የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ከፋለ ማሞ፡ የመብትና የነጻነት ተሟጋች ጋዜጠኛ

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 10 መስከረም 2015

በመቅደስ ደምስ

ከፋለ ማሞ ከአባቱ ከአቶ ማሞ ዓለሜ እና ከእናቱ ወይዘሮ ደስታ በጋሻው በሰሜን ሸዋ፣ ሰላሌ ሀምሌ 16 ቀን 1930 ተወለደ። አዲስ አበባ በሚገኘው አምሀ ደስታ ትምህርት ቤት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን ተማረ፡፡ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ ከእዛም እንግሊዝ ሀገር ሄዶ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀበለ።

በኋላም ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዊስኮንሲን ማዲሰን በጋዜጠኝነት የማስተርስ ዲግሪውን አገኘ። ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የቀድሞው የባህር ሀይል መምሪያ የአድሚራል እስክንድር ደስታ ልዩ አማካሪ ሆነ፡፡ በመቀጠል ለረጅም ዓመታት ባገለገለበት የማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያቤት የሬድዮ መምሪያ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ፡፡ በኃላፊነቱም የኢትዮጵያ ሬድዮን በማዘመን በሀገራችን ታዋቂ የሆኑ ጋዜጠኞችን ሙያዊ ክህሎት በማሳደግ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራውን አኑሯል። በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡

ምስል አንድ፡- ጋዜጠኛ ከፋለ ማሞ

ከፋለ ከመንግስት በተሰጠው ኃላፊነት በተለያዩ ጊዜያት የአርሲ ገጠር ልማት ድርጅትን፣ የመተሀራ ስኳር ፋብሪካንና የተለያዩ የመንግስት ልማት ድርጅቶችና ፋብሪካዎችን ስራ አስኪያጅ በመሆን መርቷል፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሆኖም ነበር።

የ1983ቱን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች መስፋፋት ሲጀምሩ ከፋለ ከረጅም ጊዜ ወዳጁ ጳውሎስ ኞኞ ጋር ሆኖ ‹‹ሩህ›› የተሰኘ መጽሄት በመመስረት ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡

በአገሪቱ የግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችን ፈተና መብዛት ተከትሎ ከፋለ ማሞ ከሙሉጌታ ሉሌ፣ አበበ ገላው እና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞች ጋር የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ)ን በመመስረት የማህበሩ የመጀመሪያ ሊቀመንበር ሆኗል፡፡ በማኅበር ፕሬዚዳንትነቱ ከመንግስት የተለያዩ ዛቻዎች እና ወከባዎች ይደርስበት ነበር፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ወህኒ ቤት እንዲገባ ተደረጓል፡፡

ፈተናዎች ግን አላሸነፉትም፡፡ የኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማኅበርን በመወከል በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በነፃ ፕሬስና በጋዜጠኝነት ሙያ ዙሪያ የሚደረጉ ሴሚናሮችንና ስብሰባዎችን ተካፍሏል፡፡ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ የወቅቱ መንግስት በግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን ወከባ አጋልጧል፡፡ በወህኒ ቤቶች ለሚማቅቁት የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች አንደበት በመሆን ለዓለም ማኅበረሰብና ለዓለም አቀፍ የሙያ ማኅበራት በደልና ስቃያቸውን አስተጋብቷል፡፡

ከመንግስት የሚመጣው ማስፈራሪያ እያየለ ሲሄድና ሀገር ውስጥ መቆየት ለእሱም ሆነ ለቤተሰቡ አስጊ ሲሆን ወደ ኔዘርላንድ ተሰደደ፡፡ በስደት እያለም ሀገሩን ከማገልገል አልተቆጠበም፡፡ የኢትዮ ቲቪ ዋና አዘጋጅ በመሆን ወጣት ጋዜጠኞችን በሙያው ደግፏል፡፡ የኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዢን (ኢሳት) ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስተርዳም ሲቋቋም በቀዳሚ ጋዜጠኛነት፣ በማማከርና በተባባሪ አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡

ከዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማኅበራት ጋር አስቀድሞ በፈጠረው መልካም ግንኙነት መሰረት መረጃ በመለዋወጥ ለትግሉ መጠናከር አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በመንግስት የሚደርስባቸውን ስቃይ በመሸሽ ለሚሰደዱ የግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች በየተሰደዱበት አገር ከለላ እንዲያገኙ የትብብርና የምስክርነት ደብዳቤዎችን በመጻፍ ብዙዎችን ታድጓል፡፡

በአውሮፓ ከተሞች ሲደረጉ የነበሩትን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባዎችና ስለ ሀገር የሚደረጉ ማኅበራዊ ውይይቶችን ከሚኖርበት ሆላንድ አንዳንዴ በጀርመን፣ በቤልጅየምና በፈረንሣይ እየተገኘ ሀገር ቤት ለሚታተሙ መጽሔቶች ዘገባዎችን ይልክ ነበር፡፡ በተለይ በወቅቱ ተወዳጅ ለነበረችው የጦቢያ መጽሔትና ጋዜጣ የብዕር ስሞች እየተጠቀመ ጽሁፎች ይልክ ነበር።

ከብዕር መለየት የሚያስፈራው ከፋለ ማሞ ‹‹ለእንቅልፍ አልጋ ላይ እስክወጣ ዓይኔ ከንባብ፣ እጄ ከመጻፍ ከቶውንም አይለያዩም›› ይል ነበር፡፡ ከ50 ዓመታት በላይ በዘለቀ የጋዜጠኝነት ህይወቱ ብዙ ወጣት ጋዜጠኞችን በማሰልጠን ብቁ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ለሀገሩ አፍርቷል። ከጋዜጠኝነት ሙያ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ መሪነት ጉልህ ተሳትፎ ነበረው፡፡

ከፋለ ከመንግሥት ጋር ተጋፍጦ ለግል መገናኛ ብዙሃን ማበብ ላደረገው አስተዎጽኦ የተለያዩ ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡ ዋና መቀመጫውን ብሩሰልስ – ቤልጂየም ያደረገው International Federation For Journalists (IFJ)፣ የኔዘርላንዱ የጋዜጠኞች ማኅበር Dutch Association of Journalists፣ እንዲሁም በጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ ሮብ ቤከር (Rob Bakker) ስም የተሰየመውና ለነፃ ፕሬስ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ጋዜጠኞች የሚሰጠው ሽልማት ከፋለ ካገኛቸው ሽልማቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በመልካም ሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ሰውንና ስራውን አክባሪና በእጅጉ ሀገሩን የሚወደው ጋዜጠኛና የነጻነት ታጋዩ ከፋለ ማሞ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በ83 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከፋለ የአንዲት ሴት ልጅ አባትና የሁለት ልጆች አያት ነበር፡፡

ምንጮቻችን፡-

  • መረጃ (Mereja.com) ‹‹አንጋፋው ጋዜጠኛ እና የነጻነት ታጋይ አቶ ከፋለ ማሞ አረፉ›› ጥቅምት 5 ቀን 2014 https://mereja.com/amharic/v2/609155  (October 15, 2021)
  • ኢትዮ-ፓኖራማ፤ (በአበበ ገላው) ‹‹የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ከፋለ ማሞ አረፉ›› ጥቅምት 4 ቀን 2014፡፡ https://ethiopanorama.com/?p=145920 (Oct 14, 2021)
  • ኢትዮ-ሪፈርነስ፣ (ጌታቸው አበራ) ‹‹ጋዜጠኛ ከፋለ ማሞ አለሜ ሲታወስ-1930-2014›› ጥቅምት 12 ቀን 2014፡፡ https://ethioreference.com/archives/29877 (Oct. 22, 2021)

ደምሴ ዳምጤ፡ የአራት አስርታት የሬድዮ የስፖርት ጋዜጠኝነት

Previous article

ሰለሞን ተሰማ፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ስፖርት ጋዜጠኛ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply