የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች መዝገብ /MIRH/ 9 መስከረም 2015
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤት በ1989 ዓ.ም በምኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 19/1997 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጅማ በር በሚገኘው በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ግቢ ተመሠረተ፡፡
በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ለዘመናት የጋዜጠኝት ትምህርት የሚሰጥበት በኢትዮጵያ ብቸኛው ተቋም ነበር፡፡
በቀጣዩ አመት ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ በሚገኘው የቀድሞ የጣሊያን የፕሮፖጋንዳ ማሰራጫ ጣቢያ፣ ቀጥሎም የማስታወቂያ ሚኒስቴር እና ኢትዮጵያ ሬዲዮ መስሪያ ቤት ሆኖ ባገለገለው ታሪካዊ ስፍራ ላይ ጋዜጠኞችን በሰርተፊኬትና ዲፕሎማ ደረጃ እስከ 1995 ዓ.ም ሲያሰለጥን ቆየ፡፡ ከእዛም በ1996 ዓ.ም በብሮድካስት ጋዜጠኝነት እንዲሁም በህትመት ጋዜጠኝነት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ (BA) ፕሮግራም በይፋ ከፈተ፡፡
በ1997ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከኖርዌይ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነትና ድጋፍ በብሮድካስት ጋዜጠኝነት ንዑስ ዘርፍ እና በህትመት ጋዜጠኝነት ንዑስ ዘርፍ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ማስተማር ጀመረ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤት የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች ላይ ክለሳ በማድረግ ከፕሮግራሞች ስያሜ እስከ በርካታ የኮርስ፣ ይዘት እና የክሬዲት አወር ለውጦችን አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ‹‹ፕሪንት እና ኦንላይን ጋዜጠኝነት›› የነበረው የት/ት ፕሮግራም ‹‹የመልቲ ሚዲያ ጋዜጠኝነት›› ሆኗል፡፡ እንዲሁም ‹‹የህዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ›› የነበረው ወደ ‹‹የህዝብ ግንኙነት እና ስታራቴጅክ ኮሚዩኒኬሽን›› ተቀይሯል፡፡ ‹‹የብሮድካስት ሚዲያ ጋዜጠኝነት›› ፕሮግራም ቀድሞ በነበረበት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
በዚህም መሠረት ት/ት ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ በቀንና በማታ እያስተማረ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በ2009 ዓ.ም በትምርት ቤቱ መሰጠት በጀመረው ሚዲያና ኪሙኒኬሽን ጥናት ዘርፍ በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል፡፡
ከተመሠረተ ሃያ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤት፤ አሁን ላይ በታሪካዊው የአቡነ ጴጥሮስ ካምፓስ ደረጃውን የጠበቀ የሚዲያ ማዕከል የሆነ ህንፃ እያስገነባ ይገኛል፡፡ ህንፃው ሲጠናቀቅ ት/ቤቱ አሁን ከሚገኝበት የስድስት ኪሎ ጊቢ ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ ወደዚሁ ስፍራ የሚመለስ ይሆናል፡፡ ማእከሉ የኢትዮጵያን የሚዲያ ታሪክ ያደራጀ ሙዚየም የሚኖረው ሲሆን፤ የተሻለ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የህብረተሰብ አገልግሎት ማዕከል ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤት በአጠቃላይ በሁሉም ፕሮግራሞችና መርሀ ግብሮች ወደ 600 የሚጠጉ ተማሪዎች ያሉት ሲሆን፤ 36 የአካዳሚክስና 20 የአስተዳደር፤ በአጠቃላይ 56 ሠራተኞችን ይዟል፡፡
ምንጭ፡- ትምህርት ቤቱ 25ኛ አመቱን ሲያከብር ያሳተመው በራሪ መጣጥፍ
Comments