የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ብርሃኑ ዘሪሁን፡ ጋዜጠኛና የስነ ጽሁፍ ሰው

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 13 ነሐሴ 2014

በመቅደስ ደምስ

ብርሃኑ ዘሪሁን ከአባቱ መሪጌታ ዘሪሁን መርሻ እና ከእናቱ ወይዘሮ አልጣሽ አድገህ በጎንደር ከተማ በ1925 ተወለደ። አባቱ ለልጃቸው ትምህርት አብዝተው የሚጨነቁ ሰው ስለነበሩ ልጃቸውን ቤት ውስጥ ፊደል አስቆጥረው አራት ዓመት ሲሆነው የቤተክህነት ትምህርት አስጀምረዋል፡፡ ብርሀኑ የቤተክህነት ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ጎንደር በሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት ቀጠለ፡፡

በቤተክህነት የኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ትምህርቶች መማሩ ለልዩ ተሰጥኦው መሰረት ሆኖታል፡፡ የነኅሩይ ወልደስላሴን፣ አፈወርቅ ገብረእየሱስን፣ የከበደ ሚካኤልን እና የሌሎች ኢትዮጵያውያንን በርካታ መጻህፍት በማንበብ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ እውቀት አካብቷል፡፡

በ1945 ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት የሬዲዮ ቴክኒሻንነት መማር ጀመረ፡፡ በተግባረ ዕድ ቆይታውም የታላላቅ የአለማችንን ደራሲያን ስራዎችን በማንበብ እውቀቱን አሰፋ፡፡

ቆይቶም ከአንባቢነት ወደ ጸሀፊነት በመሸጋገር የትምህርት ቤቱ ልሳን የነበረችውን “ቴክኒ-ኤኮ” የምትሰኝ መፅሄት አዘጋጅ ሆነ፡፡ ተውኔት ጽፎም ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አሳይቷል። ከትምህርት ቤቱ ውጭም ለተለያዩ ጋዜጦች ይፅፍ ነበር። ብርሀኑ ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ትምህርቱን በዲፕሎማ ሲያጠናቅቅ አንደኛ ወጥቶ ተሸላሚ በመሆን ነበር፡፡

ብርሃኑ ዘሪሁን የትምህርት ውጤቱ ከፍተኛ ስለነበር እዚያው ተግባረ ዕድ ውስጥ የቴክኒክ መምህርነት ስራ አገኘ። ጥቂት ጊዜ ከሰራ በኋላ በኢትዮጵያ የካርታና ጂኦግራፊ ድርጅት በሜካኒክነት ሙያ ለተወሰነ ጊዜ አገለገለ፡፡ ከዛም በመከላከያ ሚኒስቴር በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ።

ከ1952 በኋላ ብርሀኑ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው ክፍት የስራ ቦታ ተወዳድሮ በጋዜጠኝነት ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ጋዜጣው ላይ በሚጽፋቸው መጣጥፎች እና ታሪኮች ራሱንም ጋዜጣውንም በአጭር ጊዜ ታዋቂ ማድረግ ቻለ፡፡

ከቆይታ በኋላ ወደ ዕለታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመዘዋወር ለአስር ዓመታት በዋና አዘጋጅነት አገለገለ፡፡ ከዛም ወደ ጀርመን አገር በመጓዝ ለጀርመን ድምጽ የአማርኛ ሬዲዮ ፕሮግራም ለአምስት ዓመታት ሰርቷል፡፡ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነቱ ቀጠለ፡፡

ብርሀኑ በጋዜጠኝነቱ ለተገፉ ሰዎች መብት ተቆርቋሪ ሆኖ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ከንጉሳዊ አገዛዙ ጋር ሊስማማ አልቻለም ነበር፡፡ ይህም ወደ ሬዲዮ እንዲዘዋወር ምክንያት ሆኗል፡፡ በዝውውሩ ደስተኛ ባይሆንም በሬድዮም ስህተት ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ከመንቀፍ ወደኋላ አላለም፡፡ በዚህም ምክንያት ከጋዜጠኝነት ሙያው ለመለያየት ተገደደ፡፡

ብርሃኑ ዘሪሁን ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር በድርሰቶቹ አዲስ አቅጣጫ ማሳየት ችሏል። በ1958 ዓ.ም ‹‹የቴዎድሮስ ዕንባ›› የተሰኘውን የአፄ ቴዎድሮስን አነሳስ፣ ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ርዕይና የህይወታቸውን ፍፃሜ የሚያሳየውን መጽሀፉን አሳተመ፡፡ ቆይቶም መጽሀፉ በመድረክ ቴአትርነት ለመሰራት በቅቷል፡፡

‹‹የእንባ ደብዳቤዎች››፣ ‹‹ድል ከሞት በኋላ››፣ ‹‹የበደል ፍፃሜ››፣ ‹‹ጨረቃ ስትወጣ›› እና ‹‹የታንጉት ምስጢር›› ከብርሃኑ መጻህፍት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በ1970ዎቹ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፉትን ‹‹ማዕበል የአብዮቱ ዋዜማ››፣ ‹‹ማዕበል የአብዮቱ መባቻ›› እና ‹‹ማዕበል የአብዮቱ ማግስት›› የተሰኙ ሶስት ተከታታይ መፃሐፍትን በማሳተም ብርሃኑ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይጠቀሳል። ብርሃኑ ከደራሲነቱ ባሻገር ፀሐፌ-ተውኔትም ነበር። ከቴዎድሮስ እንባ በኋላ ‹‹ሞረሽ››፣ ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ››፣ ‹‹የለውጥ አርበኞች››፣ ‹‹ባልቻ አባነፍሶ›› የተሰኙ ቴአትሮችን ጽፏል።

ብርሀኑ የስነጽሁፍ ሀያሲም ነበር፡፡ በጋዜጦች ላይ የተለያዩ ደራሲያንን ስራዎችና ፅሁፎች እየተከታተለ ሂሳዊ መጣጥፎችን በማቅረብ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የብርሃኑ ስራዎች በበርካታ የስነ-ጽሁፍ እና የታሪክ ተመራማሪ ምሁራን ጥናት ተደርጎባቸዋል።

ብርሃኑን በቅርብ የሚያውቁት በባህሪው ዝምተኛና ቁጥብ ነው ይሉታል፡፡ ብርሃኑ ዘሪሁን በጤና መታወክ ምክንያት ሚያዚያ 16 ቀን 1979 በ54 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል። ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበር፡፡

 

ምንጭ፡

Habtamu Girma Demiessie (2018). Ethiopian Literary Giants and their Works: Novel, Play and Journalism in Ethiopia (1850’s-1960’s) pp.214-220 (https://www.academia.edu)

 

የጅማ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ሬድዮ

Previous article

ነጋሽ ገብረማርያም፤ ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት ፋናወጊዎች አንዱ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply