ይማሩ

የምርመራ ጋዜጠኝነት ምንነት

ይማሩ /MIRH/ 25 ሀምሌ 2014

በስንታየሁ አባተ

ጋዜጠኝነት እንደሚሸፍናቸው ይዘቶችና የሥራ ባህሪያት በዋናነት በሰባት ዓይነት ዘርፎች ሊከፈል ይችላል፡፡ ለምሳሌ የፖለቲካ ጉዳዮች ልዩ ትንተና፣ የንግድና ንዋይ፣ የአውደሰብ፣  የወንጀል ጉዳዮች፣ የኪነ ጥበብ፣ የስፖርት፣ ትምህርታዊ እና የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚሉትን ልንጠቅስ እንችላለን፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት ከጊዜና ከገንዘብ ባሻገር ሰፊ የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ ጥልቀት ያላቸው የሰነድ ማስረጃዎችን መፈተሽ፣ በጉዳዪ ዙሪያ አስፈላጊና በቂ ሰዎችን ማናገር፣ ብሎም ጋዜጠኛውን በብርቱ የሚፈትንና እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ማለፍ የግድ ይላል፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ጋዜጠኞች ወንጀልን፣ ፖለቲካዊ ሙስናን (በሥልጣን መባለግን) ወይም ተቋማዊ ስህተቶችን ለማጋለጥ ከወራት ባለፈ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፡፡

የጋዜጠኞችን ብስለትና ከፍተኛ የሙያ ክህሎት የሚጠይቅ ዘርፍ ሲሆን የዘገባ መነሻ ሀሳብን በጥልቀት ከመረዳት ጀምሮ አስፈላጊ የሰነድና የሰው መረጃዎችን በመለየት፣ መሰረታዊ የምርመራ ጥያቄዎችን በማዋቀር፣ የሥራ ቅደም ተከተሎችን በማቀድና በመተግበር ጋር የተያያዙ ተግባሮችን የሚያጠቃልል ሂደት ነው፡፡ ሥራው መሰረታዊ የጥናትና ምርምር ባህሪያት የሚታዩበት ጥንቃቄን፣ እርጋታን፣ የባለሙያዎችን፣ የተቋማትንና ግለሰብ ባለድርሻዎችን ትብብር የሚሻ ነው፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነትን የሚበይኑ የተለያዩ ሰነዶች እንደሚሉት የምርመራ ጋዜጠኝነት ማለት ከዕለት ተዕለት ጋዜጠኝነት በተለየ ሁኔታ ምንጮች፣ የአንድ መረጃ ባለቤቶች ወይም አቃብያን ከጋዜጠኞች የሚደብቁትን መረጃ ይፋ ለማድረግና ለማጋለጥ የሚከናወን ዘገባ የማጠናቀር ሂደት ነው፡፡ የዘገባው ዓላማ ሕገወጥነትን በማጋለጥ ሕግን፣ ፍትህን፣ ሰብዓዊ መብትንና የሕዝብ ጥቅምን ማስከበር ነው፡፡

የምርመራ ዘገባ በአብዛኛው ሕገ ወጥ ድርጊትንና ወንጀልን ከማጋለጥ ተግባር ጋር ይያዛል፡፡ በምርመራ ሕገወጥና የወንጀል ድርጊት ቀድሞ ከተደረሰበት ሕዝብ ሳይጎዳ ለመከላከል ይረዳል፡፡ የተፈፀመም ከሆነ ተጠያቂነትና ፍትህ እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ከደቂቃዎች የዜና ዘገባ እስከ ጥልቅ የምርመራ ዘጋቢ ፊልም ድረስ ሊሰራበት የሚችል ዘርፍም ነው፡፡

መሰረታዊ የምርመራ ጋዜጠኝነት መርሆዎች

ጋዜጠኝነት እንደሙያ ካሉት መለያ መርሆዎች በተጨማሪ የምርመራ ጋዜጠኝነትን በተለይ የሚመለከቱ ሦስት ዋነኛ መርሆዎች አሉ፡፡ እነዚህም ከተለመደውና ከሚመቸው ቀላል አሰራር መውጣት፣ ከግል አስተያየት ነጻ መሆን፣ እና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት መራቅ ናቸው፡፡

የምርመራ ዘገባ በምን ይለያል?

