የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 10 መስከረም 2015
በመቅደስ ደምስ
በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ውስጥ ከቀደምቶቹ ተርታ ስሙ ይነሳል፡፡ እሱን በሬዲዮ መስማት ሜዳው ውስጥ ቀጥታ ጨዋታን ከመከታተል የበለጠ ሀሴትን ያጎናጽፋል ይባልለታል፡፡ በዘመኑ ‹‹እግር ኳስን በሬዲዮ የሚያሳይ›› እስከመባል ደርሷል፡፡ ስመጥሩ የቀጥታ ዘገባ ባለሟል ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ፡፡
ደምሴ በድሬደዋ ከተማ በ1947 ተወለደ፡፡ ደምሴ የጋዜጠኝነት ህይወት መሰረቱ አባቱ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ በወቅቱ ጠንካራ የሚባለው የድሬዳዋ ስሚንቶ ውስጥ ይሰሩ የነበሩት አባቱ ደምሴን ከሰባት አመት እድሜው ጀምሮ ወደ ድሬዳዋ ስታዲየም ይወስዱት ጀመር፡፡ ደምሴ የአባቱን ቡድን በመደገፍ በኳስ ፍቅር ተለከፈ፡፡ ስታዲየም ቤቱ ሆነ፡፡

ምስል አንድ፡- ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ
በድሬዳዋ ከተማ አሸዋማ ስፍራዎች ላይ ይደረጉ የነበሩ የታዳጊ ህጻናትና የወጣቶች የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ሌሎቹ የደምሴ የስፖርት ጋዜጠኝነት መሰረት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የደምሴ ትልቅ የኳስ ፍቅር በተጫዋችነት የሚገለጽ አልነበረም፡፡ በንቁ ተመልካችነት፣ በታዛቢነትና በደጋፊነት እንጂ፡፡ የእርሱ ትኩረትና ሕልም መጫወት ሳይሆን መዘገብ ነበር፡፡ እናም ገና በታዳጊነቱ ጋዜጣ እየገዛ ያነብ ጀመር። የስፖርት አምድ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው። ጋዜጦቹን የሚገዛው ለመረጃ ምንጭነት ብቻ ሳይሆን የሙያ ብቃቱንም ከፍ ለማድረግ እንዲያግዘው ጭምር ነበር፡፡ በጋዜጣው ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንደሰለሞን ተሰማ በፍጥነት ለማንበብ ጥረት ያደርግ ነበር። አንዱን ገጽ ለማንበብ ስንት ደቂቃ እንደፈጀበትም ወዳጁን ያስመዘግባል። አንጋፋው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ፤ ደምሴ እጅግ አብዝቶ ያደንቀውና እንደ እርሱ በሆንኩ ብሎ ይመኘው የነበረ ሰው ነበር፡፡
ደምሴ የስፖርት ጋዜጠኝነቱ ኋላ ላይ ሙያው እንደሚሆን ሳያውቅ ገና ተማሪ እያለ በትምህርት ቤቱ ‹‹ሚኒሚዲያ›› ውስጥ ይሳተፍ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ስለ ጨዋታዎች የሚያዘጋጃቸውን ዘገባዎች የተመለከቱት መላኩ ወልደማሪያም የተባሉ መምህሩ ስለሐረርጌ ስፖርት እንቅስቃሴ አንድ ሀተታ እንዲያዘጋጅ ያዙትና የምስራች ሬዲዮ ላይ ለሚሰራው ሰለሞን ተሰማ ይልኩለታል፡፡ ከእዛ በኋላ ሰለሞን በተከታታይ የደምሴ ዘገባዎች ይደርሱት ጀመር፡፡ እርሱም አዘጋገቡን ስለወደደው ያበረታታው ነበር፡፡
በ1962 ገና ታዳጊ እያለ ደምሴን ወደ ስፖርት ጋዜጠኝነት እንዲገባ ያደረገ ትልቅ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚቴ አባላት የስራና የቤተሰብ ኃላፊነት ጫና የነበረባቸው ሰዎች በመሆናቸው የስፖርት ዘገባውን አጠናቅሮ ለዜና የማብቃት ድክመት ጎልቶ ይታይባቸው ነበር። ይህን ክፍተት በመጠቀም ደምሴ የሕይወት ጥሪውን ለማሳካት ብቅ አለ፡፡ ሕልሙን እውን ለማድረግ የነጻ አገልግሎት ለመስጠት ጠይቆ ተፈቀደለት፡፡ በሙያው መደበኛ ስልጠና ሳይኖረው ትምህርቱንና የስፖርት ዘጋቢነቱን አጣምሮ ያዘ። ነፃ የስልክ አገልግሎትና ነፃ የስታዲየም መግቢያ ካርድ ተሰጥቶት አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ያ ታዳጊ ልጅ የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪዎችን ቀልብ ለመግዛት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በየመንገዱ እየጠራ አድናቆቱን የሚቸረው የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪ በረከተ። ‹‹አማተር ጋዜጠኛ›› የሚለውን ስያሜም አገኘ፡፡
ደምሴ ከተመልካች አድናቆት እንደሚቸረው ሁሉ አልፎ አልፎ በእግር ኳስ ተጫዋቾች በተለይ በተከላካዮችና በግብ ጠባቂዎች እርግጫና ጥፊን ይቀምስ እንደነበር ይነገራል። አጥቂው ተከላካዩን እንዴት ሸውዶት እንዳለፈው፣ ግብ አግቢው በረኛውን አንጠልጥሎት ኳሷን ከመረብ እንዴት እንዳዋሀዳት ለመግለጽ የሚጠቀማቸው ቃላት ለዱላ የሚዳርጉት ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። ያንን ሳይፈጽም እየቀረ የተመለከተውን በተሰማው መንገድ ገልጾ ለሙያው ሲል ዱላ ይቀምሳል። ይሁን እንጂ እንዲህ የነፍሱ ያክል የሚወደው ሙያው ህይወቱን የሚመራበት ጥቂት ሳንቲም እንኳን አያስገኝለትም ነበር፡፡ በአማተር ጋዜጠኝነት በነጻ ማገልገል የጀመረ ሰሞን የድሬዳዋ ህዝብ ከኪሱ በማዋጣት ነበር የስልክ ወጪውን እንኳ የሚሸፍንለት፡፡
የአስረኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ በተካሄደ ጊዜ ግን የደምሴ ህይወት ተቀየረ፡፡ ውድድሩን ለመዘገብ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች የሆኑት ሰለሞን ተሰማና ባልደረባው ይንበርበሩ ምትኬ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ያቀናሉ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን ደምሴ ይታመምና ቤት ይውላል፡፡ ሰለሞንና ይንበርበሩም ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የሙያ ባልደረባቸውን ለመጠየቅ ወደ መኖሪያ ቤቱ ባቀኑበት ወቅት ደምሴ በምን አይነት አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ሆኖ ለብዙ ጊዜያት በነፃ ሲያገለግል እንደቆየ ይረዳሉ፡፡ በወቅቱ ደምሴ እናትና አባቱ በመፋታታቸው የሚኖረው ከባለትዳር እህቱ ጋር ነበር፡፡ ነገር ግን ከአባቱ ከምትደረግለት ትንሽ ድጎማ ቆጥቦ፤ አለባበሱን አሳምሮ መታየቱ ጥሩ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የመጣ ያስመስለው ነበር፡፡
እነ ሰለሞን የደምሴ ሁኔታ እንደከነከናቸው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የሥራ ኃላፊ በዚያን ሰሞን ከሀገር ወጥቶ ባልተመለሰው የሰለሞን ተባባሪ አዘጋጅ ነጋ ወልደ ሥላሴ ምትክ ሌላ አማተር ጋዜጠኛ ለመቅጠር በሂደት ላይ ነበሩ፡፡ እነ ሰለሞን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ደምሴ ለዓመታት በነፃ ሲያገለግል በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ሆኖ እንደ ነበር አለቃቸውን በማስረዳት ሀሳባቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ይጎተጉቱ ጀመር፡፡ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበረው በአሉ ግርማም ‹‹ከሐረርጌ የሚዘግበው ታዳጊ ይምጣ›› ሲል ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ደምሴም በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ በማቅናት እድሜ ዘመኑን ያገለገለበት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የስፖርት ጋዜጠኛ ሆነ፡፡ ከአማተር ጋዜጠኝነት ወደ መደበኛ ጋዜጠኝነት ተሸጋገረ። ጋዜጠኝነት ሙያው ሆነ። በርቀት ያደንቃቸው የነበሩት ጋዜጠኞች እጁን ይዘው ከደረሱበት አደረሱት፤ በሙያው አንቱ ተባለበት። በሐረር የተገደበው እውቅናውም በመላ ሀገሪቱ ናኘ፡፡ የድርጅቱ አባል በሆነ በዓመቱ ‹‹የአመቱ ወጣት ኮከብ ጋዜጠኛ›› ለመሆን በቃ፡፡
ደምሴ ለሙያው የነበረው ትጋትና ፍቅር ልዩ እንደነበር ይነገርለታል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድሎችን ሲያስመዘግቡ በውድቅት ሌሊት ጭምር አደጋዎችን እየተጋፈጠ ከቤቱ ወደ ቢሮው በመሄድ ድሉን የመስማት እድሉ ለሌለው ሕዝብ ያበስር ነበር።
በስሜት ተሞልቶ ውድድሮችን በቀጥታ ለሕዝብ የሚያደርስበት የዘገባ አቀራረብ መንገዱ ለየት ያደርገዋል፡፡ ‹‹የአንበሳ ግልገል›› እና ‹‹ጀግና›› በሚሉ ቃላት አትሌቶችና እግር ኳስ ተጫዋቾችን ያሞካሻል፣ ያበረታታል፣ ያደንቃል፡፡ በግጥም ያወድስም ነበር። በተለይ ‹‹የምን ማራዶና የምን ፔሌ ፔሌ፣ እኛም አገር አለ ገብረመድኅን ኃይሌ›› የምትለው ጎልታ የምትጠቀስለት ግጥሙ ነበረች።
ኢትዮጵያ ያስተናገደችው የ1980ው 15ኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ/CECAFA) ሲነሳ ደምሴ ዳምጤም አብሮ ይነሳል፡፡ በዚህ ውድድር ለፍፃሜ የቀረቡት የኢትዮጵያና ዚምባብዌ ብሄራዊ ቡድኖች ነበሩ። በዕለቱ አንድ የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን የአቻነት ግብ አገኘ፡፡ በዕለቱ ጨዋታውን ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ እንባና ሳቅ እየተናነቀው ‹‹… ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ …›› እያለ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ የደስታና ሲቃ ስሜት በተቀላቀለበት ድምጽ ያሰማው የደስታ ጩኸት ከብዙ ሰው አዕምሮ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ የደምሴ ድምፅ የሬድዮ የስፖርት መሰናዶዎች መግቢያ ድምጽ እስከመሆን ደርሷል፡፡ የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥ ዳኛቸው በመጨረሻ ለሚመታት ምት ደምሴ ‹‹ዳኙ ገላግለን›› ብሎ የተጠቀመው ንግግር ቅጽል ስሙ ሆኖ ነበር፡፡ ራሱ ደምሴም ቢሆን ጨዋታው በስፖርት ጋዜጠኝነት ህይወቱ ሁሌም የሚያስታውሰውና የሚያስደስተው አጋጣሚ መሆኑን ይናራል፡፡
ለስፖርት ዘገባ ከሰላሳ በላይ ሀገራትን የዞረው ደምሴ የአትላንታ፣ የአቴንስና ቤጂንግ ኦሊምፒኮችን በስፍራዎቹ በመገኘት በማይረሳ አዘጋገብ ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተላልፏል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናዎችን፣ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን፣ የአገር አቋራጭ ውድድሮችን፣ የዓለምና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን፣ ተዘርዝረው የማያልቁ ስፖርታዊ ውድድሮችን እየተመለከተ ዜናውን ለሕዝብ አድርሷል። ከሀገሩ እግሩ የወጣበትን አጋጣሚ ተጠቅሞ እዛው እንዲቀር በርካቶች ጎትጉተውት ነበር፡፡ እሱ ግን በሀገሩ የሚደራደር አልሆነም፡፡
ደምሴ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ብዙ ለፍቷል፡፡ እድሜ ልኩን በሚቆጭበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ በሙያው የተቻለውን ሞክሯል፡፡ ለእግር ኳስ ቁጭቴ መካሻ ነው የሚለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት እንዲያድግም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ከጋዜጠኝቱ ባሻገር የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አመራር አባል በመሆን አገልግሏል፡፡
የስፖርት የቀጥታ ስርጭትን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ስሙ በቀዳሚነት የሚነሳው ደምሴ ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ከ40 ዓመታት በላይ ሙያዊ አስተዋጽኦውን አበርክቷል።
በተለያዩ ወቅቶች በጀርመን፣ አሜሪካ፣ ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ ከወሰዳቸው አጫጭር ስልጠናዎች ውጪ በሙያው ይህ ነው የሚባል መደበኛ ትምህርት የሌለው ደምሴ በንባብ ሙያዊ አቅሙን በማጎልበት ራሱን አብቅቷል፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን በተመለከተ ሲናገር ‹‹በሙያው ተምሬ ያካበትኩት እውቀት ሳይኖረኝ ከሕዝብ ተምሬ ነው ሕዝብ ያገለገልኩት›› ብሎ ነበር፡፡
በባህርይው ተግባቢና ሰላምተኛ የሆነው ደምሴ በባልደረቦቹ ዘንድ ተወዳጅ ነበር፡፡ ለብዙ ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞችም የሙያ ተምሳሌት ነው፡፡ ደምሴ ለሶስት ዓመታት በህመም ምክንያት ከሚወደው ሙያው ተለይቶ ህክምናውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሲከታተል ከቆየ በኋላ ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበር።
ምንጮቻችን፡-
- አዲስ ዘመን፤ (ከአንተነህ ቸሬ) ‹‹ለ40 ዓመታት በትጋት ያገለገለው ድምፅ›› ሚያዝያ 21/2012
- ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት፤ ‹‹ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ አረፈ››
https://waltainfo.com/am/27002/ (November 6, 2012)
- ሰባተኛ – የስፖርት ጋዜጠኛው ደምሴ ዳምጤ
https://www.youtube.com/watch?v=sAKCVfnCQsY (August 8, 2020)
Comments