ይማሩ

የዜና ክፍላችን ፆታን ያማከለ እንዲሆን ምን እናድርግ? (አስር ምክሮች)

ይማሩ /MIRH/ 27 ጥር  2022 

በፎዮ የሚዲያ (Fojo-Media Institute) ስልጠና ተቋም የተዘጋጀ

በዘመናዊዉ የጋዜጠኝነት ዓለም ዉስጥ የሥርዓተ ጾታን ጉዳይ በቀዳሚነት ግምት ዉስጥ ማስገባት ቁልፍ የስነ-ምግባር ጉዳይ ሆኖ ይነሣል፡፡

በእዚህ ዓመት መጀመሪያ ከአምስት ሃገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች በአዉሮጳዊቷ ሞልዶቫ ዋና ከተማ ቺሲናዉ (Chisinau, Moldova) በፎዮ የሚዲያ ስልጠና ተቋም አማካኝነት በተዘጋጀው በሥርዓተ ጾታ እና የመገናኛ ብዙሃን አካታችነት ስልጠና ላይ ለመሳተፍ ተሰባስበዉ ነበር፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ዉስጥ አካታች የሆኑ የዜና ክፍሎችን ለመፍጠር የሚረዱ ዐስር ያኽል ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡

  1. መደበኛ የሆኑ የዉስጥ ግምገማ መርሃ ግብሮችን ማካሄድ፡፡ በዜና ክፍሉ ዉስጥ የሚገኙ ጅምላ ፍረጃዎች ካሉ መፈተሽ፡፡ እንዲሁም የዜና ክፍሉ አወቃቀር የፆታም ሆነ ሌሎች የብዝሃነት መልኮችን ያካተተ መሆኑን፤ በተጨማሪም የተዘነጉ ወይም ግምት ዉስጥ ያልገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ይኖሩ እንደሆነ መገምገም ያስፈልጋል፡፡
  2. በባለሙያነትም ሆነ በሌላ ምክንያት እንደምንጭነት የምንጠቀማቸዉን ሰዎች የፆታ ስብጥር ማጤን፡፡ በምንዘግባቸዉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃ የሚሰጡን ሰዎች በበቂ ሁኔታ ፆታዊ ስብጥር  ይታይባቸዉ እንደሆነ መፈተሸ እና በመረጃም ሆነ በምንጭ ቋታችን ዉስጥ ብዝሃነት እንዲኖር አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይገባል፡፡
  3. የሰዎች የማንነት መገለጫዎች መልከ-ብዙ እና ተደራራቢ እንደሆኑ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ሰዉ በአንድ ጊዜ በርካታ የማንነት መገለጫዎችን ይዞ ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህም አንድ ሰዉ በአንድ ጊዜ ይዟቸዉ የሚገኙ የፆታ፣ እድሜ፣ ዜግነት፣ ብሔር፣ ሙያ፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ማለት ነዉ፡፡ በመሆኑም ፆታን ብቻ እንደብዝሃነት መገለጫ መዉሰዱ ተገቢ አይደለም፡፡ ከላይ በምሳሌነት የተቀመጡት የማንነት መገለጫዎች እንደአስፈላጊነቱ በማጣመር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የእድሜን ጉዳይ የሚያስቀድሙ ዘገባዎች ላይ በፆታ የተለዩ ዳሰሳዎች ማድረግ እና በሥራ ጉዳይ ላይ በሚያተኩር ዘገባ ላይ ፆታን፣ እድሜን እና የሙያ ሁኔታን ግምት ዉስጥ በማስገባት አካታች የሆነ ዘገባ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡
  4. ተጋላጭ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዙሪያ ለሚሠሩ ዘገባዎች ልዩ ትኩረት መስጠት፡፡ የግለሰቦችን ስኬት እና አሸናፊነት ብቻ የሚተርኩ ዘገባዎች በጥረት ላይ ያሉ እና ማበረታታት የሚያስፈልጋቸዉን የኅብረተሰብ ክፍሎች ችላ ስለሚሉ የተለያየ ዓይነት አኗኗር ላላቸዉ እና በተለያየ ሁኔታዎች ዉስጥ ለሚገኙ ሰዎችም ሽፋን መስጠት ያስፈልጋል፡፡
  5. ጅምላ ፍረጃዎችን የሚመለከቱ እና በጠቅላላዉ እንደማኅበረሰብ ያለንን አመለካከት የሚፈትሹ እና ጥያቄ የሚያነሱ ዘገባዎችን ማዘጋጀት፡፡
  6. የፆተኝነት፣ መድሎ፣ እና የአግላይነት ባህሪ ያላቸዉ አዘጋገቦችን መለየት እና በሥራ ክፍሉ የሚዘጋጁ ዘገባዎችንም ሆነ ማስታወቂያዎችን በእነዚህ መገለጫዎች መነሻነት መገምገም፡፡ ሊወገዱ የሚገባቸዉን ቃላት እና ምስሎች ዝርዝር ማዘጋጀት እና ይህንኑም በኤዲቶሪያል ፖሊሲዉ ዉስጥ እዲካተት ማድረግ፡፡
  7. የአካታችነት መርሆች መከበራቸዉን የሚያረጋግጥ አንድ ባለሙያ መመደብ፡፡ እነዚህም ባለሙያዎች በየጊዜዉ አስፈላጊ ስልጠናዎችን መዉሰድ የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት፡፡
  8. ከዘገባ በኋላ በምናዘጋጃቸዉ ማህደሮች ዉስጥ የምንጮቻችንን ወይም የጽሑፍ ባለቤቶችን ፆታ መመዝገብ፡፡ ይህም በዘላቂነት የዜና ክፍላችንን አካታችነት እና የፆታ ስብጥር ለመገምገም ይጠቅማል፡፡
  9. በዜና ክፍሉ ጋዜጠኞች ዘንድ በዘገባ ጊዜ ወደአንድ ፆታ ብቻ የመሄድ አዝማሚያ ካለ መገምገም (ለምሳሌ ሴት ጋዜጠኞች ወደ ሴት ምንጮች የማድላት ወይም ወንድ ጋዜጠኞች ወደ ወንድ ምንጮች የማድላት አዝማሚያ)፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ጋዜጠኞች የተለመደ የልምድ አጠቃቀማቸዉን እንዲቀይሩ ማበረታታት፡፡
  10. በዜና ክፍሉ ዉስጥ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ ግልፅ ደንብ ማዉጣት እና በክፍሉ ዉስጥ የፆታዊ ጥቃት ችግሮች ያሉ እንደሆነ በጥንቃቄ ማጣራት፡፡ የዜና ክፍሉ ሠራተኞች የፆታ ጥቃት ቢደርስባቸዉ ያለመሳቀቅ ለክፍሉ ማሳወቅ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፡፡

 

ምንጭ:

https://fojo.se/10-very-practical-ideas-for-newsrooms-that-want-to-be-more-gender-sensitive-and-inclusive

የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት ሰጪ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት

Previous article

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ማኅበራት እነማን ናቸው?

Next article

You may also like

Comments

Comments are closed.