የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

አማረ አረጋዊ፡ ሦስት ዓስርታት ዓመታትን የተሻገረ ስኬታማ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ጉዞ

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 24 ሰኔ 2014

በአቢ ፍቃዱ

በእርሱ ሀሳብ አመንጪነት ተጀምረው ከዘለቁ የመዝናኛ ዝግጅቶች አንዱ የእሁድ ከሰአት በኋላው ኢቲቪ-120 ፕሮግራም ተጠቃሽ ነው፡፡

የመሰናዶው መጀመር የወቅቱ የመዝናኛ ጋዜጠኞች ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡና አቅማቸውን እንዲጠቀሙ በር የከፈተ አጋጣሚ ነበር፡፡ አማረ ጋዜጠኛን ነጻ በማድረግ ስለሚያምንና ስለሚያበረታታ የኢቲቪ 120 መሰናዶ ሙያና ባለሙያ ተጣጥመው የተገናኙበት ተሞክሮ ነበር፡፡ መሰናዶው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት ለማግኘት የበቃው ከበስተጀርባው በነበረው በእርሱ ሙያዊ ብስለት መነሻነት ነበር፡፡

ለመሰናዶው እነማን ምን ሊሰሩ ይችላሉ? የሚለውን ጥያቄ ቀድሞ ሲያስብበት ቆይቷል፡፡ የቴሌቪዥን ዝግጅቱ ግብ ተደራስያንን ማዝናናት ስለነበር ኮሜዲውን እንግዳዘር ነጋ፣ ደረጀ ሀይሌ፣ ሀብቴ ምትኩና ሌሎችም ባለተሰጥዖዎች ቢይዙት የተሻለ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበር፡፡

በያኔው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መምሪያ ኃላፊና የአሁኑ የሪፖርተር ጋዜጣ መስራችና ባለቤት አማረ አረጋዊ ሦስት ዓስርታትን የዘለቀ ስኬታማ የጋዜጠኝነት የሙያ ጉዞ ተጉዟል፡፡

አማረ ታህሳስ 29 ቀን 1947 ዓ.ም መቐለ ተወለደ፡፡ እናቱ ወይዘሮ ዘነበች ገብረማሪያም፣ አባቱ አቶ አረጋዊ ወልደ ኪዳን ይባላሉ፡፡

በመቐለ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ይማር በነበረበት ጊዜ የትያትርና የስነ-ጽሁፍ ፍቅር ያደረበት አማረ በ1955 ዓ.ም. ገና የ8 ዓመት ብላቴና ሳለ ከጓደኞቹ ጋር አንድ አነስተኛ መጽሐፍ ጽፎ ነበር፡፡ በጊዜው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መቐለን ሲጎበኙ እነ አማረ የጻፉትን መጽሐፍ አይተው ‹‹በዚሁ ቀጥሉ›› ብለው አበረታቷቸው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በመቐለ ትምህርቱን የተከታተለው ታዳጊው አማረ፣ በ1959 ዓ.ም. ባገኘው ነጻ የትምህርት እድል የጄኔራል ዊንጌት ተማሪ ለመሆን ቻለ፡፡ በጊዜው ወደ ትምህርት ቤቱ የሚገቡ ተማሪዎች ከየክፍለ-ግዛቱ የተውጣጡ በትምህርት ውጤታቸውም ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ነበሩ፡፡ አማረ ከእነዚህ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ስለነበር በ12 ዓመት እድሜው የጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተማሪ ለመሆን በቃ፡፡

በልጅነቱ ያደረበትን የስነ-ጽሁፍ ዝንባሌ የሚያጎለብትባቸው ሁኔታዎች በዚህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጋጥመውታል፡፡ በዊንጌት የተውኔት ክበብ ውስጥ ልዩ ልዩ ተውኔቶችን በመስራት በተለይ ‹‹ትዌልቭዝ ናይት›› በተሰኘው የዊልያም ሼክስፒር ቴአትር ላይ በመተወን ጭምር ተሳትፏል፡፡

በ1962 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በዊንጌት የተማሪዎች መጽሄት ላይ በእንግሊዝኛ የጻፈውን ጽሁፍ በማየት የታዳጊው የቋንቋ ክህሎት ምን ያህል የዳበረ መሆኑን ብዙዎች ተገንዝበው ነበር፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባጠናቀቀበት ዓመት እንግሊዝ አገር ነጻ የትምህርት እድል አግኝቶ ሄደ፡፡ እዚያም ለተወሰኑ ዓመታት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ ከ1967-1983 ዓ.ም. በፖለቲካ ትግል ውስጥ በመቆየት የተለያዩ መጽሔቶችን በማዘጋጀት አገልግሏል፡፡ ከ1983-1985 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም ከ1985-1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ በመሆን አገልግሏል፡፡

አማረ አረጋዊ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ኃላፊ በነበረ ጊዜ በርካታ የለውጥ ርምጃዎችን በመውሰድ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘርፍ የማይዘነጋ ውለታ ውሏል፡፡ በተለይም በዜና፣ በመዝናኛና በቋንቋዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ፣ ተመልካችን የሚመጥኑ፣ ፈጠራ የታከለባቸው ዝግጅቶች አየር ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ ‹‹የእኔ ዋና ግብ አዳዲስ መዋቅሮች እንዲዘረጉና ሳቢ የፕሮግራም ፎርማቶች እንዲቀረጹ ማድረግ ስለነበር ይህንኑ እውን ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ›› ይላል፡፡

ምስል አንድ፡ አማረ አረጋዊ

አማረ ከ1983-1985 ዓ.ም. ለሁለት ዓመታት ሰርቶ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታው እንዳበቃ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያገኘውን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ኢዜአም ላይ የአሰራር ማሻሻያ ለማድረግ ማሰቡ አልቀረም፡፡ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመንግስትን ሀሳብ ብቻ ከማስተናገድ ባሻገር የህዝብ የዜና አገልግሎት መሆን የሚችልበትን ስልት ያውጠነጥን ነበር፡፡

ሆኖም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የራሱን ብዙሀን መገናኛ ተቋም የማቋቋም ህልሙ በመበርታቱ በ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኃላፊነቱን በመልቀቅ ሚዲያና ኮምኒኬሽን ሴንተር (MCC) የተባለ ድርጅቱን አቋቋመ፡፡ በጊዜው ወ/ሮ መአዛ ብሩ እና ባለቤቷ አቶ አበበ ባልቻ አንደኛውን ድርሻ ይዘው ከአቶ አማረ ጋር ሪፖርተር ጋዜጣን በ1987 ዓ.ም. በጋራ መሰረቱ፡፡

“ነጻ ፕሬስ፣ ነጻ ሀሳብ፣ ነጻ መንፈስ” የሚለውን ትልቅ እሳቤ ይዞ የተነሳው ሪፖርተር ጋዜጣ በመጀመሪያው እትሙ በአሥር ሺህ ቅጂዎች ነበር የወጣው፡፡ ተዋናይ እና ጠበቃ አበበ ባልቻ እስከ 1990 ዓ.ም. ድረስ የሪፖርተር የ50 ከመቶ ባለድርሻ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መአዛ ብሩ ሬድዮ በመጀመሯ ሙሉ በሙሉ የባለቤትነት ድርሻው የአቶ አማረ ሆነ፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ ሙያዊ ክህሎት የታየበት ገና ከጅምሩ ነበር፡፡ ጠንካራና ጥልቅ ዜና ዘገባዎቹ፣ ‹‹ቆይታ›› የተሰኘው የቃለ-ምልልስ አምድ፣ ርእሰ-አንቀጽ እና ሌሎቹም የጋዜጣው አምዶች በቅርፅና በይዘታቸው ከፍ ያለ የጋዜጠኝነት ደረጃን ማሳየት ችለዋል፡፡ ሪፖርተር ከኢህአዴግ ጋር ንክኪ አላቸው ከሚባሉ የመገናኛ ብዙሀን ውጤቶች አንዱ ነው ብለው የሚሟገቱ ተቺዎች እንደነበሩት ሁሉ የሚዛናዊ ጋዜጠኝነት ምሳሌ የሚያደረጉት በርካቶች ናቸው፡፡

አማረ ነጻ ፕሬስ በኢትዮጵያ ማበብ አለበት ብሎ ያምን ስለነበረ ለውጥ እንዲመጣ ታግሏል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ 2ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ‹‹አሁንም ነጻ ፕሬስ፣ ነጻ ሀሳብ፣ ነጻ መንፈስ›› በሚል ርእሰ-አንቀጽ ይህንኑ የነጻ ፕሬስ አቋሙን በግልጽ አሳይቷል፡፡ በዚህ ወቅት ከሪፖርተር አማርኛው እትም በተጨማሪ የእንግሊዝኛው ዘ ሪፖርተር እንዲሁም ሪፖርተር መጽሄት መታተም ጀመሩ፡፡

አማረ በ1989 ስለነጻ ፕሬስ በጻፈው ርእሰ-አንቀጹ ‹‹ለብቻ ተሁኖ ነጻ ፕሬስ፣ ነጻ ሀሳብ፣ በአገራችን ማስፈን ከቶ አይቻልም›› ብሏል፡፡ መገናኛ ብዙሀን መጠናከር እንዳለባቸው በአጽንኦት ተሟግቷል፡፡ በጊዜው መንግስት የኢንፎርሜሽን ፖሊሲ ማውጣት እንዳለበት በብርቱ አሳስቧል፡፡ ‹‹መንግስት የራሱ መገናኛ ብዙሀን ብቻ እንደሚጠቅሙት ማሰብ የለበትም፡፡ የግል መገናኛ ብዙሀንም ሊኖራቸው የሚችለውን የጎላ ድርሻም ማስተዋል አለበት›› ሲል ጽፏል፡፡

እርሱ በሚመራው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ከአንድ መቶ ሀምሳ ሺህ በላይ ዜና እና ጽሑፎች የተስተናገዱ ሲሆን ሁሉም በሚባል ደረጃ የህዝብን የመረጃ ጥማት ከማርካት አንጻር የሚሰናዱ ነበሩ፡፡

ምስል ሁለት፡ አማረ አረጋዊ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሽልማት ሲቀበል

ለዚህ አንጋፋ የብዙሀን መገናኛ ባለሙያ በመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤትና ዋቤ የአሳታሚዎች ማህበር በ2009 ዓ.ም. እውቅና ሰጥተውታል፡፡ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የእውቅና ስጦታውን አበርክተውለታል፡፡ በ2011 ደግሞ ‹‹የበጎ ሰው›› የመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ አማረ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነው፡፡

 

ምንጮች

ከታሪኩ ባለቤት ከአቶ አማረ አረጋዊ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ

ተወዳጅ ሚድያና ኮሙኒኬሽን

ልዩ ልዩ ጥናታዊ ሰነዶች

የስልጠና ምዝገባ ጥሪ ለጋዜጠኞችና ለኢንተርኔት አምደኞች

Previous article

ሪፖርተር ጋዜጣ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply