የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 9 መስከረም 2015
በመቅደስ ደምስ
የ1966ቱን የኢትዮጵያ አብዮት ተከትሎ በርካቶች ታስረዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ተሰደዋል፣ እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ይህ እጣ ፈንታ ከደረሳቸው እውቅ ሰዎች መካከል ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲዋ የሸዋሉል መንግስቱ አንዷ ነች፡፡
የሸዋሉል የተወለደችው ምስራቅ ሐረርጌ፣ ኤጀርሳ ጎሮ በ1937 ነው፡፡ ለእናቷ ብቸኛ ልጅ ስትሆን በአባቷ በኩል ታላላቅና ታናናሽ ወንድምና እህቶች አሏት፡፡ ለእናቷ አንድ የሆነችው የሸዋሉል እናቷ ልጅ መውለድ ተስኗቸው ቆይቶ በ46 አመታቸው ያገኟት ብርቅዬ ልጃቸው ነበረች፡፡

ምስል አንድ፡- የሸዋሉል መንግስቱ
የሸዋሉል ደፋር፣ ያሰበችውን ከማድረግ ወደኋላ የማትል ብሩህ አእምሮ የነበራት ሴት ነበረች፡፡ ገና በልጅነቷ ግጥም ጽፋ ህዝብ በተሰበሰበበት የማንበብ ተሞክሮ ነበራት፡፡ የሸዋሉል የትውልድ አካባቢዋ ኤጀርሳ ጎሮ፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የትውልድ ቦታ ስለነበር በአንድ ወቅት እሳቸው ለጉብኝት በአካባቢው በተገኙበት ግጥም የማንበብ እድል አግኝታ ከንጉሡ 50 ብር ተሸልማለች፡፡
በትምህርቷ ግን አልገፋችም፡፡ በ13 ዓመቷ ተድራ ከትውልድ አካባቢዋ ወደ ሐረር ሄደች፡፡ የፖሊስ ሠራዊት አባል ከሆነው የመቶ አለቃ ባለቤቷ አምስት ልጆችን አፈራች፡፡ ሆኖም በትዳር ታስራ የቤት እመቤት ሆና መቅረት አልመረጠችም፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ቲያትር፣ አጭር ልቦለድና ኢ-ልቦለድ ጽሁፎችን እየጻፈች ሐረር ለሚገኘው ሬዲዮ ጣቢያና ለፖሊስ ሰራዊት ጋዜጣ መላክ ጀመረች፡፡ ብዙ ጊዜ ጽሁፎቿ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ፡፡ ቆይቶ ስለሴቶች መብትና ነጻነት የሚሞግቱ እና ሴቶችን ስለኑሮና ህይወት የሚመክሩ ጽሁፎችን ማሰናዳት ጀመረች፡፡ ስለሴቶች ጉዳይ አብዝታ የምትጨነቀው የሸዋሉል ለሴቶች መብትና ነጻነት የሚታገል የሴቶች ማህበር አባል ነበረች፡፡
ይህም የጽሁፍ ተሞክሮ የሸዋሉል ወደ ጋዜጠኝነት የተጓዘችበት መንገድ ነበር፡፡ አብዛኛውን የጋዜጠኝነት ህይወቷን ያሳለፈችው በሐረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል በየሁለት ወሩ ይታተም በነበረው ‹‹የምስራቅ በረኛ›› መጽሄትን በመዘጋጀት ነበር፡፡ ለሐረር ምስራቅ በረኛ ኦርኬስትራም በርካታ ግጥሞችን፣ ዜማዎችን፣ ቴአትሮችንና ዝማሬዎችን አበርክታለች፡፡ ጎን ለጎን ለኢትዮጵያ ሬዲዮ የሐረር ቅርንጫፍ ተባባሪ አዘጋጅ ሆናም ሰርታለች፡፡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣም ጽሁፎችን ትልክ ነበር፡፡
በግጥምና ዜማ ደራሲነቷ የሸዋሉል ተወዳጅ የሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎች ባለቤት ናት፡፡ ለትውልድ መንደሯ ግጥም ገጥማለች፡፡ ለወንድ ድምጻዊያን በሰጠቻቸው የዘፈን ግጥሞች ‹‹ወንዶችን ለሴቶች የፍቅር ዘፈን የምታዘፍን›› ተብላለች፡፡ በጥላሁን ገሰሰ፣ አሊ ቢራ፣ መሀሙድ አህመድ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ሙሉቀን መለሰና ሌሎች እውቅ ዘፋኞች ስራ ውስጥ የግጥምና ዜማ ውጤቶቿ ገዝፈው ይታያሉ፡፡ የሸዋሉል የባህል ስራዎችን በዘመናዊ ግጥምና ዜማ አድሳ በማቅረብ በሙዚቃ አፍቃሪው ዘንድ ተወዳጅ ነበረች፡፡
በ1964 የ27 ዓመት ወጣት እያለች ‹‹ሙዚቃ በሐረር›› በሚል ርዕስ የሙዚቀኞች ታሪክ የተካተተበት መጽሄት አዘጋጅታለች፡፡ በእዚህ መጽሄት እንደ ተስፋዬ ለሜሳ፣ መርዓዊ ዮሀንስና ሲሳይ ገሰሰ ያሉ የሙዚቃ ሰዎች ተካተውበታል፡፡ ይህ ስራዋ ለበርካቶች እንደመረጃ ምንጭ ሆኖ ለማገልገል በቅቷል፡፡
