የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፋይል / MIRH/ 08 ሰኔ 2014

በመቅደስ ደምስ


ባንዲራችን ጋዜጣ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በሱዳን ካርቱም ይታተም የነበረ የትግል ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው የፋሺስት ጣሊያንን ከኢትዮጵያ ምድር ለማባረር በሱዳኗ መዲና ካርቱም የዘመቻ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የተቋቋመ ጋዜጣ ነበር። የኢትዮጵያ አርበኞች በውስጥ ትግል ባደረጉት መስዋእትነት ኢጣሊያንን እያሸነፉ ሲመጡ ዓፄ ኃይለ ሥላሴም በሱዳን በኩል ሆነው ኢጣሊያንን ፕሮፖጋንዳ ለዓለም እያጋለጡ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እያሰቡ በነበረበት ወቅት ባንዲራችን ጋዜጣ በሚያዚያ 18 1933 ዓ.ም መታተም ጀመረ፡፡

ባንዲራችን በንጉስ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ ሰጪነትና ፔሪ ፌሎውስ በተባለ የእንግሊዝ መኮንን አማክኝነት የተመሰረተ ጋዜጣ ነው፡፡ ታምራት አማኑኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡ ታዲያ ‹‹ባንዲራ›› የሚለው ቃል ከጣሊያን ቋንቋ የተወሰደ በመሆኑ ዋና አዘጋጁ እንብዛም አይወዱትም ነበር፡፡ ከእርሳቸው በመቀጠል የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ልጅ ሲራክ ኅሩይ የዋና አዘጋጅነቱን ሥራ ሠርተዋል፡፡ ሲራክ ኅሩይ በእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ እውቅ ሰው ናቸው፡፡

ባንዲራችን ጋዜጣ መሐል ላይ የይሁዳ አንበሳ ምስል ያለበትን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፊት ለፊት ገጹ በመያዝ እንደ መለያ ሎጎ ይጠቀም ነበር፡፡ በየሳምንቱ ረቡእ ወደ አንባቢያን ይደርስ የነበረው ባንዲራችን ጋዜጣ አብዛኛው ጽሑፎች የእንግሊዙ መኮንን ፔሪ ፌሎውስ እና የሀገሩ ሰው የሆነው ጋዜጠኛ ጆርጅ ስቲርን ብእሮች ነበሩ፡፡

በጋዜጣው ላይ የሚታተሙት ጽሑፎች እንደጣሊያን የውሸት ፕሮፓጋንዳዎች ሳይሆኑ የተጣሩ መረጃዎችና ለህዝብ ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦች እንደሆኑ የጋዜጣው አንደኛ አመት ሚያዚያ 18 ቀን 1933 ዓ.ም እትሙ ያትታል፡፡ ጋዜጣው የዋጋ ተመን እስኪ ወጣለት ለተወሰኑ ጊዜያት በነጻ ሲታደል ቆይቷል፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያ ጦር የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ለማስወጣት በሚያደርገውን ትግል የእንግሊዝ ጦር በአጋርነት ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በወቅቱ የባንዲራችን ጋዜጣ ዜናዎች ትኩረትም የእንግሊዝና የኢትዮጵያ የትብብር ጦር የሚያስመዘግበውን ድልና የጣሊያን ጦር ሽንፈት ያትት ነበር። የኅትመቱን ሥራ የሚሠራው ደግሞ የዘር ግንዱ ከግሪክ የሚመዘዝ ኮንስታንቲኖስ ትሬጅ የተባለ ኤርትራዊ ሰው ነበር፡፡

ምሰል አንድ፡ ሰንደቅ ዓላማችን ጋዜጣ ሚያዚያ 28, 1933 ዓ.ም እትም

ታዲያ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ የተባበረው ጦር የሚያስመዘግበው ድልና የጣሊያን ጦር ሽንፈት ወሬዎችን የያዘው ባንዲራችን ጋዜጣ፣ በአውሮፕላን አማካኝት ከሰማይ ወደ መሬት ቁልቁል ለሕዝቡ ይበተን ነበር፡፡ በተለይም በኢጣሊያን ይዞታ ሥር የነበሩ የምእራብ ኢትዮጵያ ግዛቶች የጋዜጣው ዋነኞቹ መዳረሻዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ጋዜጣ አማካኝነት ብዙ የጣሊያን የቅኝ ግዛት ወታደሮች እንዲከዱ ማድረግ መቻሉን አንዳንድ ጽሑፎች ያትታሉ፡፡

ጣሊያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣና ዓፄ ኃይለ ሥላሴም አዲስ አበባ ሲገቡ ባንዲራችን ጋዜጣም ኅትመቱን አቆመ፡፡ ታዲያ ጋዜጣው ኅትመቱን እስኪያቆም ድረስ አጠቃላይ ኅትመቶቹ 28 ደርሰው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከ1933 ዓ.ም በኋላ ‹‹ባንዲራችን›› የሚለው ስያሜ ተቀይሮ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› በሚል መጠሪያ ዳግም በአማርኛ እና ዓረብኛ ቋንቋዎች በሳምንት ሁለት ጊዜ ዘወትር ረቡዕና ቅዳሜ ይታተም እንደነበር መረጃዎች ያትታሉ፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን የአረብኛው ክፍል “አል ዋይሂድ-Al Wahid” የሚል ሲሆን ትርጉሙም “አንድነት” ማለት ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈሉትን የሙስሊምና የክርስቲያን ወገኖችን ጀግንነት በማሰብ እንደነበር ጋዜጣው አንደኛ ዓመቱን አስመልክቶ ይዞት በወጣው ልዩ እትሙ ገልጾታል፡፡

በኋላም በ1950 ዎቹ የአረብኛው ክፍል ራሱን ችሎ መታተም ጀምሮ እንደነበር ምንጮች ያመለክታሉ፡፡

 

ምንጮቻቻን፡

Dr. Mesert chekol, 2013, The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia.

https://www.facebook.com/Insewasew/photos/a.1948634185361157/3394640177427210/?type=3

አፍሪካ በመገናኛ ብዙኃን የቢዝነስ ዘገባ ዉስጥ

Previous article

የስልጠና ምዝገባ ጥሪ ለጋዜጠኞችና ለኢንተርኔት አምደኞች

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply