የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል

ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል /MIRH/ 30 ነሀሴ 2014

በመቅደስ ደምስ

መስከረም 3 ቀን 1914 በጊዜው አልጋ ወራሽ ልኡል ራስ ተፈሪ መኮንን የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ‹‹የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽ ልኡል ራስ ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ድርጅት›› በሚል በስማቸው የተሰየመ ማተሚያ ቤት አንዲከፈት አደረጉ፡፡ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖትንም የማተሚያ ቤቱ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ፡፡

ማተሚያ ቤቱ አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያረፈበትና በወቅቱ ገነተ ልዑል እየተባለ ይጠራ የነበረው የቀድሞው ቤተ መንግስት ውስጥ በሚገኘው የጨው ቤት እየተባለ በሚጠራ ህንጻ ውስጥ ነበር የተቋቋመው፡፡ ማተሚያ ቤቱ በሰው ጉልበት በሚንቀሳቀሱ የሕትመት መሣሪያዎች ስራ ጀመረ፡፡ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ማተሚያ ቤቱ ውስጥ ለመስራት አዲስ አበባ ከተሙ፡፡

ወደ ግእዝና አማርኛ ተተርጉመውና በእጅ ተጽፈው ለአንባቢያን ይቀርቡ የነበሩት የሀይማኖት መጻህፍት ብዛት እየጨመረ በመምጣት ላይ ከነበረው የንባብ ፍላጎት ጋር አልጣጣም በማለቱ ነበር ራስ ተፈሪ ማተሚያ ቤት ለማቋቋም የተነሱት፡፡ ሀሳባቸውንም ከጀርመን ሀገር ዘመናዊ የህትመት ማሽን በማስመጣት እውን አደረጉት፡፡ የህትመት መጠኑም ማደግ ጀመረ፡፡

በ1916 ራስ ተፈሪ ለጉብኝት ወደ ምእራብ አውሮፓ አቀኑ፡፡ በዚያም ጉብኝት አንድ ነገር ቀልባቸውን ሳበው፡፡ ጋዜጣ፡፡ ጋዜጣ በእነኚህ ሀገራት የሚሰጠውን ጥቅም ተገነዘቡ፡፡ የሳቸውን ጉብኝት በተመለከተ የሰሯቸው ሰፊ ዘገባዎች አስደነቋቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጋዜጦች ስለንጉሱ ታላቅ መሪነት ሲጽፉ ሌሎቹም ስለብልህነታቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸውና ለወታደራዊ ጉዳዮች ስለነበራቸው ልዩ ፍቅር ዘገቡ፡፡ በዚህ ምክንያት እሳቸውም ስለ መንግስታቸው የሚያትት የግላቸው አንድ ጋዜጣ እንዲኖር ፍላጎት አደረባቸው፡፡ ጋዜጣው ከህዝብ ድጋፍ በማግኘት የፖለቲካ ዓላማቸውን ከግብ እንዲያደርሱ እንደሚያግዛቸው ተስፋ ጥለውበታል፡፡ በተመሳሳይ የማተሚያ ቤቱ ዳይሬክተር ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖት ማተሚያ ቤቱ ጋዜጣ እንዲኖረው ይመኙ ስለ ነበር ራስ ተፈሪ ከአውሮፓ ጉብኝታቸው ሲመለሱ ሀሳባቸውን ገለጹላቸው፡፡ ሀሳባቸውም ተቀባይነት አግኝቶ ታህሳስ 23 ቀን 1917 ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተሰኘ ባለ አራት ገጽ ሳምንታዊ ጋዜጣ ለህትመት በቃ፡፡

ራስ ተፈሪ ለጋዜጣው የሰጡት ስያሜ በኢትዮጵያ ብርሀን (እውቀት) እና ሰላም እንዲኖር የነበራቸውን ፍላጎት እንዲያንጸባርቅላቸው በማሰብ እንደነበረ በጋዜጣው ላይ ተጠቅሷል፡፡ ትርጓሜው እድገትና ዘመናዊነትን የመወከል ዓላማ ነበረው፡፡

እንደ ብላታ ጌታ ህሩይ ወልደሥላሴ ያሉ የቤተክርስቲያን ምሁራን ጋዜጣው ለህትመት እንዲበቃ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ የማተሚያ ቤቱ ዳይሬክተር የነበሩት ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖት የጋዜጣው የመጀመሪያ ሀላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡ ከቋሚ ጋዜጠኞች ባሻገር ‹‹የብርሃንና ሰላም ተላላኪ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ክፍለ ሀገራት ጽሁፎችን የሚያሰናዱ ሰዎችም እንዲኖሩት ተደረገ፡፡

የመጀመሪያው የጋዜጣው እትም ሲወጣ የማስመረቂያ መርሀግብር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የመጀመሪያው እትም ቅጂዎች ለራስ ተፈሪና በዝግጅቱ ለመታደም ለተሰበሰቡት ባለስልጣኖች ቀረበ፡፡ ንጉሱ በደስታ፤ ባለስልጣናቶቹ ደግሞ በጉጉት ነበር ያነበቡት፡፡ ሲጀምር በአራት ገጾች የጀመረው ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ ዘወትር ሀሙስ ይወጣ ነበር፡፡ ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ በሁለት ፈረሰኞች ጋዜጣው ለአዲስ አበባ አንባብያን ይሰራጭ ነበር።

ጋዜጣው ወደ ህትመት በገባበት ወቅት በህዝብ ዘንድ እውቅና ለማግኘትና ተነባቢ ለመሆን ትልቅ ድካም ይጠይቅ ነበር፡፡ አንባቢን ለማበረታታት ለመጀመሪያው አንድ ወር ጋዜጣው በነጻ ታድሏል፡፡

‹‹ብርሀንና ሰላም›› ስርጭት ጀምሮ ብዙም ሳይቆይ የወሎ ንጉስ ሚካኤል ልጅና የአጼ ምንሊክ የልጅ ልጅ የሆኑትን የወ/ሮ ተዋበች ሚካኤልን እረፍትና የቀብር ስነ ስርዐት የሚያትት ጽሁፍ ጋዜጣው በጥር 21 ቀን 1917 እትሙ ይዞ በመውጣት ለመኳንንቱና ለሀዘንተኞቹ በነጻ እንዲደርስ በመደረጉ በአንባቢዎች ዘንድ ይበልጥ ትኩረት አተረፈለት፡፡ ጋዜጣው ለሥርዓተቀብሩ ትኩረት በመስጠቱና በጻፈው ጽሁፍ ባለስልጣናቱ እጅግ ተደስተው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ጋዜጣው ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ፡፡

ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ጋዜጣው ቋሚ የዋጋ ተመን ወጣለት፡፡ ዋጋውም ለሀገር ውስጥ አንባብያን በዓመት አምስት ብር ከሀገር ውጭ ደግሞ ሰባት ብር ነበር፡፡ ገዝተው ማንበብ የሚፈልጉ ሁሉ ዳይሬክተሩን አግኝተው ማነጋገርና መመዝገብ እንደሚችሉ የሚገልጽ ማስታወቂያ በጋዜጣው ላይ መታተም ጀመረ፡፡ ለተመዘገቡ ሰዎችም ጋዜጣው በየቤታቸው እንዲደርሳቸው ይደረግ ነበር፡፡

