የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 12 ሚያዚያ 2022
በፍቃዱ ዓለሙ
በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት እድገት ታሪክ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ፈር ቀዳጅ ጋዜጠኞች አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ እሌኒ መኩሪያ ከአባታቸው ከአቶ መኩሪያ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ወ/ሮ ሶስና ወርቅነህ በ1934 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ ተወልደፈው ማደጋቸውን ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ እሌኒ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሐኪም ዶ/ር ወርቅነህ እሸቴ የልጅ ልጅ ሲሆኑ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲስ አበባ በልዕልት ዘነበ ወርቅና በሳንድ ፎርድ ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ በመቀጠል በ1951 ዓ.ም. በሊባኖስ ቤይሩት ከተማ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የነርስ ትምህርት ለአንድ ዓመት የተማሩ ሲሆን ከቤይሩት መልስ አዲስ አበባ ዩቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ለማጥናት ተመዝግበው ውጤት እየተጠባበቁ ሳለ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ለእንግሊዘኛ ቋንቋ ፕሮግራም ጋዜጠኛ ይፈልግ ስለነበረ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1952 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ተቀጠሩ፡፡ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ጋዜጠኛ ወ/ሮ ሮማን ወርቅ ካሳሣሁን ሲሆኑ ወ/ሮ እሌኒ መኩሪያ ደግሞ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የቴሌቭዥን ጋዜጠኛ በመሆን በቀዳሚነት ስማቸው ሰፍሯል።
በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋምና ተመርቆ ስራ ሲጀምር እንደ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተናጋሪ እንደሚቆጠሩም የቀድሞ ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ። ወ/ሮ እሌኒ በጋዜጠኝነት ከተሰማሩ በኋላ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የጋዜጠኝነት ትምህርት ተከታትለዋል። በሚዲያው ዘርፍ ከዓለም አቀፍ አገልግሎት በተጨማሪ በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅ ብሔራዊ አገልግሎት በዜና አንባቢነት: በሙዚቃና መዝናኛ ፕሮግራሞች አዘጋጅነት፣ በቃለ ምልልስ መድረክ መሪነት መስራታቸውን ታሪካቸው ያስረዳል።
ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ በማስታወቂያ ስራም የተካኑ ሲሆን በተለይ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አማካኝነት ይሠሩ የነበሩ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎችን ከሚያቀርቡ ጋዜጠኞች መካከል እሌኒ መኩሪያ ዋነኛዋ ነበሩ፡፡ ጋዜጠኛ እሌኒ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ በቢ.ቢ.ሲ. (BBC): በጀርመን ድምፅ ሬዲዮ (ያሁኑ ዶቼቬሌ) በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በማገልገል በሙያቸው የረጅም ዘመን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በጋዜጠኝት ለ36 ዓመታት የሰሩ ከመሆናቸው ባሻገር የኢትዮጵያ ሴት የመገናኛ ብዙሃን ማኅበር መሥራች አባልና አመራር እንዲሁም የአፍሪካ ሴቶች የሚዲያ ኮሚቴ አማካሪዎች ቦርድ አባልም ነበሩ፡፡
ወሮ እሌኒ መኩሪያ ከባለቤታቸው ከኢንጅነር ሰይፉ ለማ ጋር በትዳር ተጣምረው ሦስት ልጆችን ወልው በማሳደግ ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡
ወሮ እሌኒ መኩሪያ ባደረባቸው ህመም ምክንያት ለረዥም ጊዜያት በሕንድ እና በእንግሊዝ ሀገር ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ሐምሌ 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የመረጃ ምንጮች
- The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia, በመሠረት ቸኮል (ደ/ር), 2013,
- ሪፖርተር ጋዜጣ ፣ 2013 ዓ.ም፣ ሐምሌ እትም
- የጀርመን ድምፅ (ዶቼቬሌ) ሬዲዮ
Comments