የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/26 ግንቦት 2014

በመቅደስ ደምስ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ጋዜጣ “አእምሮ” ነው፡፡ ጋዜጣዋ ታትማ ለህዝብ መድረስ የጀመረችበት እርግጥ የሆነው ቀን ላይ አለመስማማቶች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ የመረጃ ሚኒስቴር፣ በ1966 የኢትዮጵያ የህዝብ መገናኛ ዘዴዎች (Ethiopian mass communication system) ታሪክን በተመለከተ ባወጣው ህትመት እንደገለጸው፣ አዕምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመችው ከዛሬ 122 አመታት በፊት በፈረንጆቹ 1900 መሆኑን ይገልጻል፡፡

ዘወትር ቅዳሜ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለአንባቢያን ትደርስ የነበረችው የአእምሮ ጋዜጣ፣ አማርኛ ለአንባቢያን መድረሻ ቋንቋዋ ነበር፡፡ ይህም በአፍሪካ፣ በአህጉሪቱ ቋንቋ በመዘጋጀት የመጀመሪያዋ ዘመናዊ ጋዜጣ እንዳደረጋት ይነገራል፡፡

ጋዜጣዋ መጠሪያዋን ንጉሱ ዓጼ ምኒሊክ ራሳቸው እንደሰጧት ይነገራል፡፡ በወቅቱ እንድርያስ ኢ ካቫዲያ (Andreas E. Kavadia.) የተሰኙ ግሪካዊ ነጋዴ ለንጉሱ የቅርብ ሰው እንደነበሩ ይነገራል፡፡ እኚህ ነጋዴ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር ይችሉ ነበር፡፡ አማርኛን መናገር ብቻ ሳይሆን ማንበብና መጻፉንም ጠንቅቀው በማወቃቸው የአእምሮ ጋዜጣ አርታኢ በመሆን ጋዜጣዋ በኅትመት መልክ ወደ አንባቢያን እንድትደርስ አድርገዋል፡፡

የአአምሮ ጋዜጣ በመጀመሪያ በዐራት ገጾች በ24 ኮፒዎች ለንባብ የበቃች ስትሆን፣ አብዛኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች በቤተ-ክርስቲያንና በቤተ-መንግሥቱ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ነበሩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ንጉሱ ዓጼ ምኒሊክ በአንድ ሶሪያዊ ነጋዴ አማካኝነት የኅትመት ማሽን ወደ ሀገር ቤት አስመጥተው የህትመቱን ብዛት ወደ 200 ከፍ እንዲል አደረጉት፡፡

ራሳቸው ንጉሱ ከጋዜጣዋ አንባቢያን መሐከል አንዱ ነበሩ፡፡ ታዲያ ኃይለ ማርያም ሰራቢዮን የተባሉ የንጉሱ ሰው ዘወትር ቅዳሜ ጋዜጣዋን ለንጉሱ ያነቡላቸው እንደነበር ምንጮች ይናገራሉ፡፡

አእምሮ ከፈረንሳይ ጋዜጦች ወደ አማርኛ የተተረጎሙ በርካታ ዜናዎችን አካታ ትይዝም ነበር፡፡ ከልዩ ልዩ ዜናዎችና ሌሎች ይዘት ካላቸው ጽሑፎች ባሻገር ዜጎች ማወቅ ያለባቸው መረጃዎች እና የንግድ ማስታወቂያዎች አብረው ይታተሙ ነበር፡፡ ታዲያ እነኚህ ማስታወቂያዎች የሚታተሙት በአማርኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ነበር፡፡ ይህም የሆነው በወቅቱ በአዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ ጥቂት ፈረንሳዊያንን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡

ፋሽስት ጣሊያን አዲስ አበባን ለመውረር የተቃረበበት ወቅት የአእምሮ ጋዜጣ እድሜ ማክተሚያ ሆነ፡፡ ፋስሽት ጣሊያን አዲስ አበባን ለመውረር ሦስት ሳምንታት ሲቀሩት፣ ከ28 አመታት የሥራ ቆይታ በኋላ ማለትም ሚያዚያ 3፣ 1928 ጋዜጣዋ ሥራዋን አቆመች፡፡ ሀገሪቱ በወቅቱ የነበረችበት አለመረጋጋት ደግሞ ለጋዜጣዋ መቅረት ምክኒያት ነበር፡፡

ምንጮቻችን:-

Dr. Mesert chekol, 2013, The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia.

አእምሮ – The First Newspaper in Ethiopia in Amharic

የኢ ቢ ኤስ (EBS) ቴሌቭዥን ዘገባ

Previous article

አፍሪካ በመገናኛ ብዙኃን የቢዝነስ ዘገባ ዉስጥ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply