የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

‹‹አሐዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ››

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 05 ነሐሴ 2014

በብርሃኑ ቸኮል

አሀዱ መስከረም 1 ቀን 1917 ዓ.ም በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ተወለደ። በሦስት ዓመቱ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ የኔታ መንግሥቱ ከሚባሉ መምህር ዘንድ ፊደል ቆጠረ፤ ዳዊት ደገመ። ከዚያም በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሲስ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርቱን ቀጠለ።

አሀዱ በልጅነቱ አባቱን በሞት ስላጣ ‹ሳቡሬ› የተባሉ ፈረንሳዊ ግለሰብ እገዛ ያደርጉለት ነበር፡፡ መጠሪያውም ‹አሀዱ ሳቡሬ› ሆነ። በ1928 የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ምክንያት አሀዱ ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ ቆይቶም የጣሊያኖች ትምህርት ቤት ገብቶ ለሁለት ዓመታት ያህል ከተማረ በኋላ በ13 ዓመቱ አስተርጓሚ ሆኖ መሥራት ጀመረ። እስከ 1933 ድረስ በዚህ ሥራው ቆይቷል።

ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላም የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት ሲቋቋም የግብር ሰብሳቢ ክፍል ሠራተኛ ሆኖ ተቀጠረ። በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የነበሩ አውራጃዎችን እየተዘዋወረ የሚቆጣጠር ክፍል (ኢንስፔክሽን ክፍል) በተቋቋመበት ወቅት የክፍሉ ጸሐፊ ሆነ።

በ1936 በጅቡቲ በነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በጸሐፊነት ተመድቦ መሥራት ጀመረ። የአሀዱ የጅቡቲ ቆይታው የፈረንሳይኛ ችሎታውን ለማሻሻል፣ ለማንበብና ከፈንሳዮች ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማሻሻል ጠቅሞታል።

አሀዱ ከጅቡቲ መጣጥፎችን ለጋዜጦች ይልክ ነበር። ለአብነት ያህል ‹‹አዲሱ ሥራችን›› በሚል ርዕስ የተጻፉ ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላ ኢትዮጵያውያን ማድረግ የሚገባቸውን ነገሮች የሚመለከቱ ይገኙበታል፡፡ ይልካቸው በነበሩት መጣጥፎች መነሻነት በ1942 ወደ ጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት ተዛወረ። መሥሪያ ቤቱ ከ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ‹ማስታወቂያ ሚኒስቴር› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

አሀዱ በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት በጋዜጣ ጽሑፍ አዘጋጅነት የ‹አዲስ ዘመን› እና የ‹ሰንደቅ ዓላማችን› ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ የነበሩት የብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ረዳት ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ አሀዱ በሬዲዮው ዘርፍም የዜናና ሐተታ አንባቢና አዘጋጅ ሆኖ ይሠራ ነበር።

በኋላ ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ዘርፎች የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ጎላ ባለ መልኩ የሚያቀርብ ጋዜጣ እንዲጀመር ታስቦ ሳምንታዊው ‹የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ› ጋዜጣ በ1944 በአማርኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ሥራውን ሲጀምር አሀዱ የአማርኛው ክፍል ኃላፊና ዋና አዘጋጅ ሆነ። ጋዜጣው በየሳምንቱ ዓርብ ነበር የሚታተመው፡፡

ጋዜጣው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ወሬዎች እንዲሁም ሌሎቹ ጋዜጦች የማይደፍሯቸውን ጉዳዮች ይዞ ይወጣ ስለነበር ተወዳጅ ሆነ። የሹማምንት ነቀፌታና ቅሬታም ነበረበት፡፡

አሀዱ በ‹ዛሬዪቱ ኢትዮጵያ› ጋዜጣ ያወጣቸው የነበሩት ዘገባዎች ተወዳጅ በመሆናቸው ለሱም አድናቆትን አትርፈውለታል፡፡ ከተሰጡት የአድናቆት መግለጫዎች መካከል የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት የስመጥሩ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ‹‹አሀዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ›› የሚለው ታዋቂ አገላለፅ ይገኝበታል፡፡

አሀዱ እስከ 1953 ድረስ ለ11 ዓመታት በጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት ከሰራ በኋላ በዚያው ዓመት የፖለቲካ ታዛቢ ሆኖ የእርስ በእርስ ግጭት ወደነበረባትና ኢትዮጵያም ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደላከችባት ኮንጎ አመራ። በ1953 በክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ በብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ መሪነት የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ ጀኔራሉ ተይዘው ለፍርድ ቀረቡ። አሀዱም የፍርድ ሂደቱን በጋዜጣና በሬዲዮ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያሳውቅ በመታዘዙ ከኮንጎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