የሸዋሉል በአስር ዓመት ዕድሜዋ የጻፈችው ‹‹የእዮብ ትዕግስት›› የተሰኘ ድርሰቷ የመጀመርያዋ ነው። በአንድ ወቅት ለጸደይ መጽሔት በሰጠችው ቃለ-መጠይቅ ላይ እንደተናገረችው በታዳጊነት እድሜዋ የጻፈችው ይህ ድርሰት ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ጥቂት ማሻሻያ አክላበት በኢትዮጵያ ሬድዮ ‹‹የትያትር ጊዜ›› በተባለ ፕሮግራም ላይ ተላልፎላታል። ከዚያም በ1967 ትዳሯን ትታ አዲስ አበባ በመምጣት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኛ ሆናለች፡፡ በቆይታዋም በዜና አንባቢነትና ፕሮግራም አዘጋጅነት አገልግላለች፡፡ የሬዲዮ ድራማ ጸሀፊም ነበረች፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመስራት ላይ እያለች የቀበሌ ሊቀመንበር በመሆን ህይወቷን ወዳሳጣት የፖለቲካ ዓለም ገባች፡፡ በቀበሌ ሊቀመንበርነቷ የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴ ሊቀመንበር፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የከፍተኛ የቀበሌ ማህበራት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ሆነች፡፡ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) አባልም ነበረች፡፡
የሸዋሉል የጋዜጠኝነትና የደራሲነት ሥራዋን ያለማቋረጥ በማዳበር ልዩ ልዩ ሥራዎችን አበርክታለች፡፡ በ1968 ‹‹እስከመቼ ወንደላጤ›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትማ በብዙዎች ተነቦላታል፡፡ ጋብቻና ፍቺ፣ ጾታዊ ግንኙነትና ወንደላጤነት ላይ የሚያጠነጥነው ይህ ድርሰት በወቅቱ በአደባባይ የማይነሱ ጉዳዮችን የያዘና አነጋጋሪ ለመሆን በቅቷል፡፡
ወቅቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተካረረ የፖለቲካ አቋም የተፈጠረበት፣ መጠፋፋት የበረታበትና ብዙዎች እንደወጡ የሚቀሩበት ነበር፡፡ የሸዋሉልም ከመሰል አደጋ ራሷን እንድትጠብቅ ተመክራለች፡፡ ነገር ግን ፍጹም ባላሰበችው ሁኔታ ግንቦት 19 ቀን 1969 ገና በ32 ዓመቷ ተገደለች፡፡ ገዳይዋ አንድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ታጋይ ነበር የተባለ ወጣት መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የሸዋሉል መንግስቱ አንድ ስራ አንድን ግለሰብ ባህር ተሻግሮ አዲስ አበባ እንዲመጣ እስከማስገደድ ደርሷል፡፡ ግለሰቡ ፍሬድሪክ ማርቴል ይባላል፡፡ ፈረንሳዊ ተመራማሪ ነው፡፡ ‹‹ኧረ መላ መላ›› የተሰኘው የሸዋሉል ድርሰት የሆነው የመሀሙድ አህመድ ዘፈን የማረከው ግለሰቡ የዘፈኑን ትርጉም ለማወቅ እዛው ፓሪስ የሚገኝ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ ትምህርት ቤት ገብቶ አማርኛ ቋንቋን ተማረ፡፡ ከእዛም በዘፈኑ ግጥሞች በመደነቅ ገጣሚዋን ፍለጋ አዲስ አበባ መጣ፡፡ እናም ስለሸዋሉል ኑሮና ስራዎች ከስር መሰረቱ አጠና፡፡
የሸዋሉል መንግስቱ ዛሬም ድረስ የምትታወስ ጥቂት ዘመን ኖራ ብዙ ትታ ያለፈች ብርቱ ሴት ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲ ነበረች፡፡
ምንጮቻችን፡
- የደራው ጨዋታ – ፋና 98.1፤ ፈረንሳዊውን ከፓሪስ እያበረረ ያመጣው የጋዜጠኛዋ የሸዋሉል እጅግ አስገራሚ ታሪክ ከታዋቂ ዘፋኞች ጀርባ የነበረች ገጣሚ (ክፍል 2)፤ ሰኔ 27 ቀን 2009፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=dYatSeQR6-E
- የደራው ጨዋታ- ፋና 98.1፤ እንደስሟ የተለየች ሳተና ጋዜጠኛ፣ የዘፈን ግጥም ፀሐፊ የሸዋሉል መንግስቱ፡፡ መስከረም 22 ቀን 2010፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=eUDgXTatuBc
- ሸገር ሼልፍ፤ የሸዋሉል መንግሥቱና ህያው የጥበብ ሥራዎቿ/በተሾመ ብርሃኑ ትረካ-ኤልዳ ግዛቸው
https://www.youtube.com/watch?v=ik8kbWtl-ws
- አዲስ1879፤ የሸዋሉል መንግሥቱ አሳዛኝ አሟሟት፤ ግንቦት 19 ቀን 2013
https://www.youtube.com/watch?v=Y0f56Sk3rzU
- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ ‹‹ሬዲዮ ትናንትና ዛሬ›› መጽሄት፤ የካቲት 2013፡፡
Comments