‹‹ብርሀንና ሰላም›› መታተም ከጀመረ ከአስር ወራት በኋላ የገጾቹ ብዛት ከአራት ወደ ስምንት ከፍ አለ፡፡

በሀገሪቱ እድገትና ዘመናዊነት ላይ የሚያተኩሩት ጽሁፎችም የጋዜጣውን ተወዳጅነት አሳደጉት፡፡  የምዕራባውያን ትምህርትን ጥቅምና ጉዳት የሚያትቱ ጽሁፎች ከጋዜጣው ይዘቶች ውስጥ ነበሩበት፡፡ በተለይ ደግሞ ቀደም ሲል በፈረንሳይኛ ቋንቋ ታትሞ የነበረና ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፍላጎት የሚገስጽና የሚያስጠነቅቅ ጸረ-ፋስሽት ጽሁፍ በፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤል አማካኝነት ተተርጉሞ በመጋቢት 1919 እትም ወጥቶ ነበር፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የጣሊያን ሌጋሲዮንም ተቃውሞውን ፈጥኖ ነበር ያሰማው፡፡ ይህም የበርካቶችን ቀልብ በመሳብ የጋዜጣውን ተነባቢነት ይበልጥ ከፍ እንዲል አደረገው፡፡

በ1921 የጋዜጣው ህትመት በሳምንት 500 ቅጂ ደረሰ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽ ልኡል ራስ ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ድርጅት›› በሚል ስያሜ የተቋቋመው ማተሚያ ቤትም መስከረም 27 ቀን 1921 ‹‹ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› ተብሎ ተሰየመ፡፡

ሀይማኖት ነክ ጉዳዮች፣ የንግድ ወሬዎች፣ ትምህርት፣ ግብርና እና ጤና፣ መሰረተ ልማት በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ሽፋን ይሰጣቸው የነበሩ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የውጭ ሀገራት ቆንስላዎች የተሰበሰቡ የውጭ ዜና ዘገባዎችና ማስታወቂያዎችም ይተላለፉበት ነበር፡፡ ከ1926 በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የራሱ ገመድአልባ የቴሌግራፍ መስመሮችን በመዘርጋቱ ጋዜጣው የውጭ ሀገራት ዜና ዘገባዎችን በቀጥታ መቀበል ጀመረ፡፡ በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱ ከውጭ ሀገራት ጋር የሚያደርጓቸውን ግንኙነቶች የሚመለከቱ ዘገባዎችን ያወጣ ነበር፡፡ በመሳፍንቱ ዙሪያ የሚኖሩ ሰርግና የቀብር ስነ ስርአቶችም ሽፋን ያገኙ ነበር፡፡ የአንባቢያን አስተያየቶችም በጋዜጣው ይታተሙ ነበር፡፡ አስተያየቶቹ ኋላ ቀርነትን የሚነቅፉና የንጉሱን ለውጥ አምጪ አመራር የሚያደንቁ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ንጉሱም አልፎ አልፎ ጽሁፎቻቸውን በጋዜጣው ያወጡ እንደነበር ይነገራል፡፡

የጣሊያን ወረራን ተከትሎ ብርሀንና ሰላም ጋዜጣ ስራውን አቆመ፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር የህትመት ማሽኖቹን ከአየር ጥቃት ለመከላከል የጀርመን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የብላታ ሀይሌ ወልደ ኪዳን ቤት እንዲቆዩ ተደረገ፡፡ ጋዜጣው ዳግም ስራውን የጀመረው ጣልያን ጓዟን ጠቅልላ ከኢትዮጵያ የወጣችበት አንደኛ አመት በተከበረበት ሚያዚያ 27 ቀን 1934 ነበር፡፡ የብርሀንና ሰላም መመለስም በመጽሄት መልክ ነበር፡፡ የመጽሄትነት እድሜውም ቢሆን ብዙም አልቆየ፡፡ በ1942 ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ተደረገ፡፡

 

ምንጮቻችን፡

  • መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፤ 2009፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፡ ከ1922-1927. አዲስ አበባ፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፡፡
  • ዘውዴ ረታ፤ 2007፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት፡ 1923-1948፤ አዲስ አበባ፡ ሻማቡክስ፡፡
  • Meseret Chekol. 2013. The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia. New York: University Press of America

 

ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን)

Previous article

አዲስ ዘመን ጋዜጣ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply