የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል /MIRH/ 30 ነሀሴ 2014

በመቅደስ ደምስ

‹‹አዲስ ዘመን›› በኢትዮጵያ እድሜ ጠገቡና አንጋፋው ጋዜጣ ነው፡፡ ጋዜጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ለህትመት የበቃው ግንቦት 20 ቀን 1933 ነበር፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ለአምስት ዓመታት ከቆዩበት እንግሊዝ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ ከአንድ ወር በኋላ ነበር፡፡ የጋዜጣው መጠሪያም የተወሰደው ንጉሱ ከስደት መልስ በአዲስ አበባ አድርገውት ከነበረው ንግግር ነው፡፡ በንግግራቸው «ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው» ብለው ነበር፡፡

የጋዜጣው የመጀመሪያ እትም የፊት ገጽ ንጉሡ በአውቶሞቢል ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ የሚያሳይ ትልቅ ፎቶግራፍ ‹‹የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር›› ከሚል ጽሁፍ ጋር ይዞ ነበር፡፡ ጽሁፉ ‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለኢትዮጵያ አዲስ በሆነው ዘመን ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ እያመለከተ፤ ይልቁንም ሕዝብ ለአገሩ፣ ለመሪው፣ ለንጉሰ ነገሥቱና ለንጉሠ ነገሥቱም መንግሥት ማድረግ የሚገባውን እየገለፀ የበጎን ስራ መንገድ የሚመራ እንዲሆን ይህ ጋዜጣ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ተመሰረተ›› ይላል፡፡

የንጉሡንና አስተዳደራቸውን እንቅስቃሴ ለሕዝቡ ማሳወቅ፣ ሕዝቡ ንጉሱንና አስተዳደራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግል ማድረግ፣ ግንዛቤ ማስጨበጥና የዘመናዊነት ወኪል በመሆን ማገልገል የጋዜጣው ተልእኮዎች ነበሩ፡፡

በወቅቱ በፕሬስና መረጃ ቢሮ ስር ይተዳዳር የነበረው አዲስ ዘመን የመጀመሪያ አርታኢ አምደ ሚካኤል ደሳለኝ ነበሩ፡፡ በጊዜው ትክክለኛ የሥራ መዋቅር የተዘጋጀ ስላልነበር የጋዜጣው የዝግጅት ሥራ ለመጀመሪያዎቹ በርካታ ዓመታት በበጎ ፈቃደኞች የሚከናወን ነበር፡፡ ዘጋብያኑና አርታኢያኑ ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ  ስልጠና አልነበራቸውም፡፡ አብዛኞቹ በጽሁፍ ችሎታቸው ከቤተ-ክርስቲያን የተመረጡ ነበሩ፡፡

ጋዜጣው ሲጀመር እለታዊ ነበር፡፡ ሆኖም ከቆይታ በኋላ የሰኞ እትሙ እንዲቀር ተደረገ፡፡ በይፋ የሰኞ እትሙ ከመቅረቱ በፊት አልፎ አልፎ እሁድ ቀን ህትመቱ ይቋረጥ ነበር፡፡

ጋዜጣው ሲጀመር ይወጣ የነበረው እያንዳንዱ ገጽ በሶስት አምዶች ተከፍሎ በአራት ገጾች ከተለመደው የጋዜጣ መጠን ባነሰ መጠን ነበር፡፡ ያም 28 ሴንቲ ሜትር በ28 ሴንቲ ሜትር በሆነ ወረቀት ነበር፡፡

ለመጀመሪያዎቹ ወራት የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ህትመት የሚሰራው ጦር ሀይሎች ህትመትና ስቴሽነሪ አገልግሎት (Directorate of Army Printing and Stationery Service.) ነበር፡፡ ቆይቶም ህትመቱ ዛሬ ድረስ እየታተመ ወደሚገኝበት ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ተዘዋወረ፡፡

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 1938 የሚታተምበትን ወረቀት ቁመትና ወርድ መጠን ከፍ አደረገ፡፡ የጣሊያን ወራሪ ኃይል ድል ተነስቶ ከኢትዮጵያ የወጣበት አምስተኛ ዓመት ሲከበር ጋዜጣው የገጾቹን ብዛት ወደ ስምንት ከፍ አደረገ፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ወደነበረበት አራት ገጾች ተመለሰ፡፡ ጋዜጣው ለረዥም ጊዜ ይዞ የቆየውን ቅርጽ የያዘው በ1953 ነበር፡፡

ጋዜጣው በመጀመሪያ ዜና፣ ርዕሰ አንቀጽ እና ቋሚ አምድ አልነበረውም፡፡ ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እንደ ግብርና እና ብሄራዊ ልማት የመሳሰሉ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት በቋሚነት በሳምንት አንድ ጊዜ የሚታተምበት አምድ ተጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የማህበረሰቡን ትኩረት ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ የግብርናው አምድ ያልተማረው የሀገሪቱ ገበሬ በቀላሉ በሚረዳው መንገድ የሚዘጋጅ ስላልነበር ከሁለት ዓመት በላይ መቆየት አልቻለም፡፡ ልማትና እድገት የሚለው አምድም በተመሳሳይ ቆይታው ለሁለት ወራት ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ጋዜጣው የንግድ መረጃና ማስታወቂያዎች፣ የተለያዩ ድንጋጌዎችንና ህግጋትን ያካትት ነበር፡፡

ቆይቶ እንደ ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ››፣ ‹‹ለትዝብት ያህል››፣ ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ››፣ ‹‹እሁድ እንዴት አለፈ››፣ ‹‹አዲስ አበባ በየእለቱ›› የመሳሰሉ ተወዳጅነትን ያገኙ በርካታ መሰናዶዎችን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ በመዝናኛ አምዱ ቀልዶች፣ ግጥሞችና ‹‹ከእርስዎ ለእርስዎ›› የሚል የጥያቄና መልስ ይዘት ያለው የመዝናኛ አምዶች ነበሩት፡፡ ከጋዜጣው ጋዜጠኞች መካከል ጳወሎስ ኞኞ፣ በአሉ ግርማ፣ ብርሀኑ ዘርይሁን፣ ማሞ ውድነህና ሌሎችም ይገኙበት ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ከእድሜ ባለጸጋነቱ ባሻገር በሀገሪቱ ብቸኛው እለታዊ ጋዜጣ በመሆን የመሪነቱን ስፍራ ይዞ ይገኛል፡፡ ‹‹ብዕራችን ለኢትዮጵያ ህዳሴ ይተጋል!›› የሚል መፈክር ይዞ የመንግስትን አቋም የሚያንጸባርቁ እና የተለያዩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዜና ዘገባዎችን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ‹‹ነጻ ሃሳብ›› የተሰኘ አምድም አለው፡፡

 

ምንጮቻችን፡

ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

Previous article

ሀሰተኛ መረጃና እውነትን የማጣራት ፈተና

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply