መመሪያዎች

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ሥርዓት ቃል ኪዳን

መመሪያዎች/ MIRH/ 20 መስከረም 2015

በ-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በአገራችን ጠንካራ እና ዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የተጀመረው የሪፎርም ስራን በጋራ ማሳካት እና ችግሮችን ከምንጮቻቸው የሚያደርቁ በረጅም ጊዜ እይታ የተቃኙ እርምጃዎችን መውሰድ በሀገር እና በህዝብ ላይ ሲፈፀም የኖረውን ውስብስብ የአስተዳደር በደል፣ ስር የሰደደ ኢ-ፍትሃዊ አሰራር እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መሰረታዊ በሆነ መልኩ በመቀየር እንደ አገር በፊታችን የተደቀነውን አስከፊ ሁኔታ የህልውና አደጋ ለማስወገድ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፤

ከነባራዊው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ሁኔታዎቻችን በመነሳት እና ለህዝብ ፍላጎት በመገዛት ከላይ የተጠቀሰውን ሰፊ የሪፎርም ስራ ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ በመላው ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም የህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤

ይህን ለማድረግም ሁሉም ዜጋ እና የማህበረሰብ ክፍል በተረጋጋ ሁኔታ፣ በንቃት እና በስፋት መሳተፉ ፍፁም አስፈላጊ በመሆኑ፤

በኢትዮጵያ ዘላቂ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ እድገት እንዲፋጠን፣ በሕግ የበላይነት እና በህዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት አብሮ መሥራት የሚገባ በመሆኑ፤

እንዲሁም በአገራችን እየተፈጠረ ያለውን የዲሞክራሲ መድረክ ለህዝቦች አብሮነት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብ እና ሕገ-መንግስታዊ መብቶች መከበር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማስቻል በሚደረገው ሀገራዊ ንቅናቄ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚኖራቸው ሚና ልዩ እውቅና በመስጠት ከፍተኛ ትኩረት ስላገኘ፤

የተለያዩ ሀሳቦችን እና የማህበረሰብ ድምፆችን የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዲሞክራሲ ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት መስፈን እና በሰላም መረጋገጥ ከመንግሥት ያላነሰ አይተኬ ሚና እና ሃላፊነት ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ፤

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚስተዋለው አሳሳቢ የሰላም መደፍረስ የተጀመረውን ሰፊ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ንቅናቄ ወደ ኋላ እንዳይመልሰው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋማዊ እና ቀጣይነት ባለው የአደረጃጀት መድረክ አማካይነት እየተወያዩ የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ማስቻል ፍጹም አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፤

የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት በተሞላበት አካሄድ የአገርን ብሔራዊ ደህንነት የዜጎችን ነፃነት እና መሰረታዊ መብት በዘላቂነት ማስጠበቅ በሚያስችል ደረጃ መሳተፋቸውም ተገቢ ስለሆነ፤

በሀገራችን በቀጣይ የሚደረገውን ብሔራዊ እና የአካባቢ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የሁሉንም አስትዋጽኦ እና ትኩረት የሚጠይቅ በመሆኑ፤

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ደጋፊዎቻቸው የዜጎችን እና የሌሎችን የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት እና ደጋፊዎች ሕገ-መንግሥታዊ መብት እና ግዴታዎችን ባከበረ መልኩ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ለማድረግ ይቻል ዘንድ፤

እኛ በኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ በነፃ ፈቃዳችን ይህን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአሰራር ሥርዓት የጋራ ቃል ኪዳን በመመስረት ሰነዱ ለሀገራችን ሕዝቦች እና መንግሥት በይፋ እንዲገለጽ በፊርማችን አጽድቀናል፡፡

ሰነድ፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ሥርዓት ቃል ኪዳን

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ

Previous article

ኢትዮጲያን ቢዝነስ ሪቪው – ኢቢአር

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply