ አካባቢ ተወለደ፡፡ የወላጆቹን ፍቺ ተከትሎ ከሁለት ዓመቱ ጀምሮ ያደገው ከእናቱ ጋር ብቻ ነበር፡፡ የእናቱ በኑሮ ምክንያት ከቦታ ቦታ መዘዋወር ጳውሎስ በትምህርቱ ከአራተኛ ክፍል በላይ እንዳይገፋ እንቅፋት ሆነበት፡፡ ትምህርቱ የተቋረጠው በጣሊያን መውረራ ምክንያት ነበር የሚሉም አሉ፡፡ የትምህርት ጉዞው ከአራተኛ ክፍል አይሻገር እንጂ እናቱ መጻህፍትን የማንበብና የመጻፍ ፍቅር እንዲያድርበት አድርገዋል፡፡

 

ጳውሎስ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የገባው በድንገት ነበር፡፡ ነጋዴ መሆን ነበር የሚመኘው፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ከመግባቱ በፊት በልዩ ልዩ ተሰጥኦዎች ምክንያት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሞክሮ ለማግኘት በቅቷል፡፡ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል የእንስሳት ሕክምናና ሰዓሊነት ይገኙበታል፡፡ ይስላቸው ከነበሩ ስዕሎች መካከል የኢትዮጵያ አርበኞች ከፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ጋር ያደረጉትን ትግል የሚያሳዩና ሀይማኖታዊ ይዘት የነበራቸው ስእሎች ይገኙበታል፡፡ ሥዕሎቹንም ይሸጥ ነበር።

ጳውሎስ የጋዜጠኝነት ሙያ በርን ማንኳኳት የጀመረው የሰአሊነትና የእንስሳት ሕክምና ሙያዎችን በሚመለከት ይሰማው የነበረውን ቅሬታ የሚገልጹ መጣጥፎችን ለጋዜጦች በመላክ ነበር፡፡ ለፍቅረኛው ያለውን ፍቅር በመግለጽ ጽፎ ለጋዜጦች ይልካቸው የነበሩ ግጥሞችም ወደ ጋዜጠኝነት እንዲያመራ መንገድ ከፍተውለታል፡፡ በኋላም በ1940ዎቹ አጋማሽ አዲስ በተከፈተው «የኢትዮጵያ ድምጽ» ጋዜጣ በጋዜጠኝነት ተቀጠረ፡፡ ቆይቶም የጋዜጣው ምክትል ዋና አዘጋጅ መሆን ቻለ፡፡ በተለይም ለጋዜጣው የቅዳሜ ዝግጅቶች ጳውሎስ በርካታ ጽሁፎችን ይጽፍ ነበር፡፡

ጳውሎስ ከአመታት ቆይታ በኋላ ‹የኢትዮጵያ ድምጽ›ን በመተው ወደ ‹አዲስ ዘመን› ጋዜጣ አመራ፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቆይታው በወታደራዊው ደርግ አገዛዝ ዘመን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጠጥኑ ጠጠር ያሉ ጽሁፎችን ይጽፍ ነበር፡፡ በተለይ «አንድ ጥያቄ አለኝ» በሚለው የ‹አዲስ ዘመን› ጋዜጣ አምዱ ተወዳጅነትና ታዋቂነትን አትርፏል። በእለት ተእለት ህይወቱ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነትና በጽሁፎቹ ላይ በሚስተዋለው ጨዋታ አዋቂነቱም ይታወቃል፡፡

ጳውሎስ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ በተለይ የሚታወቀው ራሱን በማስተማር ችሎታውና ስኬቱ ነው፡፡ ለመማርና ለማወቅ የነበረው ከፍተኛ ጉጉት፣ በቀላሉ የማይረካ የንባብ ጥማቱና ታታሪነቱ ራሱን ለማብቃት አስችሎታል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ መጻህፍትንና መጽሔቶችን በማንበብ የቋንቋ ችሎታውን አሳድጓል፡፡ በንባብ ያበለጸገው የቋንቋ ክህሎቱም በርካታ በእንግሊዝኛ የተጻፉ ጽሁፎችን ወደ አማርኛ በመተርጎም ለጋዜጣው አንባቢዎች ለማቅረብ ከመቻሉም በላይ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችንም እንዲያዘጋጅ አስችሎታል፡፡

ይህ ጥረቱ ጳውሎስ ከጋዜጠኝነት ሙያው ባሻጋር ታላቅ ጸሀፊ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ የጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችውን ወረራ የሚመለከተውን መጽሐፍ ጨምሮ 11 መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብና የተለያዩ ልብ ወለዶችንም ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከእነኚህ መሀከል «ዳግማዊ አጼ ምንሊክ» አንዱና ተወዳጁ ስራው ነው፡፡ ‹ከሴቶቹ አምባ›፣ ‹የአራዳው ታደሰ›፣ ‹የጌታቸው ሚስቶች›፣ ‹ድብልቅልቅ›፣ እና ‹የኔዎቹ ገረዶች› ከአጫጭር ልብወለዶቹ መሀከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ጳውሎስ በሙያው ስኬትና ተወዳጅነትን ሲያተርፍ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሟል፡፡ ፈተናዎቹ ከመንግስት አካላት፣ ከተወሰኑ አንባቢያንና የሙያ ማህበራት ጋር የተያያዙ ነበር፡፡ በእሱ የጋዜጠኝነት ዓመታት ስልጣን ላይ ያሉት አገዛዞች ትችትን የማይቀበሉ የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ሀገራት የሚተቹ ጽሁፎችንም መጻፍ ይከለክሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ጳውሎስና ሌሎች ጋዜጠኞችና ጸሐፍት በሙያቸው ህዝባቸውን ያገለገሉት ህይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ነበር፡፡

ጳውሎስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጡረታ ሲወጣ ሙሉ ጊዜውን ለድርሰቶቹ ሰጠ፡፡ ከዓመታት በኋላ በ1983 የካበተ ልምድ ካላቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች ጋር በጋራ በመሆን የግል ህትመት ሚዲያ ለመመስረት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ በዓመቱም ከረጅም ጊዜ የስራ ባልደረባው ከፍአለ ማሞ ጋር በጋራ በመሆን «ሩህ» የተሰኘ ጋዜጣ አቋቋሙ፡፡

ሆኖም ጳውሎስ ሰኔ 13 ቀን 1988 በአጥንት ካንሰር ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ጳውሎስ በህይወት ሳለ ያላሳተማቸው ስድስት መጻህፍት ነበሩት፡፡ ከእነዚህም መካከል የአጼ ምንሊክ ደብዳቤዎች ስብስብ የሆኑት ሁለቱ ስራዎቹን በ2004 የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ወጪያቸውን ሸፍኖ አሳትሟቸዋል፡፡

 

ምንጮቻችን፡

Mesert Chekol. (2013). The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia. University Press of America.

ደረጀ ትእዛዙ፤ ጳውሎስ ኞኞ ከ1926-1988 ዓ.ም፡፡ በ2014 የታተመ መጽሐፍ፡፡

አዲስ አድማስ ጋዜጣ

Previous article

ብዙ ወንድማገኘሁ አለሙ:- በሁለት የፖለቲካ ዘመናት ውስጥ ያለፈ ጋዜጠኝነት

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply