የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ብዙ ወንድማገኘሁ አለሙ:- በሁለት የፖለቲካ ዘመናት ውስጥ ያለፈ ጋዜጠኝነት

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 18 ሐምሌ 2014

በአቢ ፍቃዱ

ብዙ ወንድማገኘሁ ከቀኝ አዝማች ወንድማገኝ ዓለሙና ከወይዘሮ አበራሽ ደስታ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰንጋ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1940ዎቹ መጨረሻ ነበር የተወለደችው፡፡ የቅድመ መደበኛ ትምህርቷን በትውልድ አካባቢዋ ጎላ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ በቄስ ትምህርት ቤት ተማረች፡፡ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት መግባት ለእሷ ቀላል አልነበረም፡፡ ችግሩ አባትዋ “ሴት ልጅ የጸሎት መጽሐፍ ለማንበብ ፊደል መቁጠርና ዳዊት መድገም በቂዋ ነው” ብለው ስለሚያስቡ ነበር፡፡

አባቷ በነበራቸው አመለካከት ምክንያት ብዙ፤ የቤት ሙያ ስራ ላይ ብቻ እንድታተኩር ከማድረጋቸው በተጨማሪ ልጅነቷን ሳትጨርስ ሊድሯት ያስቡ ነበር፡፡ ሆኖም ታላቅ ወንድሟ አቶ አማረ የብዙ በልጅነት ለትዳር መሰጠትን በከፍተኛ ሁኔታ ከመቃወሙም በላይ ከአባቱ ጋር ከፍተኛ ጸብ ውስጥ ገባ፡፡ አልፎም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን እንድትከታተል አስፈላጊውን ሁሉ አሟላላት፡፡ በወንድሟ የተበረታታቸው ብዙ ትምህርቷን ገፋችበት፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በየነመርድ ትምህርት ቤት፣ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን በወቅቱ አባሃና ጂማ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአሁኑ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡

ብዙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ጋዜጣ የማንበብ ፍቅር ነበራት፡፡ በየአጋጣሚው የምታገኛቸውን ጋዜጦች ታነባለች፡፡ ጋዜጣ ማንበቧም የጽሑፍ ልምድ እንድታዳብር ረዳት፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ማዘንበል የጀመረችው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ለምታገኛቸው ምክር ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ ‹‹ጋዜጠኛ መሆን እፈልጋለሁ፤ ምን ማድረግ አለብኝ?››  እያለች ትጠይቅ ነበር፡፡

አንድ ቀን ወደ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በመሄድ ለደብዳቤዎች አምድ አዘጋጅ ‹‹ጋዜጠኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?›› የሚል ደብዳቤና ገንዝብ ይዛ ቀረበች፡፡ ገንዘቡን የያዘችው ጽሁፍ ለማውጣት ክፍያ የሚያስፈልግ መስሏት ነበር፡፡ አዘጋጁ አቶ ከበደ አምቢሳ ጽሁፉን በመቀበል ‹‹ጽሁፍ ለማውጣት ምንም ገንዘብ አይከፈልም፡፡ ይልቁንም ተሰጥኦው ካለሽ ጽሁፎችን እየጻፍሽ አምጪ” በማለት አበረታቶ መከራት፡፡

የመጀመሪያ ሙከራዋ የሆነው ጥያቄያዊ መጣጥፍ “ጋዜጠኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?” በአዘጋጁ ተቀባይነት በማግኘቱ በማግስቱ ጋዜጣው ላይ ታተመ፡፡ ይህ ጅማሬ ደግሞ ለብዙ ትልቅ እርምጃዎች መነሻ ሆናት፡፡ ከዚያም ትምህርቷን አስረኛ ክፍል ላይ አቁማ በምትጽፈው በእያንዳንዱ መጣጥፍ እየተከፈላት ለኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ መጻፍ ጀመረች። በዚህ ወቅት ተዋናይ የመሆን እድል አግኝታ በእድሜዋ ማነስ ምክንያት ሳይሳካላት በመቅረቱ ተቆጭታ ነበር፡፡ መቆጨቷን ግን በዝምታ አላቀበችውም፡፡ ይልቁንም ልጆች ከመድረክ መገለል የለባቸውም የሚል አንድ መጣጥፍ በጋዜጣ አወጣች፡፡ ለመጻፍ የተነሳሳችው አንድ ጃፓናዊ ሕጻን የሂሳብ ሊቅ ሆነ የሚል ዜና ጋዜጣ ላይ ካነበበች በኋላ ነው፡፡ በኋላም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ከማጀት እስከ አደባባይ” በሚል የሴቶች አምድን በማዘጋጀት በቋሚነት መስራት ጀመረች፡፡

“ከማጀት እስከ አደባባይ” አምድን ታዘጋጅ በነበረችበት ጊዜ ከጋዜጣው ምክትል አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ ጋር ነፋስ ስልክ አካባቢ በሴተኛ አዳሪነት ስለተሰማሩ ሴቶች ቁጥር እያደገ መሄድ ከተነጋገሩት በመነሳት ጋዜጠኛ መሆኗን ደብቃ ስለሴቶቹ ህይወት በሥፍራው ተገኝታ የጻፈችው ምልከታዊ ዘገባ ለሙያው የነበራትን እምቅ አቅም ያሳየችበት ነበር፡፡ ብዙ ስለተሞክሮዋ ስትናገር ‹‹ማታውኑ ወደ ጭፈራ ቤት አመራሁና እዛ ከሚሰሩት ሴቶች መካከል አንዷን ቦታው ላይ ስራ ለመጀመር አስቤ እንደመጣሁ በመንገር ቀረብኳት፡፡ እሷም አዝናልኝ ባልገባበት እንደሚሻል ምክር ሰጠችኝ፡፡ እኔ ግን ያን ምሽት ሁሉንም ነገር እዛው ሆኜ አየሁ፡፡›› ብላለች፡፡ ከዛም “አንድ ሌሊት በዳንስ ቤት” የሚል ዘገባዊ መጣጥፍ ጻፈች፡፡

የብዙ መጣጥፍ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሳይወጣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ገብረእግዚ ስላዩት ‹‹አገሪቱ የሴተኛ አዳሪዎች መናኸሪያ ሆናለች እያላችሁ ነው?›› በማለት ስለተቆጡ እንዳይታተም ተከለከለ፡፡ ሚኒስትሩም አልፈውም ‹‹ጸሀፊዋን ማግኘት እፈልጋለሁ›› ብለው አናገሯት፡፡ እርሷ ግን ‹‹መታረም ያለበት ነገር መታረም አለበት እንጂ እውነታውን መካድ ችግሩ ስር እንዲሰድ መንገድ መክፈት ነው፡፡›› ብላ ስለመነች ጽሁፉን በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ላይ አወጣችው፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሄዳ ያቀረበችው የዝውውር ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ በጣቢያው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስትሰራ የነበረውን ከማጀት እስከ አደባባይ ይዛ ቀጠለች፡፡ በዚህ ስራዋ መላ ኢትዮጵያን ዞራ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲታወቁ ከማድረግ ባሻገር እንዲታረሙም የበኩሏን ተወጥታለች፡፡ በዚህ ሥራዋ ውጤታማ መሆኗ “ተጓዥ ካሜራችን” የሚል ዝግጅት አዘጋጅ ሆና እንድትመረጥ መነሻ ሆኗል፡፡

ብዙ በጋዜጠኝነት ከ18 ዓመት በላይ ካገለገለች በኋላ በ1983 ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከመንግሥት መገናኛ ብዙሀን ከተባረሩ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ሆነች። በጊዜው ከአምስት ዓመቱ ብቸኛ ህጻን ልጇ ጋር በሥራ ማጣት ከፍተኛ ችግር ላይ ወደቀች፡፡ በኋላም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ብዙን በምትሰራው ስራ ያውቋት ስለነበርም በሚመሩት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት በቢሯቸው ውስጥ እንድትሰራ ቀጠሯት፡፡

ምስል አንድ፡ ጋዜጠኛ ብዙ ወንድማገኘሁ አለሙ

አዲሱ ስራዋ ብዙን ሌላ ፈተና ውስጥ ከተታት፡፡ ከፕሮፌሰሩ ጋር መስራቷ ያላስደሰተው መንግሥት ክትትል አበዛባት፡፡ ፕሮፌሰሩን እንድትሰልል ትዕዛዝ እስከመስጠት ደረሰ፡፡ እሷ ግን በዚህ ዓይነቱ ስራ ከመሰማራት ሞቷን እንደምትመርጥ በራሷ ወስና ወደ እስራኤል ተሰደደች፡፡

ብዙ ከምትወደው ስራ ያለአግባብ መሰናበቷና ልጇን አዲስ አበባ ትታ መሄዷ ሰላም አሳጣት፡፡ ለመኖር ስትል ዝቅተኛ የተባለውን ስራ ሁሉ ለመስራት ሞከረች፡፡ ብዙም ሳትቆይ  ወደ ካናዳ ተሰደደች፡፡ እዚያም ኑሯዋን ለማሸነፍ የተለያዩ ስራዎችን መስራት ቀጠለች፡፡ የአገሯ ሁኔታ ግን ሁሌም ያሳስባት ነበር፡፡ እንደሷ በግፍ ከሚወዱት አገራቸውና ስራቸው ተባረው በባዕድ አገር የሚንከራተቱ ኢትዮጵያውያን ሁኔታም እንቅልፍ ይነሳት ነበር፡፡ ይህ ነገር ያበቃ ዘንድ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመደገፍ በአገሪቱ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትግል አድርጋለች፡፡

 

ምንጮቻችን:

  • ብዙ ወንድማገኘሁ ዓለሙ ቃለመጠይቅ ሐምሌ 2014
  • አዲስ ዘመን ጋዜጣ

ጳውሎስ ኞኞ፡ ራሱን በራሱ በማስተማር በሙያ ከፍ ያለ ጋዜጠኛ

Previous article

በአሉ ግርማ: ጋዜጠኛው ደራሲ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply