ይማሩ/ MIRH/ 17 ጥር 2022
በዴቪድ ብርወር የተፃፈ
ትርጉም በፍቃድ አለሙ
ይህ የስልጠና አጋዥ ጹሑፍ የተዘጋጀዉ በጃፊና ሲሪላንካ ለሰለጠኑ የብሮድካስት ጋዜጠኝነት ተማሪዎች ሲሆን ሥልጠናዉ በተለይም ቀደም ያለ የጋዜጠኝነት ልምድም ሆነ ስልጠና ያላገኙ ሰልጣኞች በልዩነት በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ላይ ትኩረት በማድረግ የተሰጠ ነው፡፡
የሬዲዮ ዜና ጹሑፎችን እንዴት እናዘጋጅ:
ጠቃሚ የሆኑ እና የተመረጡ ርእሰ ጉዳዮችን በማንሳት በግልፅ ቋንቋ እና በጠቃሚ የድምፅ ግብዓቶች የተከሸኑ ቁምነገር ዘገባዎችን ማቅረብ ከሬዲዮ ጋዜጠኞች የሚጠበቅ ነዉ፡፡
ለሬዲዮ የተቀረፁ ልዩ ልዩ ድምፆች ወጥ ወደሆነ ስሜት ሰጪ ዜናነት የሚያድጉት በስክሪፕት ጹሑፍ አማካኝነት ነዉ፡፡ የዜናዉን ዐብይ ነጥቦች እና በቃለ–መጠይቅ የተካተቱ አሳቦችን ማጉላት የሚቻለዉ በምንጽፈዉ የሬዲዮ ስክሪፕት አማካኝነት ነዉ፡፡ በሬዲዮ ዜና ዉስጥ ከምንጠቀማቸዉ የተቀረፁ ድምፆች ባልተናነሠ ለስክሪፕታችን የምንጠቀማቸዉ ቃላት እጅግ ወሳኝ ናቸዉ፡፡ የሬዲዮ ዜና አጫጭር እና ቀላል ዓረፍተ ነገሮችን በመጠቀም በአድማጮች ዘንድ በተለመዱ ቃላት መፃፍን ይጠይቃል፡፡ ዉስብስብ እና ረጃጅም ዓረፍተ ነገሮችን መጠቀም አድማጮችን ግራ ሊያጋባ እና ዐብይ ጉዳዩን መጨበጥ እንዳይችሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡
በቀላሉ የሚደመጥ እና ትርጉም ሰጪ የሆነ የሬዲዮ ስክሪፕት ለማዘጋጀት የሚያግዙ ዋና ዋና ዘዴዎች ቀጥሎ ተዘርዝረዋል፡
በዜና ጹሑፍ (ስክሪፕት) ውስጥ የድምፅ ግብዓቶችን ስለማስተዋወቅ:-
በሬዲዮ ዜና ዉስጥ የምናካትታቸዉን እንደ ቃለ መጠይቅ ያሉ ድምፆች ለአድማጭ ጆሮ ከማድረሳችን በፊት የድምፅ ግብዓቶቹን ምንነት (አስፈላጊነት) በምንጽፈዉ ስክሪፕት አማካኝነት ማብራራት ይኖርብናል፡፡ በስክሪፕታችን ቀጣዩን የድምፅ ግብዓት (ለምሳሌ፣ ቃለ መጠይቅ ወይም የተፈጥሮ ድምፆች) በምናስተዋዉቅ ጊዜ በድምፅ ግብዓቱ የሚካተቱ አሳቦችን በመተው ድግግሞሽን ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ስክሪፕታችን በጣም ረዝሞ በድምፅ ግብዓቱ ልናስተላልፍ የሚገባንን መልዕክት ከበቂ በላይ እንዳይጠቀልልብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
በዜና ጹሑፍ (ስክሪፕት) የአድማጮችን ቀልብ ስለመሳብ:-
የአድማጮችን ቀልብ ለመሳብ የመጀመሪያዉ ዘዴ ቀጥተኛ እና ቀላል የአፃፃፍ ዘዴዎችን መጠቀም ነዉ፡፡ ይህንን የምናደርገዉ የተፈፀሙ ድርጊቶችን በቀጥታ በማስቀመጥ እንዲሁም የጉዳዩን ቁልፍ፣ ቁልፍ ዝርዝሮች ከወሳኝ ወደ ቀላል እርከን በማስቀመጥ ነዉ፡፡ ይህ ሲባል ምንም እንኳን የዜናችን ዝርዝር ጉዳዮች ክብደት እየቀነሰ ቢመጣም ዜናችን እስከመጨረሻዉ ድረስ ስሜት የሚሰጡ እና ከዋና ጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸዉ ሃሳቦችን ሊይዝ ይገባል፡፡
የግል ምልከታ እና አስተያየቶች:-
በዜና ጹሑፍ (ስክሪፕታችን) የምንጠቀማቸዉ ቃላት የእኛን የግል ምልከታ የሚያንፀባርቁ እና ስሜት አዘል መሆን የለባቸዉም፡፡ ዜናዉ የያዘዉን አሳብ አዳምጦ አሳብም ሆነ ዉሳኔዎችን መያዝ የአድማጮች ድርሻ ሲሆን ስሜታዊ አገላለፆችን በመጠቀም የአድማጭን ቀልብ ለመያዝ መሞከር ፈፅሞ ያልተገባ ነዉ፡፡
ሚዛናዊ እና የተሟላ አቀራረብ:-
በዜና ጹሑፍ (ስክሪፕት) ጊዜ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ ልዩ ልዩ የድምፅ የአሳብ ግብዓቶችን በማካተት ዜናዉ ከአድሎአዊነት ነፃ የሆነ እና ከተካተቱት ግብዓቶች ዉስጥ ለየትኞቹም ጉዳዮች ወገናዊነት የማያንፀባርቅ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ዜናችን በምንም ዓይነት መልኩ አቅጣጫ የሚያስት ወይም ጫና የሚያሳድር መሆን የለበትም፡፡
የዜና ጹሑፍ (ስክሪፕት) እና ቃለ መጠይቆች
ምንም እንኳን አንዳንድ ጋዜጠኞች ስክሪፕት የሚጽፉት ቃለ መጠይቅ ከማድረጋቸዉ ቀደም ብሎ ቢሆንም ይህንን ማድረግ የቃለ መጠይቅ ፍሬ አሳቦችን ለጻፍነዉ ስክሪፕት በሚመች መልኩ ብቻ መቆራረጥ ተገቢ አይሆንም፡፡
አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ የዜና ጽሑፍ ከመጻፋቸዉ በፊት የሚካተቱ የድምፅ ግብዓቶችን ለማድመጥ የሚፈልጉ ሲሆን ይሄኛዉ ስሜት የሚሰጡ ስክሪፕቶችን ለመፃፍ የተሻለ አማራጭ ነዉ፡፡ ሆኖም እጅግ በርካታ (ወይም ረጃጅም) የድምፅ ግብዓቶቸ በሚኖሩን ጊዜ የዜና ጽሑፉን ከግብዓቶች ጋር ማጣመር እና የመጀመሪያ እና የመቋጫ ድምፆችን መወሰን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡
ማጣራት:-
በዜና ጽሑፋችን (ስክሪፕታችን) የምናካትታቸዉን አሳቦች እዉነተኛነት እና ትክክለኛነት ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፡፡ ከምንጽፈዉ ስክሪፕት ባለፈም ቃለ መጠይቅ የምናደርጋቸዉ ሰዎች የሚሰጡን መረጃ የተረጋገጠ መሆኑን ማጣራት የሚያስልግ ሲሆን በምናጣራበት ጊዜ የምናገኛቸዉን ተጨማሪ መረጃዎች ወደ ስክሪፕታችን ማካተት አስፈላጊ ከሆነ ማካተት ይኖርብናል፡፡
የሥነ ምግባር ጉዳዮች:-
ገለልተኝነት፣ ሚዛናዊነት እና ፍትሓዊነት በመባል የሚታወቁት የጋዜጠኝነት መርሆች በስክሪፕታችን መካተታቸዉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ቃለ መጠይቅ የምናደርጋቸዉ ሰዎች ጠንካራ አሳብ እና አስተያየት ቢኖራቸዉም በዜናዉ ዉስጥ ከሚካተቱት ልዩ ልዩ አሳቦች መካከል ያለ በቂ ምክንያት አንድን ሃሳብ ብቻ ማጉላት ተገቢ አይደለም፡፡ የስክሪፕታችን ሚዛናዊነት የተጠበቀ መሆን ይገባል፡፡
አፃፃፍ:-
የዜና ጹሑፋችን (ስክሪፕታችን) የጉዳዩን ዋና ዋና አሳብ በቀላል እና ቀጥተኛ አገላለፅ በማቅረብ መጀመር የሚኖርበት ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት አንቀፆች በኋላ ዋና ጉዳዩን በተጨማሪነት የሚያብራሩ ትንተናዎች እና የአዉድ ማብራሪያዎች ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡
አሻሚ የሆኑ አገላለፆችን በመጠቀም ስክሪፕታችንን መዝጋት ፈፅሞ ተገቢ አይደለም፡፡ የስክሪፕታችን መደምደሚያ ግልፅ የሆነ እና መረጃ ሰጪ አሳብ ሊይዝ የሚገባዉ ሲሆን በቃለ መጠይቃችን ወቅት ምንጮቻችን የሚሰጡንን አሳቦች እንደመነሻ ልንጠቀም እንችላለን፡፡
ስሜት የሚሰጡ ጽሑፎች (ስክሪፕቶች):-
ስክሪፕታችንን ጽፈን ስንጨርስ ለራሳችን ደግመን በማንበብ ስሜት የማይሰጡ፣ ግራ የሚያጋቡ፣ ወይም ሌላ ማስተካከያ የሚሹ የጽሑፎቻችንን ይዘቶች ከተቻለ ከባልደረቦች ጋር በመሆን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይም ቀርፀን ያካተትናቸዉን የድምፅ ግብዓቶች በድጋሚ በማዳመጥ አስፈላጊ ድምፆች ሁሉ መካተታቸዉን ማረጋገጥ ይመከራል፡፡
ጥያቄዎች
ከሚከተሉት አሳቦች ዉስጥ እዉነት የሆነዉን ለዩ?
- በሬዲዮ ዘገባ ዉስጥ ዋናዉን ቦታ የሚይዙት የድምፅ ግብዓቶች ስለሆኑ ዋና ዋና ድምፆችን መሰብሰብ እንጂ ስለሚፃፉ ቃላት መጨነቅ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ስክሪፕታችንን የሚያዳምጡት እንጂ የሚያነቡት ባለመሆኑ እና ቃላቱ ትክክለኛ እስከሆኑ ድረስ ድምፅን ከመደገፍ ያለፈ ያን ያህል ወሳኝ አይደሉም፡፡
- ጥሩ የሬዲዮ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ቃላት እጅግ አስፈላጊ ናቸዉ፡፡ የምንፅፈዉ ስክሪፕት የተመጠነ እና አድማጮች በቀላሉ በሚረዱት ቋንቋ የተፃፈ መሆን ይኖርበታል፡፡የድምፅ ግብዓቶቻችን ምንም ያህል ጥራት ቢኖራቸዉም ስክሪፕታችን በጥንቃቄ ካልተፃፈ የምንፈልገዉን መልእክት ማስተላለፍ አንችልም፡፡
Comments