አንድን የተበላሸ ተግባር እስከመጨረሻው በጥልቀት የሚመረምር፣ ሲያጠናቅቅና ዘገባውን ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለሚሹ የፖሊስና የፍትህ ተቋማት ትልቅ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆኑ አንዱና ዋነኛ መለያው ነው፡፡

የምርመራ ዘገባ ስሙ እንደሚያመለክተው መረጃን አነፍንፎ ማግኘትን፣ የተገኘውን መረጃ ትክክለኝነት ማጣራትን፣ ከአንድ ምንጭ የተገኘን መረጃ ከሌላ ምንጭ ከተገኘው ጋር ማነጻጸርን በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ ተጠራጣሪነትን መጠቀምን ያካትታል፡፡ ሙያው መረጃን ከመሰወር አንስቶ ጋዜጠኛውን በኃይል ተስፋ ለማስቆረጥና ለማስፈራራት አቅም ያላቸውን ልዩ ልዩ ባለሥልጣናትንና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን መመርመርን ስለሚያካትት ተግዳሮቱ ከፍተኛ ነው፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት ከእለት ተእለት የዘገባ ሥራ ጋር መሰረታዊ መርሆዎችን የሚጋራ ቢሆንም በውጣ ውረዶቹና በፈታኝ ክዋኔዎቹ መብዛት የተለየ ባህሪ አለው፡፡ አንዱና ዋናው ችግር መረጃ ያላቸው ምንጮች ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ መረጃ ለመስጠት ተነሳሽነት አለማሳየታቸው ነው፡፡ ፈቃደኛ ቢሆኑ እንኳ በዘገባው ውስጥ በስም መጠቀስ ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የምርመራ ጋዜጠኞች ምንጮቻቸውን በስም ላለመጥቀስ ወይም የምንጮቻቸውን ማንነት በምስጢር ለመያዝ ቃል ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህንኑ ቃል በማክበር የምንጮቹን ማንነት በምስጢር ለመጠበቅ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የመሟገት ቁርጠኝነት ያስፈልጋቸዋል፡፡

የምንጮችን ማንነት የመደበቅ ኃላፊነት ግን በዘፈቀደ የሚፈጸም ሳይሆን በሙያዊ መርሆዎች ላይ በመመስረት ነው፡፡ ጋዜጠኞች ምንጮቻቸው በስም ያለመጠቀስ ቅድመሁኔታ ሲያስቀምጡ ፈቃደኛ የሚሆኑት የሚከተሉትን መርሆዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ (1) ምንጩ መረጃውን የሚሰጠው እውነትን በማውጣት ህገወጥ ድርጊትን ለመከላከል ከሚል ሀሳብ እንጂ ማንንም ከመጉዳት ፍላጎት አለመነሳቱን ማረጋገጥ፤ (2) በስም መገለጽ የሚፈልገው ምንጭ ከሚሰጠው መረጃ አንጻር ምትክ የማይገኝለት የመረጃው ባለቤት መሆኑን ማወቅ፤ (3) ከምንጩ የሚገኘው መረጃ ትክክለኛና ቢቀር ዘገባውን የሚያጎድል መሆኑን እንዲሁም የያዘው የዜና እሴት ከፍ ያለ መሆኑን ማረጋገጥ፡፡

የምርመራ ዘገባ መስራት ለጋዜጠኞችና ለመገናኛ ብዙሀን ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያስገኛል፡፡ ከጥቅሞቹ መካከል ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የመረጃ ዋጋ ያለው ዘገባ በማቅረብ ህገወጥነትን ይከላከላል፤ ፍትህና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ የህብረተሰቡን ሰላምና ዲሞክራሲ ይንከባከባል፤ የፖለቲካ ስርዓቱና የመንግስት አሰራር ግልጽና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የምርመራ ዘገባ አዘውትረው የሚሰሩ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሀን በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ስለሚያገኙ በገበያ ላይ የሚይዙት ስፍራ እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ ባለሙያዎችም ከፍተኛ ሙያዊ እውቅና ያገኛሉ፡፡

የምርመራ ዘገባ መነሻ ሐሳብ

የምርመራ ዘገባ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ለመነሻ የሚሆናቸውን ጉዳይ ከጭምጭምታና ሀሜቶች፣ ከተለያዩ ምንጮች ከሚደርሱ ጥቆማዎች፣ ከምልከታቸው፣ ከተለያዩ ዘገባዎች፣ ከማኅበረሰብ ትስስር ገጾችና ሌሎችም ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጋዜጠኞች በምርመራ ሊሰሩባቸው በሚያስቧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መረጃ በመስጠት የሚያግዙ እንደ ሀሮ (Help a Reporter Out-HARO or https://www.helpareporter.com/  ያሉ የጋዜጠኞች መገናኛ መረቦች መኖራቸው የመረጃ ግኝትና ፍሰትን እያቀለለው ነው፡፡

በምርመራ ጋዜጠኝነት ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች

የምርመራ ዘገባን የሚሰሩ ጋዜጠኞች የመረጃ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መረጃውን ማን ጻፈው? መረጃውን ማን ነው ያቀበለው? የመረጃ ምንጮች አስተማማኝነት እስከ የት ድረስ ነው? ምንጩ መረጃውን ለመስጠት ያነሳሳው ምክንያት ምንድነው? የደረሰው መረጃ ወይም ጥቆማ ሕዝባዊ ጠቀሜታው ምንድነው ነው? በመረጃ ምንጮችና በጉዳዩ መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ዘገባው ቢሰራ ያሉ የጥቅም ግጭቶችና ተጽእኖ ወይም ለውጥ የማምጣት አቅሙስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎች በጥንቃቄ መመለስ አለባቸው፡፡

በተጓዳኝም ከሥራ ጋር በተያያዘ ከመረጃ እስከ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ እጥረት፤ ከገንዘብ እስከ የቡድን ሥራ ልምድ ውስንነት፤ ከመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለቤቶቻቸው ጫናና የጥቅም ግጭት እስከ ሕጋዊ ከለላ ማጣት ያሉ ፈተናዎችን የሚደቅን መሆኑንም ታሳቢ ማድረግ ግድ ነው፡፡

ለምርመራ ጋዜጠኝነት የሚጠበቁ ቁልፍ ክህሎቶች

ስኬታማ የምርመራ ጋዜጠኛ ለመሆን የማወቅ ጉጉት፣ ጽኑ ሙያዊ ፍቅር፣ መረጃ የማነፍነፍ ጠንካራ ተሰጥኦና የምርመራ ክህሎት ያስፈልጋል፡፡ ተቋማዊ መሰረትና ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ክህሎት እንዲሁም በጫና ውስጥ ለመስራት የሚያስችል ቁርጠኝነት  ይስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ እውቀት፣ ትንታኔ የመስጠት (ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንፃር የመረዳት) እና ትክክለኛና ተገቢ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ክህሎት ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ምርመራ ዘገባ የሚሻቸውን ልዩ ልዩ የተደበቁ መረጃ ይዘቶችን ማነፍነፍ፣ መከታተል፣ ማዳበርና ዘገባው የሚሻውን መረጃ የተሟላ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡

የምርመራ ጋዜጠኛ ለመሆን የተለየ ትምህርት ይጠይቃል?

በሀሳብ ደረጃ አንድ ጋዜጠኛ በጀማሪነት የምርመራ ዘገባ ዘርፍ ለመሰማራት ቢያንስ  በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የተማረ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ለጋዜጠኛው የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ሙያዊ ዋስትና አይሰጥም፡፡ ከትምህርት ቤት የሚገኘው እውቀት ጀማሪው ጋዜጠኛ በተከታታይ የሚያገኛቸውን ሙያዊ ሥልጠናዎች ለመቀበልና ከተሞክሮው ለመማር መሰረት የሚሆኑትን መነሻዎች ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ ጋዜጠኛው የሙያውን ተግባራዊ ሀሁ የሚጀምረውና በሙያ ውጣውረዶችና ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ የሚማርበት እውነተኛ ሥፍራ የዜና ዘገባ ክፍል ነው፡፡ እዚያ ጋዜጠኛው በተሞክሮ እየተማረ ጋዜጠኛ መሆን ይጀምራል፡፡

በምርመራ ዘገባ ላይ ለመሰማራት የሚሻ ጋዜጠኛ በማያቋርጥ የዜና ዘገባ ተሞክሮ ውስጥ ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ የዜና እሴት ባላቸው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔሀብታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ በላይ የዜና ምንጮችን የሚሹ መረጃ ማጣራትንና ማረጋገጥን የሚፈልጉ፣ አወዛጋቢነት ያላቸውን ዘገባዎች የማዘጋጀት ልምድ ሊያዳብር ይገባል፡፡ በሂደቱም ጥያቄ የመጠየቅ ክህሎት፣ በመረጃ ይዘቶች መካከል ያለውን ተዛምዶ የመመልከት፣ የማነጻጸርና የመተንተን ችሎታ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡

ስለምርመራ ጋዜጠኝነት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች

የምርመራ ጋዜጠኝነትን የሚመለከቱ የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የምርመራ ዘገባ በወረትና አንድ ሰሞን ከእለት ተእለት ዘገባ ወጣ ብሎ ‹ለለውጥ› ያህል እንደ ጀብድ የሚሰራ ሥራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የምርመራ ዘገባ ግን ታስቦበትና ታቅዶ የሚከናወን፣ ከግለሰብ ዘጋቢ ይልቅ የዘጋቢዎች ቡድን ቢሰራው የሚመረጥ፤ ብዙ ድካምንና ፈተና መጋፈጥን የሚጠይቅ፣ የተቋምና የህግ ጥበቃ የሚያሻው ፈታኝ የሙያ ዘርፍ ነው፡፡

በምርመራ ጋዜጠኝነት ዘጋቢውን ከሚዘገብው ዘገባ በላይ አድርጎ ማየት ከተለመዱትና ከተሳሳቱት አመለካከቶች አንዱ ነው፡፡ የምርመራ ዘገባ ዋና ዓላማ አንድ ታዋቂና ዝነኛ ጋዜጠኛ መፍጠር አይደለም፡፡ የሥራው አፈጻጸምም የአንድ ግለሰብ ጋዜጠኛ የጀብዱ ተግባር ሳይሆን የቡድን ሥራ ነው፡፡ ሥራው ከእለት ተእለት የዘገባ ሥራ የሚለው በሚፈልገው ክህሎት፣ ቁርጠኝነት፣ ተጨማሪ የሰውኃይል ወይም ቡድን፣ ጊዜና ሀብት እንጂ ሙያው ያው ጋዜጠኝነት ነው፡፡ የባለሙያውም ተልዕኮ እንደማንኛውም ጋዜጠኛ ሁሉ ለእውነት፣ ለህጋዊነትና ለፍትህ በመሥራት ህዝብን ማገልገል ነው፡፡ ከዚያ በላይ የምርመራ ጋዜጠኛ መሆን ለጋዜጠኛው ከሙያው ሥነምግባር በላይ የሚያደርገውን መብት አይሰጠውም፡፡

ሌላው ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነት የተሳሳተው አመለካከት ደግሞ ዘገባው በአገር መሪዎች፣ በከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን እርከንና ብዙ ቢሊዮን ብር በሚያንቀሳቅሱ ትልልቅ ኩባንያዎች የጥቅም ትስስር በሚከናወን የዘረፋና የቅሌት ተግባሮች እንዲሁም የተጭበረበሩ አገር አቀፍ ምርጫዎች ምርመራ ላይ በማተኮር መወሰን ነው፡፡ ይህ አመለካከት ብዙ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሀን ራሳቸውን በማሳነስ ወደ ምርመራ ዘገባ እንዳይገቡ የሚከለክል ጎታች አለመካከት ነው፡፡ የምርመራ ዘገባ ግን በየትኛውም እርከን ሊሰራ የሚችል በየአካባቢው ያሉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔኃብታዊና ማህበራዊ ብልሽቶችና የተዛቡ አሰራሮች ላይ አተኩሮ ሊከናወን የሚችል ነው፡፡

የምርመራ ዘገባ እንከኖችን፣ ጥፋቶችንና መጥፎ ተግባሮችን በማጋለጥ ብቻ የሚወሰን ነው ብሎ ማሰብም ሌላው የተለመደ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ የምርመራ ዘገባ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከህዝብ እይታ የተሰወሩ መልካም ተግባሮችንና የማህበረሰብንና የግለሰብ ተሞክሮዎችን በጥናትና በምርምር ላይ ተመስርቶ በመዘገብ ህዝብ እንዲጠቀምባቸው ማድረግም የምርመራ ዘገባ አንድ አካል ነው፡፡

 

ምንጮቻችን፡

  • ማዕረጉ በዛብህ (1995)፤ የጋዜጠኝነት ሙያ፡ ንድፈ ሀሳቡና አተገባበሩ፡፡ አዲስ አበባ፤ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፡፡
  • Forbes, Derek. A watchdog’s guide to investigative reporting: A simple introduction to principles and practice in investigative reporting. KONRAD ADENAUER STIFTUNG:JOHANNESBURG, 2005.
  • Hunter, Mark Lee. Ed.  UNESCO, The Global Investigative Journalism Case Book: UNESCO Serieses on Journalism Education. UNESCO: 2012
  • National Open University of Nigeria. Investigative and Interpretive Reporting . NOUN. Abuja: 2012

በአሉ ግርማ: ጋዜጠኛው ደራሲ

Previous article

ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፡ የአፍሪካው አንጋፋ የዜና ድርጅት

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply