የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)

የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/ 04 ሀምሌ 2014

በመቅደስ ደምስ

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የቀድሞውን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ተክቶ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ ባሕል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ እንደ አንድ መምሪያ በ1986 ተቋቋመ፡፡ ድርጅቱ ታህሳስ 7 ቀን 1987 ሳምንታዊውን የበኩር ጋዜጣ የምስራች እትም በማውጣት ክልሉን ማእከል ያደረጉ ዜና ዘገባዎች እና ልዩ ልዩ የመረጃ ጥንቅሮችን ለሕዝብ ማድረስ ጀመረ፡፡

የበኩር ጋዜጣ የመጀመሪያዎቹ ዘጋቢያንና አርታዕያን ከኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተውጣጡ 13 ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ በኩር ጋዜጣ በክልል ደረጃ በመታተም የመጀመሪያው ጋዜጣ ነው፡፡ “በኩር” ማለት “የመጀመሪያ” አልያም “ቀዳሚ” ማለት ነው፡፡

ጋዜጣው በተለይ ስለአማራ ክልል ማኅበራዊ፣ ምጣኔሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ማወቅ ለሚሹ ዜጎች አንድ የመረጃ ምንጭ ሆነ፡፡ በወቅቱ ጋዜጣው በስምንት ገጾች በሳምንት አንድ ጊዜ በአራት ሺህ ቅጂዎች ይታተም ነበር፡፡ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የየህትመቱን ካሜራ-ዝግጁ ቅጂ በፖስታ ቤት ወደ አዲስ አበባ በመላክ ከታተመ በኋላ በአውቶብስ ተጓጉዞ ባህርዳር ይደርሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የበኩር ጋዜጣ ሳምንታዊ ኅትመቱ ከአራት ሺሕ ቅጂ ወደ ዘጠኝ ሺሕ ቅጂ አድጓል፡፡

አሁን ላይ የበኩር ጋዜጣ ህትመት እዛው ባህር ዳር ከተማ የሚከናወን ሲሆን፤ አሚኮ ከበኩር በተጨማሪ ሦስት በተለያዩ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጦች አሉት፡፡ የጋዜጦቹ ተደራሾች በክልሉ የሚገኙ የአዊኛ፣ አፋን ኦሮሞና ኸምጥኛ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ለክልሉ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች መረጃ ለማድረስ የሚዘጋጁት አራቱ ጋዜጦች ከጥቅምት 1 ቀን 2003 ጀምሮ በየ15 ቀኑ ይታተማሉ፡፡

አሚኮ ለክልሉ ማህበረሰብ ዜናና መረጃ በስፋትና በፍጥነት ለማዳረስ ባለው ዓላማ መሰረት ግንቦት 16 ቀን 1989 ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት የአየር ሰዓት በመከራየት “የአማራ ብሄራዊ ክልል ድምጽ” በሚል መጠሪያ የራሱን ሥርጭት ጀመረ፡፡ የዝግጅቱ ተደማጭነትም እየጨመረ በመምጣቱ የስርጭት ሰዓቱ ከአንድ ሰዓት ወደ ዘጠኝ ሰዓት አደገ፡፡ በመቀጠል መጋቢት 22 ቀን 1994 ኤፍ. ኤም. ባሕርዳር 96.9 በቀን የሁለት ሰዓት ስርጭቱን በመጀመር በኢትዮጵያ ከኤፍ ኤም 97.1 ቀጥሎ ሁለተኛው ኤፍ. ኤም. ሬድዮ ጣቢያ ሆነ፡፡

ኤፍ. ኤም. ባሕርዳር ቀስ በቀስ ስርጭቱን ወደ 24 ሰአታት አሳደገ፡፡ በክልሉ ከአማርኛ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚተላለፉ አማራ ኤፍ. ኤም. ደሴ 87.9፣ አማራ ኤፍ. ኤም. ደብረ ብርሃን 91.4፣ አማራ ኤፍ. ኤም. ጎንደር 105.1፣ አማራ ኤፍ. ኤም. ደብረ ማርቆስ 95.1፣ አማራ ኤፍ. ኤም. ደብረ ታቦር 90.0፣ አማራ ኤፍ. ኤም. አዲስ አበባ 103.5 ስርጭት ላይ የሚገኙ የራዲዮ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ የራዲዮ ጣቢያዎቹ አሁን ላይ በቀን የስድስት ሰዓታት አካባቢያዊ ስርጭት አላቸው፡፡ በቅብብሎሽ ዘዴም ወልድያና አካባቢው እንዲሁም ደብረ ማርቆስና አካባቢውን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

ከሬዲዮ በመቀጠል አሚኮ የቴሌቪዥን ስርጭትን ጀመረ፡፡ ሚያዝያ 19 ቀን 1992 ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት በመከራየት የተጀመረው የአማራ ቴሌቪዥን ስርጭት በሳምንት የሰላሳ ደቂቃ የአየር ሰአት ይሸፍን ነበር፡፡ በኋላም የስርጭት ሰአቱን ሲያሳድግ ቆይቶ በራሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ የ24 ሰዓታት ስርጭት በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ የአማራ ቴሌቪዥን አማርኛን ጨምሮ ከአሥር በላይ በሚሆኑ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ለተመልካቾቹ ዝግጅቶቹን ያደርሳል፡፡

አሚኮ የመገናኛ ብዙሀን ሥራውን በማስፋፋት ተጨማሪ አገልግሎት ህብር ቴሌቪዥን በሚል ስያሜ በሰኔ ወር 2014 ጀምሯል፡፡ ይህ ወደ ስርጭት የገባ የአሚኮ ሁለተኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ አሚኮ በመደበኛ መገናኛ ብዙሀን የሚገለግልባቸውን ሁሉንም ቋንቋዎች በህብር ቴሌቪዥን በመጠቀም መረጃ ያሰራጫል፡፡

ከ750 በላይ ሠራተኞች ያሉት አሚኮ፤ ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ነው፡፡ የአሚኮ ዋና መቀመጫ ባህር ዳር ሲሆን በክልሉ ልዩ ልዩ ቦታዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ የቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት፡፡ አሚኮ በ1986 የተቋቋመውን የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የተካው ከመጋቢት 3 ቀን 2013 ጀምሮ ነው፡፡

 

ምንጭ፡

ድረ ገጽ፡ https://www.amharaweb.com

ልዩ ልዩ ያልታተሙ ጽሑፎች

ስለ ሞባይል ጋዜጠኝነት ማወቅ ያለብን

Previous article

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC)

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply