የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 13 ነሐሴ 2014
በመቅደስ ደምስ
ነጋሽ ገብረማርያም ሀረርጌ ውስጥ ጨርጨር አውራጃ ሀብሮ ወረዳ ልዩ ስሙ መቻራ በሚባል አካባቢ በ1917 ተወለደ፡፡ ነጋሽ ፊደል የቆጠረው በቄስ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ትምህርቱንም ዳዊት እስከመድገም አድርሷል፡፡ ከእዛም ታላቅ ወንድሙን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብቶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡
በመቀጠልም በመምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከሰለጠነ በኋላ ለአንድ አመት ጅማ ውስጥ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ ከጅማ መልስ አዲስ አበባ ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ገባ፡፡ በወቅቱ ነጋሽ የተመደበው በሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከልጅነት እድሜው ጀምሮ የወንድሙን አሰፋ ገብረማሪያምን ፈለግ ተከትሎ ጸሀፊ የመሆን ፍላጎት ነበረው፡፡ (አሰፋ ከፋስሽት ጣሊያን ወረራ በኋላ የተጻፈው ‹‹እንደወጣች ቀረች›› የተሰኘ ልብወለድ ጸሀፊ ነው፡፡)
ለስነ ጽሁፍ ያደላ የነበረው ነጋሽ በተመደበበት የሳይንስ ትምህርት ዘርፍ መቀጠል አልፈለገም፡፡ እናም ትምህርቱን አቋርጦ ስራ መስራት ጀመረ፡፡ በኋላም የወደብ አስተዳደር ስልጠና ለአንድ አመት ወስዶ በምጽዋ ወደብ ስራ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ከስነ ጽሁፍ የሚያርቀው ሲሆን ትቶት ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ በመጨረሻ ምኞቱ ሰምሮ በአሜሪካን ኤምባሲ በትርጉም ሰራተኝነት ተቀጠረ፡፡
በመስሪያ ቤቱ የሚያገኛቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገራት የህትመት ውጤቶች የዕውቀት አድማሱን ለማስፋት እድሉን ሰጡት፡፡ ቀስ በቀስ የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍ ለጋዜጦች መላክ ጀመረ፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ መስራቱ በስነ ጽሁፍ ዙሪያ ነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኝ አስቻለው፡፡ አሜሪካ በሚገኘው ሞንታና ስቴት ዩኒቨርስቲ ለሁለት አመታት የጋዜጠኝነት ኮርስ ወሰደ፡፡ ይህም ዘመናዊውን የጋዜጠኝነት ሙያ በተመለከተ ስልጠና ከወሰዱ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡
ነጋሽ ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት ሲመለስ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ተጨማሪ ኮርሶችን በመከታተል የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ ቆይቶም ወደ አሜሪካ በመመለስ ከሲራከስ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት ሁለተኛ ዲግሪውን ይዟል፡፡
በ1953 ከአሜሪካ ሲመለስ በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ተቀጠረ፡፡ ቆይቶም በብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሀንስ ዋና አዘጋጅነት የሚመራው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ ሆነ፡፡ በአዲስ ዘመን በቆየባቸው አራት ዓመታት ጋዜጣው ንጉሰ ነገስት አጼ ሀይለስላሴን ከማሞገስ ባሻገር የህዝብ ሀሳብና ችግሮች የሚተላለፍበት እንዲሆን በማድረግና ሙያዊ ይዘት እንዲኖረው ጥሯል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ወደ አምስት ቀን ዕለታዊ ህትመት እንዲያድግ ያደረገውም እሱ ነበር፡፡ በእንግሊዘኛው “Editorial” የሚባለውን በህትመት ሚዲያ ዘርፍ የህትመቱ አቋም ለሚንጸባረቅበት አምድ ‹‹ርዕሰ አንቀጽ›› የሚል አዲስ የአማርኛ አቻ ቃል የፈጠረው ነጋሽ ነበር፡፡ ነጋሽ በቤተ ክህነት ሰዎች ይመራ የነበረውን የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት ሙያ ለውጦ በትምህርትና እውቀት ተደግፈው መስራት ከጀመሩ ውስን ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበር፡፡
የሚያምንበትን ነገር ከመናገር ወደኋላ የማይለው ነጋሽ፤ ንጉሰ ነገስቱ ዙፋናቸውን የሚተካ ሰው አስበው እንደሆነ በዘዴ ጠይቋቸው ነበር፡፡ በወቅቱ በንጉሠ ነገሥቱ እና አልጋ ወራሻቸው መካከል አለመግባባት ስለነበር ጥያቄው በበርካታ ኢትዮጵያውያን ጭንቅላት ውስጥ የሚመላለስ ነገር ግን ማንም ደፍሮ የማይጠይቀው ነበር፡፡ ንጉሱም የነጋሽን ብልሀት የተሞላበት ጥያቄ ምላሽ የለኝም በሚል ጭንቅላታቸውን ነቅንቀው አለፉት፡፡ በርካቶች ነጋሽ ለጥያቄው ቅጣት እንደሚጠብቀው አስበው ነበር፡፡
ነጋሽ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን የህዝብ ሀሳብ በነጻነት የሚተላለፍባቸው መሆን አለባቸው የሚል የጸና አቋም ነበረው፡፡ ለአቋሙም በከፍተኛ ጫና ስር ሆኖ ታግሏል፡፡ በእዚህም ሳቢያ ከአለቆቹ ጋር በተደጋጋሚ ተጋጭቶ እስከ እስር የዘለቀ ፈተና አጋጥሞታል፡፡
ንጉሰ ነገስቱ ከዙፋናቸው ወርደው የደርግ መንግስት ስልጣን ሲይዝ አዲሱ መንግስት አዲስ ዘመን ጋዜጣን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት ነጋሽ በመቃወሙ ምክንያት ሹመት በሚል ሽፋን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዘዋውሮ የሬዲዮና ቴሌቪዥን መምሪያ ምክትል ኃላፊ እንዲሆን ተደረጎ ነበር፡፡ ደርግ የመምሪያውን ኃላፊ ንጉሴ ሀብተወልድን እስር ቤት ሲያስገባው ነጋሽ ቦታውን እንዲወስድ ቢጠየቅም ሳይቀበለው ቀረ፡፡ በምትኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነ፡፡ ኢዜአ ለሰባት ወራት ብቻ ካገለገለ በኋላ ከማርክሲስታዊ አመለካከት ጋር አልተዛመድክም በሚል የደርግ መንግስት ከሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያው አርቆ ወደ ከተማ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት የስራ ክፍል መደበው፡፡ ከሁለት አመታት በኋላም ያለፍላጎቱ በ52 ዓመቱ ጡረታ እንዲወጣ ተደረገ፡፡
የጋዜጠኝት ሙያ እንዲጎለብት ብርቱ ፍላጎት የነበረው ነጋሽ ገብረማርያም ለተተኪዎች እውቀት በማስተላለፍ ስሙ በብዛት ይነሳል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የትርፍ ሰዓት መምህር ሆኖ ለአንድ ዓመት አገልግሏል፡፡ በመቀጠል የአያት ሪል ስቴት መጽሄትን ለሶስት ዓመታት አዘጋጅቷል፡፡
ነጋሽ ጡረታ ከወጣ በኋላም በጋዜጠኝነትና በህዝብ ግንኙነት ዙሪያ በርካታ ስልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ በኮሚዩኒኬሽንና ተጓዳኝ ርዕሶች ላይ በሚመክሩ በርካታ ፓናሎችና ሲምፖዚየሞች ላይ ቀርቦ ንግግር አድርጓል፡፡ በጋዜጠኝነቱ ላበረከተው ላቅ ያለ አስተዋጽዖ በ1994 የስነ ጥበብና የመገናኛ ብዙሀን የሽልማት ድርጅት ‹‹የረጅም ዘመን አገልግሎት ኮከብ ጋዜጠኛ›› በሚል ሽልማት አበርክቶለታል፡፡ ነጋሽ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ የልቦለድና ቴአትር ደራሲም ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት መሰረታዊያንና መርሆች ላይ የሚያተኩር ‹‹ጋዜጠኛ መሆን እፈልጋለሁ›› የሚል መጽሀፉን ጨምሮ የተለያዩ ልቦለዶችንና ቴአትሮችን ደርሷል፡፡
ነጋሽ በኩላሊት መታወክ ሕክምና ሲከታል ቆይቶ ሀምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በ93 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ነጋሽ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡
ምንጮቻችን፡
Mesert Chekol. (2013). The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia. New York: University Press of America.
Ethiopian Literary Giants and their Works: Novel, Play and Journalism in Ethiopia (1850’s-1960’s) by Habtamu Girma Demiessie. (pp. 165-170)
https://www.ethiopiaobserver.com/2015/10/04/journalist-and-author-negash-gebre-mariam/
https://amharic.voanews.com/a/journalist-author-negash-gebere-mariam-7-18-2017/3949204.html
Comments