አሀዱ የፍርድ ሂደቱን ለአንድ ሳምንት ያህል እየተከታተለ በዝርዝር አቀረበ። ሕዝቡም ‹‹የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣን እየተሻማ ገዝቶ አነበበ። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ሹማምንቱን ባለማስደሰቱ አሀዱ ‹‹ወደ ፍርድ ቤት ድርሽ እንዳትል›› ተባለ። በግዞትም ወደ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ተልኮ ለአምስት ወራት ያህል በቁም እስረኛነት ተቀመጠ። በኋላም በምህረት የግዞት ጊዜውን ፈፀመ።

አሀዱ ከግዞት መልስ በጋዜጠኝነት አልቀጠለም፡፡ በመጀመሪያ በሶማሊያ ቀጥሎም በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ሆኖ እስከ 1966 ድረስ አገለገለ። ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የሶማሊኛ፣ ፈረንሳይኛና ኢጣልያኛ ቋንቋዎች ችሎታው ክፍለአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ እውቀቱ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ በየካቲት 1966 የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ ተሰናብቶ የልጅ እንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ ሲቋቋም አሀዱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆኖ ተሾሙ።

 

አሀዱ ሹመቱን የተቀበለው በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት እንዲታወጅና የማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አሠራርም እንደሚሻሻል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንንን ቃል አስገብቶ ነበር። አሀዱ ከማለፉ ጥቂት ወራት በፊት ለሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ለመዓዛ ብሩ ቃለመጠይቅ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፤ ‹‹…ሹመቱን የምቀበለው በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት የሚታወጅ ከሆነና ምንም አላንቀሳቅስ ብሎ ያስቸገረው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚሻሻል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ሹመቱን አልቀበልም፡፡…››

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የነበሩት ልጅ እንዳልካቸውም ‹‹የተማርኩት የጋዜጣ ነፃነት ባለበት አገር ነው። የፕሬስ ነፃነት ለአንዲት አገር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተማርኩበት አገር አይቻለሁ፡፡…›› በማለት የጠየቀው እንደሚፈጸም ቃል በመግባት ሹመቱን እንዲቀበል አግባቡት።

አሀዱ የጋዜጣ መስሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን ሰብስቦ ሕዝባዊ ቁጣው እየበረታ ስለመጣ በተለመደው መንገድ መጓዝ እንደማይበጅና በዘርፉ ያሉትን ችግሮች መለየት እንደሚያስፈልግ በመንገር ሥራውን ጀመረ። ሆኖም ሹማምንቱ በተለመደው መንገድ ከመጓዝ ውጭ ለሌላ ሀሳብ ቦታ ባለመስጠታቸውና በልጅ እንዳልካቸው የተገባለት ቃል ሊፈፀም ስላልቻለ አሀዱ ኃላፊነቱን ለቆ ወደ ጅቡቲ ተመለሰ።

ከወራት በኋላ ንጉሱን ከሥልጣን ካስወገደው ደርግ ሊቀ መንበር ሌተናንት ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አሀዱ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ሽግግሩን እንዲያግዝ ጥያቄ ቀረበለት፡፡  አሀዱ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የሐረርጌ ክፍለ ሐገር ዋና አስተዳዳሪ ሆነ። ከ11 ወራት የአስተዳዳሪነት አገልግሎት በኋላ እርሱ ‹‹በማላውቀው ምክንያት›› በሚለው ሰበብ ነሐሴ 1967 በቁጥጥር ሥር ውሎ እስከ መስከረም 1975 ድረስ ያለፍርድ ለሰባት ዓመታት ከታሰረ በኋላ ተፈታ። ከዚያም እስከ ህይወቱ ፍጻሜ እስከ ህዳር 2012 ድረስ ከቤተሰቦቹ ጋር በአሜሪካ ኖረ፡፡

አሀዱ ‹የዓለም መስተዋት› እና ‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፍፃሜና የደርግ አነሳስ› የተባሉ መጻህፍት ከማሳተሙም በላይ ያልታተመ ‹አሀዱ ሳቡሬ› በሚል ርዕስ የተጻፈ የግል ህይወት ታሪክ መጻህፍት ደራሲ ነው፡፡

ምንጮቻችን፡-

መዓዛ ብሩ– ሸገር ኤፍ.ኤም.102.1 የቅዳሜ ጨዋታ እንግዳ – አሀዱ ሳቡሬ- ታህሳስ 4፣ 2012

ሲሳይ አጌና– ኢሳት ቴሌቪዥን- የሳምንቱ እንግዳ ቃለመጠይቅ- አሀዱ ሳቡሬ- ህዳር 23፣ 2012

አዲስ ዘመን – ሐምሌ 2012

Chekol, Meseret. 2013. The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia. New York: University Press of America.

ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፡ የአፍሪካው አንጋፋ የዜና ድርጅት

Previous article

የጅማ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ሬድዮ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply