ይማሩ

የቃለ መጠይቅ አስፈላጊ ዝግጅቶች እና ክንውኖች

ይማሩ / MIRH/ 14 ታህሳስ 2014

ጽሑፍ፡ ጃልዲፕ ካትዋላ (mediahelpingmedia )

ትርጉም፡ በ MIRH ቡድን

ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ ከማድረጋቸዉ በፊት እቅድ ማዉጣት እና በቂ ዝጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከቃለ መጠይቁ በፊት በጉዳዩ ላይ በቂ የመረጃ ማጣራት ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ጥያቄዎችን በምናዘጋጅበት ጊዜ ከተጠያቂዉ መልስ የምንፈልግላቸዉን ነገሮች በሦስት ጥያቄዎች መጠቅለል እንችል እንደሆነ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የቃለ መጠይቁን ርዕሰ ጉዳይ በበቂ ሁኔታ መያዛችንን የምናረጋግጠዉ የቃለ መጠይቁን ጥያቄዎች ወደ ሦስት መጠቅለል ስንችል ነዉ፡፡ በተግባር ቃለ መጠይቁን በምናካሂድበት ጊዜ  ተጠያቂዉ የሚናገሩትን በሙሉ ትኩረት ማዳመጥ እና ማስታወሻ በመያዝ ወይም በመሰል ጉዳዮች በመጠመድ ሃሳባችንን ተጠያቂዎች ከሚናገሩት ዝርዝር ማራቅ የለብንም፡፡

በቃለመጠይቅ ዝግጅት እና ሂደት ወቅት ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ጠቃሚ ምክሮች፡፡ 

 1. ከቃለ መጠይዉ በፊት ለተጠያቂዎች ጥያቄዎችን አለመስጠት፡፡ ምንም እንኳን ከተጠያቂዎች ጋር በቃለ መጠይቁ ጠቅላላ ጭብጥ ዙሪያ መወያየት ክፋት ባይኖረዉም ቀድሞ ዝርዝር ጥያቄዎችን መስጠት ተጠያቂዉ በልምምድ ላይ የተመረኮዘ መልሶችን እንዲሰጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ 
 2. በቃለመጠይቁ ወቅት የቀጠሮ ሠዓት አክብሮ መገኘት እጅግ አስፈላጊ ነዉ፡፡
 3. ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ከመሄዳችን በፊት መቅረፀ ድምፅ እና ሎሎች መሣሪያዎች በሚገባ መሥራታቸዉን እና በቂ የኃይል (ባትሪ) አቅም እንዳላቸዉ ማረጋገጥ፡፡
 4. ተጠያቂዎቻችን ምንም ዓይነት የሥራ ሁኔታ፣ ስልጣን ወይም ፆታ ቢኖራቸዉም በትኅትና እና በክብር ማነጋገር፡፡ ያልተጋነነ እና ትኅትና ያለዉ ሰላምታ በመስጠት መጀመር፡፡ 
 5. ቃለ መጠይቁ የሚካሄድበትን ቦታ ምቹ ማድረግ እና በአካባቢው የሚረብሹ ድምፆች ካሉ ምንም ዓይነት ድምፅ ረብሻ የሌለበት ቦታ መምረጥ፡፡ በዋናነት ቃለ መጠይቁ በጋዜጠኞች ቅጥጥር ሥር መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ 
 6. የቃለ መጠይቁን ሂደት እና አጠቃላይ ድባብ መቆጣጠር የጋዜጠኞች ድርሻ ቢሆንም የቃለ መጠይቁን ትኩረት ግን በጋዜጠኛዉ/ዋ ላይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ወቅት ትኩረት ማድረግ አለባቸው ሲባል ጠቃሚ መረጃ እና አሳቦችን ለመሰብሰብ እንጂ የራሳቸዉን አሳብ ለማንፀባረቅ መሆን የለበትም፡፡
 7. በቃለ መጠይቅ ዝግጅት ሂደት ቅድመ ማጣራት እና ተያያዥ መረጃዎችን መሰብሰብ አስፈላጊ ቢሆንም በአንድ ጥያቄ ዉስጥ ኹሉንም ጉዳዮች ለማካተት መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡ በአድማጭ/ተመልካች/አንባቢ ቦታ በመሆን እነርሱ ሊያዉቁ የሚፈልጓቸዉን ነገሮች በቅደም ተከተል ማስቀመጥ እና መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ 
 8. ዋና ዋና ጥያቄዎችን አስቀድሞ መጠየቅ፡፡ ቃለ መጠይቁ በገፋ እና ከበድ ያሉ ጥያቄዎች በቀረቡ ቁጥር ተጠያቂዎች መልሳቸዉን የማሳጠር፣ ብሎም ቃለ መጠይቁን የማቋረጥ አዝማሚያ ሊያሳዩ ስለሚችሉ ለዋና ዋና ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ 
 9. የቃለ መጠይቅ ዓላማ የአሳብ ምልልስ ማድረግ እንጂ ተጠያቂዉን ማሳጣት እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
 10. በተቻለ መጠን የማስታወሻ ደብተርን አለመመልከት፡፡ በተደጋጋሚ ማስታወሻ ደብተርን መመልከት በተጠያቂዎች ዘንድ ትኩረት ማጣት እና በጋዜጠኞች ዘንድ የአሳብ መከፈልን ሊፈጥር ይችላል፡፡
 11. ከተጠያቂዎች ጋር ተገቢ የሆነ ዓይንለዓይን ግንኙነት ማድረግ እና የሰዉነት እንቅስቃሴያችንን መመጠን ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በተደጋጋሚ ጭንቅላታችንን የምንነቀንቅ ከሆነ ተጠያቂዉ/ዋ በአሳባቸዉ እንደተስማማን በመገመት አሳባቸዉን ከማብራራት ሊቆጠቡ ስለሚችሉ እና እኛም በቂ መረጃ ላናገኝ እንችላለን፡፡ በተቃራኒዉ ጭንቅላታችንን በተቃርኖ ስንነቀንቅ ወይም ፊታችን ላይ ድንጋጤ መሰል ኹነት የሚያነቡ ተጠያቂዎች አሳባቸዉን በነፃነት ከማብራራት ሊቆጠቡ እንደሚችሉ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
 12. በተቻለ መጠን ጥያቄዎቻችንን ወደ ሦስት ወይም ዐራት ጥያቄዎች ለመገደብ መሞከር፡፡ በእነዚህ ጥቂት ጥያቄዎች ከተጠያቂዉ/ዋ ምንፈልገዉን አሳብ ማግኘት ካልቻልን ጥያቄዎቻችንን መቀየር ይኖርብናል፡፡ 
 13. ምን፣ ማን፣ ለምን፣ የት፣ መቼ፣ እና እንዴት በሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሽፋን ለመስጠት መሞከር፡፡
 14. ጥያቄዎችን ከማርዘም ይልቅ ማሳጠር ይመረጣል፡፡ በተለይም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ጥያቄዎችን ደራርቦ መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ማድረጉ ተጠያቂዉ/ዋ ተደርበዉ የተጠየቁ ጥያቄዎችን ሳይመልሱ እንዲያልፉ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ 
 15. ቃለ መጠይቅ በምናደርግበት ወቅት የምንጠቅሳቸዉ እዉነታዎች/ማስረጃዎች የተረጋገጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በተለይም በቀጥታ ሥርጭት ጊዜ የተሳሳተ መረጃ ይዘን ስንጠቅስ መገኘት እና በተጠያቂዉ መታረም አይኖርብንም፡፡ 
 16. አንዳንድ ጊዜ ተጠያቂዎች እኛ ከጠበቅነዉ በላይ አዳዲስ መረጃዎች ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ተጠያቂዎች በሚናገሩበት ጊዜ ሁሉ በጥንቃቄ ማዳመጥ ይገባል፡፡ 
 17. ተጠያቂዎች ለአንድ ጥያቄ መልስ ከሰጡ በኋላ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን (ለምሳሌ ቁጥር) የተመለከቱ እርማቶች ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር የተናገሩትን አሳብ ለመቀየር ሲሉ በድጋሚ መልስ ለመስጠት እንዲችሉ መፍቀድ አይገባም፡፡

አእምሮ ጋዜጣ

Previous article

አካታች እና ፆታን ታሳቢ ያደረገ የዜና ክፍል እንዴት እንፍጠር? 

Next article

You may also like

Comments

Comments are closed.