የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC)

የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/ 04 ሀምሌ 2014

በመቅደስ ደምስ

የ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቴሌቪዥን እንደ አዲስ የብዙሀን መገናኛ ቴክኖሎጂ በመስፋፋት ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘበት ወቅት ነበር፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ትሆን ዘንድ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በአገሪቱ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወደ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ቴሌቪዥን ለማቋቋም ጠይቀው ፍቃድ ተከልክለዋል፡፡ በኋላም ፊሊፕስ ኢትዮጵያና ቶምሶን ቴሌቪዥን ኢንተርናሽናል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለማቋቋም እቅድ አቀረቡ፡፡ እቅዱ መሣሪያዎችን ማቅረብና የሰው ኃይል ማሰልጠንን ያካተተ ሲሆን የ247 ሺህ ብር ዓመታዊ በጀት የሚጠይቅ ነበር። ከብዙ ደብዳቤዎች መጻጻፍ በኋላ ሐምሌ 29 ቀን 1956 ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እቅዱ ቀርቦ ይሁኝታ አገኘ፡፡

በወቅቱ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የነበረው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንጻ አራተኛ ፎቅ የቴሌቪዥን ጣቢያው የመቋቋሚያ ሥፍራ እንዲሆን ተወሰነ። በመስከረም ወር 1957 ብሔራዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት እንደሚጀመር መንግስት በይፋ አስታወቀ። ፍቃድ ባገኘ በሦስተኛ ወሩ ጥቅምት 23 ቀን 1957 በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዘውድ በዓል ምሽት ላይ የቴሌቪዥን አገልግሎቱ በንጉሠ ነገሥቱ ተመርቆ በይፋ ሥራውን ጀመረ።

ሥዕል 1የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ 1950ዎቹ መጨረሻ

የቴሌቪዥን ጣቢያው ተመርቆ ሥራ ሲጀምር በአንድ ጠባብ ስቱዲዮ ውስጥ አምስት እንግሊዛውያንና 27 አትዮጵያውያን ሠራተኞች የነበሩ ቢሆኑም ቀስ በቀስ የውጭ አገራት ሠራተኞቹ እና ኃላፊዎች በኢትዮጵያውያን ተተክተዋል፡፡ በጊዜው 8ዐ በመቶ የአየር ሰዓቱ በውጭ አገር ፊልሞች የሚሸፈን ነበር። የአገር ውስጥ ዝግጅቶቹና ዜናው በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ብቻ የሚቀርቡ ሲሆን የሥርጭት ጊዜው በየቀኑ ከ4ዐ ደቂቃ ያልበለጠ ነበር። ፕሮግራሞቹ በሙሉ በቀጥታ ስርጭት ይተላለፉ ስለነበር ሥራው ለአቅራቢዎቹ ፈታኝ መሆኑ አልቀረም፡፡

እስከ 1963 ባሉት ዓመታት ባለ ጥቁርና ነጭ ቀለሙ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “እናንተው ፍረዱ”፣ “ህዝብና ጤናው”፣ “ጥያቄና መልስ”፣ “የሕጻናት ክፍለጊዜ” የተሰኙት ዝግጅቶቹ በተመልካቾች ተወዳጅ ነበሩ። ዘውዳዊው ሥርዓት በወታደራዊው ሥርዓት ከተተካ በኋላ በታህሳስ ወር 1969  የቴሌቪዥን ሥርጭቱ አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው ስቱዲዮ ኤርትራ ድረስ እንዲታይ ተደረገ።

ሥዕል 2የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባለ ጥቁርና ነጭ ቀለም ስርጭት

ከ1976 ጀምሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሥርጭት ሽፋን ከአዲስ አበባና ኤርትራ በተጨማሪ በጅማ፣ ባህርዳር፣ መቐለ፣ ጎንደር፣ ነቀምትና መቱ በተገነቡ ማሰራጫ ጣቢያዎች አማካኝነት ለከተሞቹ አገልግሎት መስጠት ቻለ። መስከረም 2 ቀን 1977 ከተከበረው 1ዐኛው ዓመት የደርግ ምስረታ በዓል ጀምሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባለቀለም ሆኖ ሥርጭቱን ቀጠለ።

ከ1983 የመንግስት ለውጥ በኋላ ቀደም ሲል ያልነበሩት የትግርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎችን ጨምሮ በርከት ባሉ ቋንቋዎች የተለያዩ የመዝናኛና ልዩ የበዓል ዝግጅቶችን ማቅረብ ጀመረ፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ‹‹120››፣ በትግርኛ ‹‹ቀዳም ምሳና››፣ በኦሮምኛ ‹‹ዳንጋ›› የተሰኙ የመዝናኛ ዝግጅቶች መቅረብ ጀመሩ። “ህብረ ትርኢት” አንዱ የቴሌቪዥን ጣቢያው ተወዳጅ ዝግጅት ነበር፡፡

የቴሌቪዥን አገልግሎቱ እስከ 1990 በአንድ ቻናል ብቻ ሲሰራ ቆይቶ ሁለተኛ ቻናል ኢቲቪ 2 ተከፈተ። በኋላም በመዝናኛው ኢንዱስትሪ የተሰማሩ የተለያዩ ድርጅቶች ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር አብረው ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እና የነበረው የአየር ሰዓት አለመጣጣም ለሦስተኛው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቻናል ኢቲቪ 3 መከፈት ምክንያት ሆነ፡፡ ይህም የሆነው ሐምሌ 01 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ጣቢያዎቹ በአሁኑ ጊዜ “ኢቲቪ ዜና”፣ “ኢቲቪ መዝናኛ” እና “ኢቲቪ ቋንቋዎች” በሚል ይታወቃሉ፡፡

በኋላም የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሚል እንዲተካ ተደረገ፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ ይሰራጭ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን) የዝግጅት አድማሱን በማስፋት በሳተላይትና ዘመኑ ባመጣቸው የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት በመላው ዓለም ላሉ ተመልካቾቹ ዝግጅቶቹን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት (93.2)

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ታሪክ ከጋዜጦች ቀጥሎ የሬዲዮ ዘርፍ ሁለተኛውና ትልቁ የብዙሀን መገናኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቴሌቭዥን ሥርጭት ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ሬዲዮ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ አሁን ካሉት ሦስት የሬዲዮ ጣቢያዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ከቀዳሚዎቹ የሬዲዮ ጣቢያዎች የሚመደብ እድሜ ጠገብ ተቋም ነው፡፡ ሐምሌ 14 ቀን 1923 የመሰረት ድንጋዩ ተጥሎ፤ መስከረም 2 ቀን 1928 በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር በይፋ ሥራውን ጀመረ፡፡

ሆኖም ከስምንት ወራት ስርጭት በኋላ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ምክንያት የሬዲዮ ጣቢያው ከነበረበት ንፋስ ስልክ ተነስቶ ወደ አሁኑ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ተዛውሮ የወራሪው ኃይል መገልገያ ሆነ፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ የሬዲዮ ጣቢያውን ጉዳት አድርሶበት ቢሄድም የእንግሊዝ ጦር መልሶ ገንብቶት ሥርጭቱ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን በመጠቀም የአገሪቱ ማህበራዊ፣ ምጣኔሀብታዊና ፖለቲካዊ እድገትን የሚደግፉ በርካታ ዝግጅቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የሥርጭት ሰአቱ ወደ 19 ሰዓት ከፍ እንዲል በተደረገበት በ1961 ዓ.ም. ጣቢያው በአማርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛና አረብኛ ቋንቋዎች ይጠቀም ነበር፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው ከአዲስ አበባ ዋና ማሰራጫው በተጨማሪ በአስመራ፣ ሐረርና መቱ የማሰራጫ ጣቢያዎች ነበሩት፡፡

ከፒያሳ ስቱዲዮው ወደ ብስራተ ወንጌል የሬዲዮ ጣቢያ ከተዘዋወረ በኋላ በ2001 ዓ.ም ወደ አሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና መስሪያ ቤት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው ለሀገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ እድገት በርካታ አስተዋኦ ያበረከተና በብዙ ኢትጵያውያን ልብ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ላሉ ዜጎች ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ አሁን ላይ በስምንት የሀገር ውስጥና በሶስት አለም አቀፍ ቋንቋዎች ዝግጅቶቹን ለአድማጮቹ ያደርሳል፡፡ አማርኛ፣ ሀረሪ፣ አፋር፣ ትግርኛ፣ አኝዋክ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ እና ንዌር ከሀገር ውስጥ የሚጠቀማቸው ቋንቋዎች ሲሆኑ፤ እንግሊዘኛ፣ አረብኛና ፈረንሳይኛ ደግሞ አለም አቀፍ ቋንቋዎቹ ናቸው፡፡

ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1

ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኤፍ ኤም ጣቢያ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ ለኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ መመስረት ሀሳብ አመንጪ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለሥራ ጉብኝት ከተጓዘበት ጀርመን ስለኤፍ. ኤም. ጣቢያዎች ያገኘው መረጃ በኢትዮጵያ የኤፍ. ኤም. ጣቢያ ቢቋቋምስ ለሚል ሀሳብ መነሻ ሆኗል፡፡ ሀሳቡም ተቀባይነት አግኝቶ ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 ተቋቋመ፡፡ ጣቢያው ሰባት ጋዜጠኞችን ከኢትዮጵያ ራዲዮ በማዘዋወር ነበር ሥራውን የጀመረው፡፡

የኤፍ. ኤም. ሬድዮ ስርጭት ሲጀምር የአየር ሰዓቱ ሽፋን ለ18 ሰዓታት የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ 2000 አዲስ ዓመት በሚከበርበት ወቅት ሥርጭቱ ወደ 24 ሰዓት ከፍ አለ፡፡ ይህ የሬዲዮ ጣቢያ የ24 ሰዓታት ስርጭት በማስተላለፍ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ነው፡፡ ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 ለአዲስ አበባና በዙሪያዋ እስከ 120 ኪሎ ሜትር ባሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ አድማጮች ዝግጅቶቹን ያደርሳል፡፡ የጣቢያው ልዩ ልዩ የሙዚቃ፣ የስፖርትና የመዝናኛ ዝግጅቶች በአድማጮች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ችለዋል፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ የማስተላለፊያ ዘዴዎች በመላ አገሪቱና፤ በሳተላይት አማካኝነት ደግሞ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እና ሌሎች አገራት ስርጭቱን በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡

ኤፍ. ኤም. 104.2

ኤፍ. ኤም. 104.2 ሦስተኛው የኢትዮጵያ ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን የሬዲዮ ጣቢያ ሲሆን እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛና አረብኛ ቋንቋዎችን በመጠቀም ለ18 ሰዓታት ዜናና የተለያዩ ዝግጅቶችን ለአድማጮች ያቀርባል፡፡ በአዲስ አበባ ያለውን የውጭ ዲፕሎማት ማህበረሰብ፣ የውጭ ኢንቨስተርና ለተለያዩ ጉዳዮች አዲስ አበባ የሚቆዩ የውጭ ዜጎችን ለመድረስ ያለመ የሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ በ2007 አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኤፍ. ኤም. 104.2 አሁን ላይ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ዜናና ልዩ ልዩ ዝግጅቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የሬዲዮ፣ የቴሌቭዥን ሥርጭት ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (EBC) በማኅበራዊ፣ በምጣኔሀብታዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ ሁለገብ መረጃና መዝናኛ በማቅረብ አንጋፋ እድሜ ያለው የመገናኛ ብዙሀን ተቋም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ 4 መቶ በላይ ሠራተኞች በአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ አሉት፡፡

 

ምንጮቻችን፡-

  • “ሬዲዮ ትናንትና ዛሬ” መጽሄት (የካቲት 2013) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን
  • የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አምሳኛ ዓመት የምስረታ በዓል መጽሄት
  • Meseret Chekole. (2013). The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia. University Press of America.
  • https://en.unesco.org/events/celebrating-radio-diversity-world-radio-day-2020-ethiopia

እና ሌሎች ጥናቶች

 

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)

Previous article

ድሬ ቲዩብ (DireTube.com)

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply