ይማሩ /MIRH/ 14 ጥቅምት 2015
በስንታየሁ አባተ
የግጭት ምንነት
ግጭት በተፈጥሮና በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ ያለና ሁሌም የሚኖር እውነታ ነው፡፡ የግጭት ዋነኛ ምክንያት ልዩነት ነው፡፡ ልዩነት ሊጠፋ እንደማይችል ሁሉ ግጭትም አይጠፋም፡፡ ሰዎች ሁሌም በግጭት ውስጥ ይኖራሉ ወይም ከግጭት ነጻ የሆነ ማህበረሰብ የለም፡፡
የግጭት ምክንያት የሆነው ልዩነት በተለያዩ መልኮች ሊከሰት ይችላል፡፡ የሀብት ውስን መሆንና በፍትሓዊነት አለመከፋፈል፣ ተቃርኖ እንዳላቸው በሚያምኑ ሁለት ወገኖች መካከል በቂ ወይም ምንም ዓይነት ውይይት አለመኖር፣ ተጋጪዎቹ አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸው የተዛባ አመለካከትና እምነት፣ ያልተፈታና ካለፈ ታሪክ የሚቀዳ የበቀል ስሜት እና የስልጣን ክፍፍል ኢ-ፍትሓዊነት በመላው ዓለም የግጭት መነሻዎች ተብለው የሚታወቁ ናቸው፡፡
የዘውግ ፖለቲካ በገነነባቸው አገራት ደግሞ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ትርክቶችና እነሱ የሚያስከትሏቸው ተቃርኖዎች ሰብኣዊ ቀውሶችን ለሚያመጡ ግጭቶችና የእርስ በእርስ ጦርነቶች ምክንያት ይሆናሉ፡፡
ሰዎች በሀብት ሽሚያና ክፍፍል፣ በአስተሳሰብ፣ በአስተያየትና በእምነት ልዩነት ምክንያት ወደ ግጭት ማምራታቸው የተለመደ ነው፡፡ በማህበረሰብ ውስጥ የፍትህ መጥፋት፣ የኑሮ ዋስትና ማጣት፣ የህልውና አደጋ ላይ መውደቅ፣ ጭቆና፣ መገለልና የማንነት ክብር መነፈግ ስር ለሰደደ ግጭት መነሻ ይሆናሉ፡፡
ግጭት በቀጥታ አስተውሎት ከማይታይበት የእምቅ ደረጃ ተነስቶ እያዘገመ በማደግ ጉልህና ውስብስብ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ መፍትሄ ካልተበጀለትና ነባራዊ ሁኔታን የግጭቱ ባህሪ ወደሚሻው ለውጥ መውሰድ ካልተቻለ ወደ ሁከትና ነውጥ፣ ወደ ውድመትና ጥፋት ሊያመራ ይችላል፡፡ በአግባቡ ከተያዘ ወደ ነውጥና ጥፋት ሳያመራ ለሰዎች የጋራ እድገት የሚበጅ መንገድ ሊከፍት ይችላል፡፡
ይህም ግጭት በራሱ ጥሩም መጥፎም እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ግጭትን ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርገው የሰዎች አያያዝ ነው፡፡ ግጭት በጥበብ ከተያዘ ሰዎች የአዎንታዊ ለውጥና የእድገት መሳሪያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የአንድን ግጭት ምንነት የማህበረሰቡ አባላት በጋራ ለመገንዘብ ከተጉና የጋራ መፍትሄ ለማግኘት ፈቃድ ካላቸው ግጭት የመጠፋፋት ምክንያት መሆኑ ቀርቶ ወደ ጋራ ልማት ሊወስድ ይችላል፡፡
ግጭትና ሉላዊ ሁኔታዎች
ግጭት አሁን ላለው የዓለም ስርዓት መፈጠር ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ከቅርብ አበይት የታሪክ ክስተቶች በመነሳት ለመመርመር ቢሞከር እንኳ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእስያና በአፍሪካ የተከሰቱ ግጭቶችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ግጭቶቹ ወደ አውዳሚና በላዔሰብዕ ጦርነቶች ከመሸጋገራቸው በፊት በሰዎች አስተሳሰብ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ እምነትና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ደረጃ የታዩ ልዩነቶችና ቅራኔዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ ማህበረሰቦች ግጭቶቹን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ተስኗቸው በተቀሰቀሱት ጦርነቶች ሚሊዮኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1991 የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ጎራ መፍረስን ተከትሎ ገሀድ የወጡ ማህበረሰባዊ ልዩነቶች ወደ ግጭትና ነውጥ አድገው በምስራቅ አውሮፓ የተቀሰቀሱት ጦርነቶች ውድመትና ጥፋት አድርሰዋል፡፡ መካከለኛው ምስራቅ በማያቋርጥ ግጭትና ጦርነት መታወኩን ቀጥሏል፡፡
ከ1996 እስከ 2006 ባሉት አሥር ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህፃናት ተገድለዋል፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወላጆቻቸውን አጥተዋል፤ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደግሞ የከፋ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአፍሪካ አህጉር በሱዳን፣ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በርዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ በመካከለኛው አፍሪካ፣ በናይጄሪያ፣ በላይቤሪያና በሌሎች አገሮች በተቀሰቀሱ ጦርነቶች ሚሊዮኖች አልቀዋል፡፡ በርካታ አገሮች ከገቡባቸው ጦርነቶች መውጣት አቅቷቸው በወደቁ አገረመንግስታት መዝገብ ውስጥ ሰፍረዋል፡፡ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶርያና አፍጋኒስታን ከእነዚህ ተርታ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ግጭትና መገናኛ ብዙሃን
ግጭቶች የሚያደርሱት ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ መገናኛ ብዙኃን ለእንዲህ ዓይነት ዘገባዎች የበለጠ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ሰዎች በባህሪያቸው ስለ አሉታዊ ወይም የተለዩ ክስተቶች የማወቅ ጉጉት ስላላቸው ለውጥ፣ ልዩነት፣ ያልተለመደ ክስተት፣ ግጭትና ነውጥ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ እንደ ዜና እሴት ይቆጠራሉ፡፡ በሌላ በኩል የመገናኛ ብዙሃን አሉታዊ ዘገባዎችን በሂሳዊ ዓይን የሚያዩ ታዛቢዎች ለዘገባዎቹ ዝንባሌ “መርዶ ነጋሪነት” የሚል ቅጽል እስከመስጠት ድረስ ዜናና ግጭት የተቆራኙ ሆነዋል፡፡
ይህም አሉታዊ ዝንባሌ መገናኛ ብዙኃንና የግጭት ወቅት ዘገባቸው ምን መልክ ሊኖረው ይገባል? የሚል ጥያቄ ቀስቅሷል፡፡ የጋዜጠኞችስ አዘገጋብ ምን መልክ ቢኖረው ይበጃል? የሚለውን ጥያቄ ይህ አጭር ጽሁፍ ይመለከታል፡፡
ሓላፊነት የተሞላበት የግጭት አዘጋገብ ሊኖር እንደሚገባ የሚመክሩ ጥናቶች እንደሚሉት ጋዜጠኞች ስለ ግጭት ሲዘግቡ ከወትሮው የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግጭቱ ወደ ነውጥ ያላመራ በልዩነትና ውጥረት ብቻ የሚገለጽ ችግር ከሆነ የችግሩን ምንነትና የሚገኝበትን ደረጃ በሰከነ ቋንቋ፣ በሚዛናዊነትና መፍትሄ ላይ ባተኮረ አቀራረብ ሊዘግቡ ይገባቸዋል፡፡
ዘገባቸው ስሜትና ቁጣ ቀስቃሽ በመሆን በቂምና በበቀል ግጭትንና ነውጥን እንዳያባቡሱ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ገለልተኛ አቋም መያዝ፣ ትክክለኛና የተሟላ መረጃ መያዛቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወደ ሁከትና ነውጥ የተሸጋገረ ግጭት ባለበት አውድ ውስጥ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች መገናኛ ብዙኃኑ ላይ የበላይ መሆን ስለሚሹ መረጃው ተዓማኒና ከቅድመ ምርመራ የጸዳ መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡
ጋዜጠኞች በግላቸው ጭምር ደኅንነታቸው አደጋ ውስጥ የሚገባበትም ወቅት መኖሩን አስበው የራሳቸውን ደኅንነት ማስጠበቂያ እርምጃዎች እየወሰዱ (ከአለባበስ እስከ መውጫ መንገዶችን ቀድሞ መለየት) መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡
ስለ ግጭት የማወቅ አስፈላጊነት
ለጋዜጠኞች ለውጥ በራሱ ዜና ነው፡፡ ለውጥ ሲኖር ደግሞ በለውጡ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል አለመግባባት ወይም “ግጭት” ይኖራል፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኞች ስለግጭት መሰረታዊ ጉዳዮችም ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ግጭት ሲባል ሁሌም ደም አፋሳሽ የሆነውን ነገር ማየት ስህተት ነው፡፡ ይልቁንም ግጭት ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋር፣ አንድ ቡድን ከሌላ ቡድን ጋር፣ አንድ አገር ከሌላ ሉኣላዊ አገር ጋር የሚገቡበትን መቃቃርና አለመስማማት ሁሉ የሚጠቀልል ነው፡፡ ስለግጭቶች ዓይነትና ባህሪያቸው ማወቅ የጋዜጠኞች የቤት ሥራ ነው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች የታመመን ሰው ለማከም ሲነሱ የህመሙን መነሻና መድኃኒቱ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉት ሁሉ ጋዜጠኞችም ግጭትን ለመዘገብ ሲነሱ የግጭቱ መሰረታዊ ምክንያትና መፍትሔው፣ እድገትና መድረሻው ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለባቸው፡፡ ስለ ግጭቱ መሰረታዊ ምክንያት ሳይረዱ ግጭትን መዘገብ በየትኛውም መመዘኛ ሚዛናዊና ሁሉን ያካተተ ዘገባ ሊያስገኝ አይችልም፡፡
ግጭት ከመነሻው በአግባቡ ከተያዘና ልዩነት እንዳላቸው የሚያስቡ ሁለት ወገኖች ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ከቻሉ ግጭት አዎንታዊ ለውጦችን ሊፈጥር ሲችል፤ በዚህ ተቃራኒ የተመራ አለመግባባት ግን ወደ ደም አፋሳሽ ነውጥ ሊሸጋገር ይችላል፡፡
ይህ ጽሑፍ ውስጥ በሁለት ወገኖች መካከል የሚከሰትና ከመነሻው በአግባቡ ባለመያዙ ወደ ደም አፋሳሽነት የሚያመራ የግጭት ዓይነትን ይዳሰሳል፡፡
የደም አፋሳሽ ግጭት መነሻዎች
ባህል መር መግፍኤዎች– አንድ ቡድን ስለሌላው ወገን ለዓመታት የሚናገራቸው፣ የሚስላቸውና የሚያምንባቸው እሳቤዎች ናቸው፡፡ እሳቤዎቹ አካላዊ የሆነውን ደም መፋሰስ የሚያጋግሉ ዓይነተኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህም እንደ ጥላቻ ንግግር፣ “መጤ” ጠልነት፣ አንደኛው ወገን እንደ ጠላት ሌላው እንደ ጦር ጀግናው የሚተርካቸው ተረኮች፣ ጦርነትን የሚያወድሱ ስነቃሎች ሀይማኖታዊ መከራከሪያዎች፣ ጾታዊ ማግለሎች፣ ተቋማዊ ጥላቻ፣ ቅኝ ግዛት፣ ጽንፍ የወጣ ብዝበዛ፣ ድኅነት፣ ሙስና፣ ማጭበርበርና ሰዎች ያለፍላጎታቸው ተከፋፍለው እንዲኖሩ የሚያስገድዱና የሚገፋፉ የሕግ ማዕቀፍና ትርክቶችን ያጠቃልላሉ ፡፡
ጋዜጠኞች ሊያውቁና ሊመልሷቸው የሚገቡ ጥያቄዎች
ለዓመታት በሚብላላ ገፊ ምክንያት ድንገት ገንፍሎ የሚወጣን አካላዊ የሆነ ደም አፋሳሽ ግጭት ማስቆም ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን መረዳትና ስረ መሰረቱ እስካልተፈታ ድረስ ደም አፋሳሽ ግጭቱ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሊነሳ እንደሚችል መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ኃይል
በግጭት ውስጥ ሁሉም ወገን በመገናኛ ብዙኃን ላይ የራሱን የበላይነት ለመያዝ ስለሚታትር ጋዜጠኞች የግጭት ወቅት ዘገባን እንዴት መምራት እንዳለባቸውና ለሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች እኩል ድምጽ መሆን እንደሚገባቸው እያጤኑ በጥንቃቄ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጋዜጠኞች እንደየሚሰሩበት የመገናኛ ብዙኃን የአርትኦት (ኤዲቶሪያል) ፖሊሲ የሚገዙ ቢሆንም በጋራ የሚያከብሯቸውና የሚመሩባቸው የሙያው አቅጣጫዎችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ጠንካራ የግጭት ዘገባ አቀራረብ የሚመራበት ሙያዊ ሰነድ አለመኖሩ የሚፈጥረው ጫና እንዳለ ሆኖ ግጭቱና ተፋላሚ ወገኖች በራሳቸው መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የግጭት ዘገባ ጋዜጠኝነት ሀላፊነት ለተሞላበት አዘጋገብ ወሳኝ የሆነው ሙያዊ ነጻነት በአብዛኛው ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡
በግጭት ዘገባ መፈጸም የሌለባቸው 7 ዋነኛ ተግባሮች
- የተለመዱና አሰልቺ ቃላትን መጠቀም– ስለግጭቱ መረጃ ለማግኘት ጓጉቶ ለሚጠብቀውም ሆነ ለዘገባው የተለየ እሴት የማይጨምሩ አሰልቺ አባባሎችን ማስወገድ፤
- ሁሉንም ማመን– በግጭት ውስጥ የዜና ምንጮች መረጃ የሚሰጡት ከየራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት አንፃር እየቃኙ ስለሆነ ጋዜጠኛ ሁሉንም ከማመን ይልቅ እያንዳንዱን በጥርጣሬ መመልከት ይገባዋል፡፡ “እናትህም ብትሆን የምትነግርህን እንዳለ መቀበል የለብህም” የሚለው ማሳሳቢያ ይበልጥ በዚህ ወቅት ይሰራል፡፡ ማጣራት ተገቢ ነው፡፡ ጠያቂ መሆንም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ለወራት በተካሄደ ጦርነት ውስጥ “ግማሽ ሚሊዮን ሰው ተገድሏል” የሚል መረጃ ቢኖር ጋዜጠኛው መቼ፣ የት፣ በማን፣ መረጃውስ በማንና እንዴት ተጠናቀረ የሚሉ የማጣሪያ ጥያቄዎችን በማንሳትና ሃቁን በማጣራት መዘገብ ይገባዋል፡፡
- ከአውዱ መውጣት– አንድ ጋዜጠኛ ስለአንድ ክስተት ሲዘግብ በክስተቱ መፈጠሪያ አካባቢ ነባር እውነታ ላይ ተመስርቶ መረጃውን ማቅረብ እንጂ ከክስተቱ ጋር ተዛማጅ ባልሆነ ባእድ አውድ ውስጥ በማስገባት መዘገብ የተሰሳተ ትርጓሜ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡
- የሰዎችን ስቃይ መርሳት– በግጭት ውስጥ ጾታዊ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር ዓይነት ወንጀሎች በስፋት እንደሚከሰቱ ማስታወስና ዘገባዎችን ሁሌም ሰዋዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡ አንድ ግጭት በሰዎች ላይ ያደረሳቸውን ስቃይ ማሳየት ለተጎጂዎች ድምጽ የመሆን ሚና የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ በአንድ ግጭት በቀጥታ ተሳታፊ ከሚሆኑ ሰዎች ሌላ ተጎጂዎች እንዳሉ ለማሳየት ያስችላል፡፡
- ቃላትን ያለጥንቃቄ መጠቀም– ቃል በራሱ ወደለየለት ግጭት እንደሚያስገባ ማሰብ፤ በግጭት ውስጥም ዘገባ ሲሰራ ለቋንቋ አጠቃቀም እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ “ዘር ማጥፋት” የሚለው ቃል የራሱ ትርጉምና መገለጫ ያለው በመሆኑ በግጭት ውስጥ በርካታ ሰው ስለሞተ ብቻ ዘር ማጥፋት ተፈጽሟል ከማለት መቆጠብ፡፡
- አጀንዳ ተቀባይ መሆን– በግጭት ዘገባ ስራ ላይ እያንዳንዷን ነገር ከጊዜ ጠቀሜታ ጋር በማሰብ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በሰዎች አጀንዳ አለመጠለፍ ይልቁንም እንደጋዜጠኛ በደራሽ ነገር እየተወሰዱ ከግጭቱ ጋር የተያያዙ ተከታታይ ዘገባዎችን ከማቅረብ ለሌሎች አጀንዳ የመስጠት አቅምን ማሳየት ይገባል፡፡ ይህም ጋዜጠኞች ግጭት ሲዘግቡ በሙያዊ ነጻነት መስራት እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው፡፡
- የአካባቢን ተፅዕኖ መዘንጋት– ጋዜጠኞች ግጭትን ሲዘግቡ የተለያየ ፍላጎት ካላቸው አካላት እስከግድያ የሚደርሱ አደጋዎች ሊጋረጡባቸው እንደሚችሉና ራሳቸውን ጭምር ሳንሱር እያደረጉ እንደሚሰሩ ማመን ይገባል፡፡ ይህን እውነት ተገንዝቦ ግን ደግሞ በእጅጉ ሚዛን ከሳተና ወገንተኝነቱ በግልፅ ከሚለይ አካሄድ መለስ ባለ ማዕቀፍ ውስጥ መስራት ይጠይቃል፡፡
ለመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች 4 ዋነኛ ምክረ ሐሳቦች
- የተግባቦት (መነጋገሪያ) መድረክ መሆን– በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች መገናኛ ብዙኃንን እኩል የመፈለግ ጽኑ ፍላጎት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በዚህ ወቅት ዘርፉ ለአንዱ ተፋላሚ ወገን ሳያደላ ሁለቱም እኩል ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መፍቀድ አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ከቻሉ እነሱ የጋዜጠኝነት ሥራቸውን ሲከውኑ እግረመንገዳቸውን ተፋላሚ ኃይሎችን ወደንግግር እያመጡና ግጭትን እያበረዱ ይሄዳሉ፡፡
- ማስተማር– ወደእርቅና ድርድር ለመምጣት ሁለቱ ወገኖች እርስበእርሳቸው እየተዋወቁ በተለይም ስለየግል ፍላጎታቸው እያወቁ መምጣት ይገባቸዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው የተፋላሚ ኃይሎችን የተናጠል ፍላጎት እና ስለ እርስ በእርሳቸው ያላቸውን የተዛባ አረዳድ እየጠየቁ ለተደራሲ ባበቁት ቁጥር ሕዝቡም ሆነ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች እየሰከኑና ወደ ሰላም የሚወስዳቸውን መንገድ እየመረጡ እንዲሄዱ አስቻይ ሁኔታ የመፈጠር እድል ይሰፋል፡፡
- መተማመንን መገንባት– አለመተማመን ዋነኛው የግጭት መንስኤ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን የየቡድኖችን እውነተኛ ስሜትና የስጋት ምንጮች አደባባይ ላይ ባወጡ ቁጥር ምስጢር የሚባለውና ላለመተማመን መነሻ የሚሆነው ጉዳይ እየታወቀ ወደ ግጭት የሚሄድ እድልም ይቀንሳል፡፡
- ስሜታቸውን እንዲገልጹ መፍቀድ– በተለይም ግጭትን (ቅራኔን) በእንጭጩ ወደ መፍታቱ ደረጃ ሲኬድ ሁለቱም ወገኖች የውስጥ ስሜታቸውን በመገናኛ ብዙኃን በኩል እንዲገልጹና ለበቀል የሚያነሳሳቸውን ጉዳይ ግልጽ እንዲያደርጉት ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ቅራኔን ጎዳና ላይ አውጥቶ ወደ ቀውስ እንዲያመራ ከማድረግ ይልቅ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ማድረግ ቢቻል ወደ ደም አፋሳሽነት ሳይቀየር መፍታት የሚቻልበት እድልም ይፈጠራል፡፡
ግጭትን መቀንበብ
ማንኛውም ዘገባ የተገኘውን መረጃ ሁሉ ማካተት ስለማይችል በሙያዊ መመዘኛና የዘገባው ባለቤት በሆነው ብዙሀን መገናኛ የአርትኦት ፖሊሲ መሰረት ከመረጃ ስብስቡ መካከል መርጦ ይዘግባል፡፡ መርጦ የማካተትና መርጦ የመተው ሂደትም የዜና ማዕቀፍ ይባላል፡፡ ማዕቀፍ ማለት የሚዘገበውን ሁነት ለማዋቀር ዘጋቢው የሚመለከትበት መስኮት ማለት ነው፡፡ መስኮት ከፊትለፊት ያለውን ነገር የሚያሳየው በማዕቀፉ ስፋትና ዘጋቢው ከሚገኝበት አንጻር ስለሆነ ሁሉንም አያሳይም፡፡
ግጭት የሚዘገብበት ማዕቀፍ (Frame) አንድም ዘጋቢዎችና አርታኢያን አንድን ግጭት ከተለያየና አማራጮችን ካካተተ ዕይታ መመልከትና መዘገብ ቢችሉ ውጥረትን ማርገብና ተቀናቃኝ ኃይሎችን ወደ ንግግር ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በግጭት ዘገባ ውስጥ ቂምና በቀል፣ ቁጣና ጥቃት ሊያስከትሉ የሚችሉ የጭካኔ ተግባራትንና የጥላቻ ንግግሮች ባለማካተትና ወደ መፍትሄ የሚወስዱ ጭብጦችን የማዕቀፉ አካል በማድረግ በኃላፊነት መዘገብ ይቻላል፡፡ ጦርነትን እንደ ጀብድና ስፖርታዊ ውድድር የሚያሳዩ ማዕቀፎች ኃላፊነት ከተሞላበት የግጭት አዘጋገብ ጋር ይጻረራሉ፡፡
በግጭት ውስጥ ከታጠቁ ኃይሎች ባሻገር ንጹሃን ሰዎችን የዘገባ አካል ማድረግ እውነቱን ለመረዳትና የግጭቱን ሁለንተና ተፅዕኖ ለማሳየት ስለሚያግዝ “ከራስ አጥር ወጥቶ ማሰብ” የሚለውን አባባል መተግበር ይገባል፡፡ ይህም ዘገባውን ሰዋዊ ህላዌ እንዲኖረው ማድረግ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን አጫጭር ዘገባዎች ከመስራት ባሻገር በጥልቅ ትንታኔ፣ ፕሮግራሞችና የመወያያ መድረኮችም ሽፋን እንዲያገኙና ለሰፊ ሀሳብ መንሸራሸር ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ማድረግ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ፈተናና እርምጃዎች
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብሔርና ሌሎች ማንነቶች ላይ መሰረት አድርገው በሚቋቋሙ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ለሁለቱም ቅራኔና ግጭት ውስጥ ላሉ አካላት እኩል ድምጽ መሆንና የመነጋገሪያ መድረክ ማበጀት ለጋዜጠኞች ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ይልቁንም ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን የራሳችን የማንነት ጎራ ነው በሚሉት ውስጥ ተወሽቀው የቀውሱ ዋነኛ አቀጣጣይ የመሆን አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ከመገናኛ ብዙኃን ባለቤትና አስተዳዳሪዎች፣ ከራሳቸው ከጋዜጠኞች፣ ከተፋላሚ ኃይሎች ፍላጎት፣ ውጭያዊ ጫናና አቅምም ጭምር ነው፡፡
በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር በይፋ በሚደረጉ ጦርነቶች ውስጥ ማንነትን መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች በመገናኛ ብዙኃን በኩል በተዛባ ሁኔታ እየተሳሉ ነው፡፡ የብሔር ማንነት ላይ የተደራጁት መገናኛ ብዙኃን እንደየፍላጎታቸው ግጭቶችን እየመረጡ ሲዘግቡ ሙሉውን ስዕል ከመስጠትም በመቆጠብ ነው፡፡ በአንፃሩ ‹‹የአጥቂውን›› ኃይል ጥፋት ለማሳየት የማይፈልጉ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሌላ ትርክት ይዘው ሲዘገቡ ይታያል፡፡
ይህ አካሄድ አገርና ሕዝብን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ቆም ብሎ ማጤንን (የመገናኛ ብዙኃንን የሚቆጣጠረው የመንግሥት ተቋምና የሕግ ማዕቀፎችን ጨምሮ) በዋናነት የመገናኛ ብዙኃንን ዋነኛ ሥራ አስቦ ”በቃ” የሚል የጋዜጠኛና የሙያ ማህበራት ጠንክሮ መውጣትን ይጠይቃል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ወይም ጋዜጠኞች ግጭትን ለመፍታት ከሚጠበቅባቸው አዎንታዊ ሙያዊ ሚና አንጻር ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ለሚያሳዩት ተቃርኖና መወቃቀስ እኩል ቦታ ሰጥቶ ገለልተኛና ትክክለኛውን ዘገባ መስራት የሚናቸውን ስኬት ይወስናል፡፡ ይህን ማድረግ ከቻሉ ሥራቸው ግጭትን ለማስወገድ የሚኖረው ድርሻ ሰፊ ይሆናል፡፡
ግጭት አነፍናፊና አበረታች ከመሆን ይልቅ በቅድመ ግጭት ደረጃ መገናኛ ብዙኃን ወደከፋ ግጭት ሊያመራ የሚችልን የተቀናቃኝ ኃይሎች ፍላጎት፣ የጋራ ጉዳይና በንግግር የመፈታት እድል በዘገባዎቻቸው ለሕዝብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በግጭት ወቅት ግጭቱ በሰዎች ምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ መግለጽ ይኖርባቸዋል፡፡ የሰላም መንገዶችን እንዲሁም በድኅረ ግጭት መገናኛ ብዙኃን ትኩረታቸውን የሰላም አማራጮች አተገባበር ላይ ማድረግ እና ግጭቱ ረግቧል ብሎ ነገሩን ከመርሳት ይልቅ ተከታታይና አዳዲስ አዳጊ ጉዳዮችንና መፍትሔያቸውን በወጥነት መዘገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለተጨማሪ ንባብ፡
- ሕዝቅያስ አሰፋ (2011)፤ የሰላምና እርቅ ትርጉምና መንገዶች፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እድገትና ከተፈጥሮ ጋር ባሉን ግንኙነቶች ላይ ያሏቸው አንድምታዎች፡፡ አዲስ አበባ፡፡
- International Media Support, Conflict sensitive journalism.
- Andrew Puddephatt, Voices of war: Conflict and the role of the media.
- International journalists’ network, Conflict reporting: Tips from local journalists in Africa.
- Friedrich Naumann Foundation for Freedom, Introduction to conflict-sensitive reporting.
- Mulatu Alemayehu Moges, Why Silence? Reporting Internal Conflict in Ethiopian Newspapers.
Comments