የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን)

የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/ 17 ነሀሴ 2014

በመቅደስ ደምስ

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ዋና መቀመጫውን በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ያደረገ፣ ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) የሆነ የክልሉ መገናኛ ብዙሀን ነው፡፡

ኦ.ቢ.ኤን አሁን ያለውን መዋቅር ከመያዙ አስቀድሞ በአራት የኦሮሚያ ክልል የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ሥር አልፏል፡፡ እነርሱም የኦሮሚያ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ፣ የኦሮሚያ ባህልና ህዝብ ግንኙነት ቢሮ፣ የኦሮሚያ መገናኛ ብዙሐን ድርጅት እና የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ናቸው፡፡

ድርጅቱ በመጀመሪያ ይተዳዳር የነበረው በኦሮሚያ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሥር ነበር፡፡ በ1989 የኦሮሚያ ባህልና ስፖርት ቢሮ ከኦሮሚያ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ጋር በመዋሀድ የኦሮሚያ ባህልና ህዝብ ግንኙነት ቢሮን ፈጠሩ፡፡ በወቅቱም ቢሮው ከኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌዥቭን ድርጅት የአየር ሰዓት በመግዛት STVO (ኤስ.ቲ.ቪ.ኦ) በሚል ስያሜ በሳምንት ለአንድ ሰዓት በቴሌዥቭን እና በሳምንት ለ90 ደቂቃ በሬድዮ ዝግጅቶቹን ሲያሰራጭ ቆይቷል፡፡

ለዘጠኝ ዓመታት የክልሉን የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሥራ ያከናውን የነበረው ንዑስ ቢሮ ራሱን ወደ ኦሮሚያ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት ለወጠ፡፡ በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ሬድዮ ራሱን ችሎ ከአዲስ አበባ በቀን የ6 ሰዓት ስርጭት ነበረው፡፡ ቆይቶም አዳማ ከሚገኘው ከራሱ ስቱዲዮ በቀን ለ9 ሰዓት ስርጭት ጀመረ፡፡

የኦሮሚያ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት ከሬዲዮ ባሻገር መጋቢት 16 ቀን 2001 በአስር ማሰራጫ ጣቢያዎች የኦሮሚያ ቴሌዥቭን ስራ እንዲቀጥል በማድረግ የተለያዩ መሰናዶዎችን ለተመልካቾቹ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ተቋሙ በ2003 የስም ለውጥ በማድረግ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚል ስያሜ ያዘ፡፡ ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ2010 በአዋጅ ቁጥር 208/2010 መሰረት አሁን ያለው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ተቋቋመ፡፡

ኦ.ቢ.ኤን በሬዲዮ በኤፍ. ኤም፣ በአጭር ሞገድ እና መካከለኛ ሞገድ አማካኝነት በ18 ማሰራጫ ጣቢያዎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ተደራሽ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኦ.ቢ.ኤን ከሬዲዮኑ ባሻገር ሶስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉት፡፡ እነርሱም OBN Tv (ኦ.ቢ.ኤን. ቲቪ), OBN Horn of Africa (ኦ.ቢ.ኤን ሆርን ኦፍ አፍሪካ) እና OBN Gaammee (ኦ.ቢ.ኤን ገሜ) ናቸው፡፡

ኦ.ቢ.ኤን. ቲቪ በኦሮምኛ ቋንቋ ዜናና የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡ ኦ.ቢ.ኤን ሆርን ኦፍ አፍሪካ ደግሞ አማርኛ፣ አኝዋክ፣ ትግርኛ፣ ጉራጌኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ስዋህሊኛና አረብኛን ጨምሮ በ17 የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያሰራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡

ሶስተኛው ጣቢያ ኦ.ቢ.ኤን ጋሜ ለህጻናት አስተማሪና አዝናኝ የሆኑ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካን ጨምሮ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ተደራሽ ናቸው፡፡

አሁን ላይ ኦ.ቢ.ኤን የ24 ሰአት የቴሌቪዥንና የ17 ሰአት የሬዲዮ ስርጭት አለው፡፡ አማርኛን ጨምሮ በ17 የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ዝግጅቶቹን ለአድማጭ ተመልካቾቹ ያደርሳል፡፡

ኦ.ቢ.ኤን ከአዳማ ስቱዲዮው በተጨማሪ በአዲስ አበባም ማሰራጫ ጣቢያ አለው፡፡ በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ቅርንጫፎቹና ተወካዮቹ ይሰራሉ፡፡ ከሚያቀርባቸው አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶች ባሻገር የማስታወቂያ አገልግሎት፣ የአየር ሰዓት ሽያጭ፣ የስርጭት መሳሪያዎችና የስቱዲዮ ኪራይ፣ የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት፣ የአርካይቭ ሽያጭና መሰል አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡

የድርጅቱ ዓላማ ዘመናዊ የመገናኛ ብዙሀን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሚዛናዊ፣ ወቅታዊና ጥራት ያላቸውን የመረጃ ጥንቅሮች ማቅረብ፤ ማዝናናት፣ ማስተማርና ህዝቡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ልማት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ማስቻል ነው፡፡ የክልሉን መልካም ገጽታ መገንባትና ብሔራዊ አመለካከት መፍጠር ተልዕኮው ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ታማኝና ተመራጭ የመረጃ ምንጭ፣ በአፍሪካ ታዋቂ ብዙሀን መገናኛ መሆን ራዕዩ ነው፡፡ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ባሁኑ ወቅት የተለያዩ ማህበራዊ ብዙሀን መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም ተደራሽነቱን በማስፋት ላይ ይገኛል፡፡

 

ምንጮች፡

  • ኦ.ቢ.ኤን – ‹‹የኦ.ቢ.ኤን. ታሪካዊ ዳራ›› 2010፡፡
  • ቃለምልልስ – ከአቶ መስፍን በዳሳ የኦ.ቢ.ኤን. ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር፡፡ 2014፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ

Previous article

ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply