የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፡ የአፍሪካው አንጋፋ የዜና ድርጅት

የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/ 29 ሀምሌ 2014

በተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) እና ስንታየሁ አባተ

ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በ1934 በያኔው ጽህፈት ሚኒስቴር ስር ‹የፕሬስ ክፍል› በሚል ስያሜ ተቋቋመ፡፡ ዋና ስራው ከዓለም አቀፍ የዜና ድርጅቶች የዓለም ወሬዎችን በሞርስ ኮድ እየተቀበለ ለጋዜጦችና ለአዲስ አበባ ሬድዮ ማከፋፈል ነበር፡፡ ዜና ከልዩ ልዩ ተቋማት ተቀብሎ ለልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሀን የማሰራጨት ስራ በመሰረቱ የዜና አገልግሎት ተግባር በመሆኑና ኢዜአም ይህንኑ ተግባር ሲያከናውን የቆየ ስለሆነ ‹የፕሬስ ክፍል› የተቋቋመበት 1934 ኢዜአ የተመሰረበት ዓመት ሆኖ ይወሰዳል፡፡ ይህም ኢዜአን በአፍሪካ የመጀመሪያው ብሔራዊ የዜና አገልግሎት ድርጅት ያደርገዋል፡፡

‹የፕሬስ ክፍል› ከተቋቋመ ከሁለት ዓመት በኋላ በ1936 ‹አዣንስ ዳይሬክሲዮን› በሚል ስያሜ በአቶ መኮንን ሀብተወልድ ዳይሬክተርነት የሚመራ አንድ ድርጅት ተቋቋመ፡፡ ድርጅቱን ከ1956 እስከ 1963 በዳይሬክተርነት የመሩት ዘውዴ ረታ (በኋላ አምባሳደር) እንደገለጹት የድርጅቱን ስያሜ የፈጠሩት በወቅቱ የፈረንሳይኛ ትምህርት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ስያሜው ከ‹አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ› (የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት) የተቀዳ ነው፡፡

የዳይሬክሲዮኑ አስፈላጊነት በወቅቱ ለብዙዎች የሚኒስቴሩ ሀላፊዎች ግልጽ ስላልነበረ በቂ በጀት አልተመደበለትም ነበር፡፡ የበጀት ችግሩ እየባሰ ሄዶ በ1940 የነበረውም አነስተኛ በጀት በመቀነሱ ዳይሬክሲዮኑ ተዘጋ፡፡ እስከ 1946 ድረስም ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በ1946 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በፕሬዝዳንት አይዘንሀወር ግብዣ አሜሪካን ለመጎብኘት ሲዘጋጁ የጉዟቸውንና የጉብኝታቸውን ዜና ለህዝብ ለማድረስ ሲባል ‹አዣንስ ዳይሬክሲዮን እንደገና ተቋቋመ፡፡

የዳይሬክሲዮኑን ሥራ ለማሻሻል ይደረጉ ከነበሩት ጥረቶች ጋር ድርጅቱ አገራዊ ስያሜ እንዲይዝ ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነበር፡፡ በኋላም በ1957 ድርጅቱ ‹የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ› የሚል ስያሜ አገኘ፡፡ በዚያው ዓመትም በ1934 ተቋቁሞ የነበረው ‹የፕሬስ ክፍል› በኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ ሥር እንዲሰራ ተወሰነ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የድርጅቱ ስያሜ አገራዊ መልክ መያዙን ቢቀበሉም ‹ወሬ› የሚለውን ቃል አልወደዱትም ነበር፡፡ ስለዚህ እሳቸው ሌላ ቃል እንዲፈለግ ባዘዙት መሰረት የሰንደቅ ዓላማችንና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስራች በነበሩት ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ ሰብሳቢነት ከነጋሽ ገብረማሪያም የቀረበው ‹‹የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት›› የሚል ስያሜ ተወስዶ ለንጉሱ ከቀረበ በኋላ ተቀባይነት በማግኘቱ በ1960 ድርጅቱ በአዲሱ ስያሜ እንደገና ተቋቋመ፡፡

በዚህ ወቅት ድርጅቱ ተልዕኮውን በግልጽ ማሳየት ችሎ ነበር፡፡ ተልዕኮውም ‹‹ኢትዮጵያንና የተቀረውን ዓለም የሚመለከቱ ትክክለኛ የሆኑና የተሟሉ ዜናዎችን ሰብስቦ በሀገር ውስጥና በውጭም ሀገር እንዲታተሙና አንዲነገሩ ማቅረብ ሲሆን፣ ይህንኑ ለማከናወን ዜናዎችንና ዜና ነክ የሆኑትን ሁሉ ሰብስቦ በመገናኛ ዘዴዎች ለሚገለገሉ ድርጅቶችና የግል ሰዎች አስፈላጊና ተገቢ ነው ብሎ በሚወስነው ዋጋና ሁኔታ መሠረት ተስማምቶ እያስከፈለ ማሰራጨት›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ኢዜአ የንጉሳዊ መንግስቱን ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የሚያራምዱ ዘገባዎችን መስራት ዋንኛው የስራው ጥራት መመዘኛ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት ድርጅቱ በዋና ሥራ አስኪያጅ እየተመራ የኢንፎርሜሽን፣ የቴክኒክና መገናኛ እንዲሁም የአስተዳደር ዋና ክፍሎች ይዞ እንዲዋቀር ተደረገ፡፡ በኢንፎርሜሽን ዋና ክፍል ስር የብሔራዊ ልሳን (አማርኛ)፣ የእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ዜና ማዘጋጃ ክፍሎች፣ ዜና መመዝገቢያና የፎቶግራፍ ክፍሎች ተዋቀሩ፡፡ የሰው ኃይል ብዛቱም ከ120 በላይ ነበር፡፡

ምስል አንድ፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት (ኢዜአ) ነባር ህንጻ

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት በ1966 በተቀሰቀሰው አብዮት ከተወገደ በኋላ የመጣው ወታደራዊ መንግስት ኢዜአ ከ1970 ጀምሮ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር በመምሪያ ደረጃ እንዲተዳደር አደረገ፡፡ ድርጅቱ እንደገና ሲዋቀር ቴክኒክና ኦፕሬሽን፣ የአዲስ አበባ ዜና ዝግጅትና የክፍለሀገራት ዜና ዝግጅት እንዲሁም የውጭ ቋንቋዎች ዜና ዝግጅት የተባሉ አራት ዋና ክፍሎች እንዲኖሩትና አስተዳደርና ገንዘብ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን ተደረገ፡፡ በ1974 የድርጅቱ ሰራተኞች ብዛት 190 ደርሶ ነበር፡፡ ለ1975 የተመደበለት በጀትም 1.2 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ኢዜአ በወታደራዊው አገዛዝ ዘመን ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ጀምሮ በተማከለ የእዝ ሰንሰለት መዋቅር የደርግ ጽህፈት ቤት የእለት ተዕለት ክትትል ያልተለየው መረጃ ተቀብሎ የማሰራጨት ተግባር ማከናወን ዋነኛው ሥራው ሆኖ ቆይቷል፡፡ የሥርዓቱን ፖለቲካዊና ርዕዮተዓለማዊ ፍላጎቶች አገልግሏል፡፡

ኢሕአዴግ በ1983 ሥልጣን መያዙን ተከትሎ ኢዜአ የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን ያስቻሉ በርካታ ለውጦችን አድርጓል፡፡ ራሱን በቻለ ህንጻ ላይ የራሱ ዋና ጽህፈት ቤት እንዲኖረው ከመደረጉም በላይ አሰራሩን በማዘመን በኢትዮጵያ በኮምፒዩተር መረብ ከቅርንጫፎቻቸው ጋር ተገናኝተው መስራት ከቻሉ የመጀመሪያዎቹ መስሪያ ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ በ1992 ስራውን በጀመረው የማዘመን መርሀግብር ከአሥራ አምስት ቅርንጫፎቹ ጋርና ደንበኞቹ ከሆኑ መገናኛ ብዙሀን ጋር በኮምፒዩተር መረብ ተሳስሮ ለመስራት በቅቷል፡፡ የሰው ኃይሉንና የስራ አካባቢውን የማሰልጠንና የማዘመን ተከታታይ እርምጃዎች አድርጓል፡፡

ሆኖም ኢዜአ በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ የመንግስት የኮሚኒኬሽን ፖሊሲ ለውጦች ምክንያት ደጋግሞ መልሶ በመደራጀትና እየወደቀ በመነሳት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ ከነዚህም መካከል ጋዜጠኞቹ በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስር እንዲሆኑ ተደርገው ድርጅቱ በዝቅተኛ የአስተዳደር መዋቅር ስር ዳግም እንዲደራጅ መደረጉ የሚጠቀስ ነው፡፡

በ2006 ደግሞ “የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ” በሚል ስያሜ እንደገና ተቋቁሟል፡፡ በዚህም አገራዊ መግባባት የመፍጠርና ገጽታን የመገንባት ተልዕኮዎች ተሰጥቶት ተጠሪነቱ የአስፈፃሚው አካል ለሆነው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሆነ፡፡ በ2011 በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ በአዲስ መልክ ተደራጀ። ኢዜአ ዛሬ ላይ በማዕከልና በመላ አገሪቷ በሚገኙ 36 ቅርንጫፎች 400 ያህል ሰራተኞችን ይዞ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም ደንበኛ ብሎ ለለያቸውና ውል ላሰረላቸው 24 የመገናኛ ብዙኃን ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችን በቋሚነት በማቅረብና የመረጃ ምንጭ በመሆን እየሰራ ይገኛል። በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ እንግሊዝኛ እና አረብኛ ቋንቋዎች የተለያዩ ይዘቶችን እያቀረበ ነው፡፡

ምስል ሁለት፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት (ኢዜአ) አዲሱ ህንጻ

ኢዜአ በየሁለት ወሩ የሚታተም “ነጋሪ” የተሰኘ መጽሔትና የልዩ ልዩ ህትመቶች ባለቤት ነው፡፡ በ2014 በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ የ’ሚዲያ ኮምፕሌክስ’ን እያደራጀ በማጠናቀቁ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

 

ምንጮቻችን፡-

 

የምርመራ ጋዜጠኝነት ምንነት

Previous article

‹‹አሐዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ››

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply