ማህበረሰብ ተኮር መገናኛ ብዙሀን ፕሮፋይል

የጅማ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ሬድዮ

ማህበረሰብ ተኮር መገናኛ ብዙሀን ፕሮፋይል / MIRH/ 10 ነሀሴ 2014

በብርሃኑ ቸኮል

የጅማ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ኤፍ. ኤም 102.0 ለጅማና አካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ነው፡፡ ሬድዮ ጣቢያው ግንቦት 4 ቀን 2000 ዓ.ም. የሙከራ ስርጭቱን በኦሮምኛና አማርኛ ቋንቋዎች ጀመረ፡፡ በቀን ለአምስት ስዓት በሚሰራጨው የሙከራ መርሀግብር ውስጥ በአብዛኛው የተካተቱት በሁለቱ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሙዚቃዎች ነበሩ፡፡

ህዳር 10 ቀን 2001 ሬድዮ ጣቢያው በቀጥታ የ10 ሰዓት መደበኛ ስርጭት ጀምሮ መስከረም 23 ቀን 2002 በይፋ ተመረቀ፡፡ ጣቢያው የስርጭት ሰዓቱን በማራዘም ቀጥታ ሥርጭቱን  ከሰኞ እስከ አርብ በቀን ወደ 13 ሰዓት፤ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ወደ 15 ሰዓት አሳደገ፡፡

ሬድዮ ጣቢያው የዩኒቨርሰቲውን ማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት መርህ የሚከተል ከመሆኑም በላይ ዓላማውም ማህበረሰቡን ማገልገል ነው፡፡ ሬድዮ ጣቢያው የተቋቋመበት ሂደትም ማህበረሰቡን ያሳተፈ ነበር፡፡ በተለይም ከጥቅምት እስከ ጥር 2000 ዓ.ም. በጅማ ከተማ በተካሄደ የህዝብ ስብሰባ የማህበረሰብ ሬዲዮ ምንነትን የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ በጅማ ከተማ ውስጥ ያሉ የ13 ቀበሌዎች ነዋሪዎች ስብሰባ ተካሂዶ በማህበረሰብ ሬድዮ መርሆዎችና በሬድዮ ጣቢያው አሰራር ላይ ማህበረሰቡ ተወያይቷል፡፡

ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ የመንግስት ሠራተኞችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ መምህራንንና ልዩ ልዩ የሙያ ማህበረሰቦችን፣ የንግዱን ማህበረሰብና ሌሎችንም የሚወክሉ ሰዎች ከየቀበሌው ተመርጠው ተግባራዊ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በማህበረሰብ ሬድዮው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ ተካተዋል፡፡ አሳታፊ በሆነ አሰራር መሰረት የተደራጀው የጅማ ማህበረሰብ ሬድዮ የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. የህጋዊ ሰውነት የምስክር ወረቀት ከከተማው መስተዳድር ተቀበለ፡፡

በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚገኙ ከሌሎችም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ግንኙነቶች ተካሂደዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሚዲያ አክሽን ፋውንዴሽን የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ጋር የነበረው ትብብር ተጠቃሽ ነው፡፡ በመስከረም ወር 2000 ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ የመጡ አና ኦሌመርት እና ኒሌስ ቴንአቨር የተባሉ ሁለት ኔዘርሊዲዊያን የድርጅቱ ተወካዮች ድርሻም ከፍተኛ ነበር፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው ለ21 የጅማ ዞን ወረዳዎች እና አጎራባች ዞኖች በመረጃ ምንጭነት እያገለገለ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አጓራባች ዞኖችም በጣቢያው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ምንጭ፤

  • የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ዳይሬክተር
  • https://ju.edu.et/community-radio/

‹‹አሐዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ››

Previous article

ብርሃኑ ዘሪሁን፡ ጋዜጠኛና የስነ ጽሁፍ ሰው

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply