የግል መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በኢትዮጵያ Voice of America (VOA)

በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሚዲያ/ MIRH/16 ሰኔ 2015

በሳሙኤል አሰፋ

የአሜሪ ድምጽ ራዲዮ በ1934 ዓ.ም እ.ኤ.አ በ1942 የናዚን ፕሮፓጋንዳ ለመዋጋት ትክክለኛ እና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ማሰራጨት በሚል ተጀመረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቪኦኤ (VOA) ወጥነት ያለው የእውነት፣ የተስፋ እና የመነሳሳት መልእክት በማስተላለፍ ዓለምን አገልግሏል። ቪኦኤ በአርባ አምስት ቋንቋዎች ሥርጭት ያለው ሲሆን በዓለም እጅግ ግዙፍ ባለብዙ ሚድያ የዜና አውታር ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ አካል የሆነው ቪኦኤ ሙሉ በጀቱ የሚሸፈነው በአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች መሆኑን በድረ ገጹ ላይ ተመላክቷል:: ከ326 ሚሊዮን በላይ የሚገመተውን ሳምንታዊ ዓለም አቀፍ ተመልካቾችን በማገልገል ላይ የሚገኘው ቪኦኤ፤ በድረ ገጽ እና በማህበራዊ ሚዲያ፣ በራዲዮ እና በቴሌቭዥን አማካኝነት ዜና፣ መረጃ እና የባህል ፕሮግራሞችን ያቀርባል።

ቪኦኤ በአፍሪካ ቀንድ አገራት በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኤርትራ የራዲዮ ሥርጭቶችን ያስተላልፋል፡፡ የአማርኛ ፕሮግራም የሚሠራጨው ከአንድ መቶ ሚሊየን በላይ የሚሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ ለሚኖር ሕዝብና እንዲሁም በመላው ዓለም ለሚገኙ የቋንቋው ተናጋሪዎች ነው፡፡ አፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ኦሮሚያ ውስጥ ለሚኖሩ ከአጠቃላዩ የሕዝብ ቁጥር 37 ከመቶ የሚሆነውን ለሚሸፍኑ ኢትዮጵያዊያን ሲሆን ትግርኛ ፕሮግራም ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ ይደመጣል፡፡ የቪኦኤ አድማጮች ዝግጅቶችን በራዲዮ አጭርና መካከለኛ የአየር ሞገዶችና በሳተላይት ቴሌቪዥን እንዲሁም በዲጂታል መልክ እየተዘጋጁ በእጅ ስልክና በኮምፕዩተር አማካኝነት ለአድማጭ ተመልካቾች በበይ መረብ ይቀርባሉ፡፡

የሥርጭት ይዘቶች ትኩረት ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ ባሉ ክንዋኔዎች፣ በአካባቢያዊ፣ በአህጉራዊ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ዜናዎች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በአሜሪካ ባሕሎች፣ ፖለቲካ፣ ወጎችና ልማዶች፣ መዋዕለ-ዜና፣ በምጣኔ ኃብት፣ በጤና፣ በትምህርት እና ሌሎችም ስፋት ያላቸው ጉዳዮች ላይ የሚሠናዱ የመረጃ እና የመዝናኛ ቅንብሮች እየተዘጋጁ ይተላለፋሉ፡፡

ጋለፕ የሚባለው ዓለምአቀፍ ቅኝቶችን የሚያካሂድ ተቋም በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም ያካሄደው ጥናት ውጤት እንዳሳየው የአሜሪካ ድምጽ ኢትዮጵያ ውስጥ በየሣምንቱ በሦስት ሚሊየን አዋቂዎች የሚደመጥ ግንባር ቀደም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ ከእነዚህ አድማጮች ውስጥ አርባ ከመቶ የሚሆኑት ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 24 የሆኑ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚሁ የጥናት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ከዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆነው የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) አድማጭ ጣቢያው የሚያስተላልፋቸውን መረጃዎች “የማይጠራጠሩት፤ የሚያምኑት፤” መሆኑን አሳይቷል፡፡ የወቅቱን ክንዋኔዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ ያስቻላቸው መሆኑንም እነዚሁ ጥናቱ ያካተታቸው አድማጮቹ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ተልዕኮና ኤዲቶሪያል ነፃነት የቪኦኤን ጋዜጠኞች ከተፅዕኖ፣ ከጫና ወይም በመንግሥት ባለሥልጣናትና በፖለቲከኞች ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት ወይም የበቀል ጥቃት በሚጠብቋቸው ሕግጋት የተረጋገጠ ነውም ይላል።

ተልዕኮ

የቪኦኤ ተልእኮ የተወሰደው በፕሬዚዳንት ጄራልድ አር ፎርድ እኤአ ጁላይ 12 ቀን 1976 በሕግ ከተፈረመው ከቪኦኤ ቻርተር ነው። ቻርተሩ የቪኦኤ ፕሮግራሞችን የአርትዖት ነፃነት እና ታማኝነትን ይጠብቃል።

የዩናይትድ ስቴትስ የረዥም ጊዜ ጥቅም የሚጠበቀው ከዓለም ሕዝቦች ጋር በሬዲዮ በቀጥታ በመነጋገር ነው። ውጤታማ ለመሆን የአሜሪካ ድምጽ የአድማጮችን ትኩረት እና ክብር ማግኘት አለበት። ስለዚህ እነዚህ መርሆዎች የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) ሥርጭቶችን የሚቆጣጠሩ ይሆናሉ፡-

  1. ቪኦኤ በቋሚነት ታማኝ እና እውነተኛ የዜና ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። የቪኦኤ ዜና ትክክለኛ፣ ተጨባጭ እና ሁሉን አቀፍ ይሆናል።
  2. ቪኦኤ የሚወክለው አሜሪካን እንጂ የትኛውንም የአሜሪካን ማህበረሰብ ክፍል አይደለም፣ ስለሆነም ሚዛናዊ እና አጠቃላይ የአሜሪካን ጉልህ ሀሳቦች እና ተቋማትን ሃሳብን ያቀርባል።
  3. ቪኦኤ የዩናይትድ ስቴትስን ፖሊሲዎች በግልፅ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ያቀርባል እንዲሁም በእነዚህ ፖሊሲዎች ላይ ኃላፊነት የተሞላበት ውይይት እና አስተያየት ያቀርባል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሬድዮ

Previous article

ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘጉ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን

Next article

You may also like

Comments

Comments are closed.