የግል መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/14 ሀምሌ 2014
በንግስት በርታ
አዲስ አድማስ በአድማስ የማስታወቂያ ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ በ1992 የተቋቋመ ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው፡፡ የጋዜጣው የመጀመርያው እትም ለአንባቢዎች የደረሰው ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር። ጋዜጣው ከሁለት አሥርት በላይ ያለማቋረጥ ከአንባብያን በመድረስ ከሚታወቁት ጥቂት የግል ጋዜጦች አንዱ ነው፡፡
በሥራ አስኪያጇ ገነት ጎሳዬ እና በዋና አዘጋጁ ነቢይ መኮንን የሚመራው አዲስ አድማስ ህብረተሰብ፣ ፖለቲካ፣ ንግድ፣ ምጣኔሀብት፣ ጤናና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን የሚያካትቱ ዘርፈ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዘገባዎችን ለአንባቢ ከማቅረቡም በላይ ለባህል፣ ኪነጥበብና አዝናኝ አርዕስት ትኩረት ይሰጣል።
አዲስ አድማስ ለንባብ፣ ለባህልና ለኪነጥበብ የሚሰጠው ትኩረት ከሌሎች ጋዜጦች በተለይ የሚታወቅበት ባህሪው ነው፡፡ ከፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሂሶች በተጨማሪ በፈጠራ ጭብጦች ላይ የሚያተኩሩ የደራሲያን፣ ገጣሚያንና የልቦለድ ሀያስያን መጣጥፎችና ሥራዎችን ያስተናግዳል፡፡ በሙዚቃ ስራዎች ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀርባል፡፡ ወጥና ትርጉም አጫጭር ልብወለዶችን ያስነብባል፡፡ የኪነጥባባዊ ዝግጅቶችን በመጠቆም አዳዲስ መጻህፍትና የኪነጥበብ ሥራዎችን ያስተዋውቃል።
የአዲስ አድማስ መሥራችና ባለቤት ታህሳስ 6 ቀን 1997 ከዚህ አለም በሞት የተለየው ጋዜጠኛ አሰፋ ጎሳዬ ነበር። አሰፋ ጋዜጣውን ልዩ በሆነ የይዘት ጣዕም ከፍ ያለ የሙያ ደረጃ የሚታይበት የህኅመት ውጤት የማድረግ ራዕይ ነበረው፡፡ ጋዜጣው ያንን የላቀ ራዕይ በጥረትና በጽናት እውን ለማድረግ ይሰራል፡፡
ጋዜጣው ከወረቀት ህትመት በተጨማሪ በድረገጹ https://www.addisadmassnews.com/ ለዲጂታል አንባቢዎቹ እየደረሰ ነው፡፡ ለተከታታዮቹ አማራጩን በማስፋት በዩትዩብ አድራሻ https://www.youtube.com/c/AddisAdmasstube?sub_confirmation=1 እየቀረበ ነው፡፡
ምንጭ፤
- አዲስ አድማስ ጋዜጣ ድረገጽ https://www.addisadmassnews.com/
- ልዩ ልዩ ጥናቶች
Comments