ይማሩ

በአውሮፓ ነባር መገናኛ ብዙኃን ቲክ ቶክን በመጠቀም ብዙ ሺሕ ወጣቶችን እየሳቡ ነው

ወጣቱ ትውልድ ከነባር መገናኛ ብዙሃን ጋር ያለው ቅርበት ደካማ እንደሆነ ልዩ ልዩ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በአውሮፓ የሚገኙ አንጋፋ መገናኛ ብዙኃን ቲክ ቶክን እንደ አንድ ፕላትፎርም በመጠቀም ወጣቱን ትውልድ በመሳብ ከነባሩ መገናኛ ብዙሃን ጋር ሁነኛ ትሥሥር መፍጠር እንደቻሉ እየተነገረ ነው፡፡

ይማሩ /MIRH/ 18 ሚያዚያ 2023 

በፍቃዱ ዓለሙ

ከሺሕ ዓመታት በላይ በውስን መገናኛ ብዙኃን ተይዞ የነበረው የመረጃ ሥርጭት ሥርዓት ሁነኛ መሻሻሎችን አሳይቷል፡፡ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያያዞ በተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ፕላትፎርሞች አማካኝነት ዓለም አቀፍ የመረጃ ሥርጭቱን ቀይሮታል፡፡ በተለይ የማኅበራዊ ትሥሥር ዘዴዎች የመረጃ ተደራሽነትን ብቻ ሳይሆን የይዘት ቀረጻ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠር ችለዋል፡፡ ግለሰቦች ከመረጃ ተቀባይነት ወደ መረጃ አሰራጭነት እንዲሸጋገሩ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ያለፉትን ሁለት አሥርት ዓመታት ብቻ የተመለከትን እንደሆነ እንደ ፌስቡክ፣ ቱዊተር እና ኢንስታግራም የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከነባሩ የመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ አማራጭ የመረጃ ምንጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ይህ የቴክኖሎጂ እድገት ግለሰቦችን ከመረጃ ተቀባይነት ወደ መረጃ አሰራጭነት ማሸጋገሩ ለነባር መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ፈተና ብቻ ሳይንሆን እድልም አምጥቶላቸዋል፡፡ በተለይ ብዙ ሺሕ አንባቢያንን እና አድማጭ ተመልካቾቻቸውን በማጣታቸው ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ነባር መገናኛ ብዙኃን ለምሳሌ እንደ ጋዜጣ እና መጽሔት የመሳሰሉ ሚዲያዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ኅትመት ማቋረጣቸውን ተከትሎ አንዳንዶች ተገደውም ቢሆን ወደ በይነ መረብ የገቡ ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የብሮድካስት ዘርፉን ከተመለከትን ከሳተላይት ሥርጭት በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ተጨማሪ የይዘት ዝግጅቶቻቸውን እንዲያቀርቡ እድል ይዞላቸው ብቅ ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ነባር መገናኛ ብዙኃን አንባቢያዎች እና አድማጭ ተመልካቾቻቸውን ይዘው ለመቀጠል እና አዳዲስ የይዘት አማራጮችን ለማቅረብ የበይነ መረብ ተደራሽነታቸውን በየጊዜው አሻሽለው ቢቀርቡም፤ ወጣቱን ትውልድ ለመያዝ ግን ፈተናው አሁንም ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ የቴክኖሎጂ እድገት በየጊዜው የሚወልዳቸውን ፕላትፎርሞች በመጠቀም ነባሩንና አዲሱን ትውልድ በተለይ ወጣቱን ለመያዝ ነባር የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ልዩ ልዩ ዘዴዎቸን እንዲከተሉ አስገድዷቸዋል፡፡

ቲክ ቶክ (TikTok)

አዝናኝ፣ አስተማሪ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች በስፋት የሚስተናገዱበት አዲሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ቲክ ቶክ (TikTok) ሆኗል፡፡ አውሮፓውያን ሀገራት በተለይ በጀርመን ከሚገኙ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን መካከል ዶይች ቬለ (DW) ወጣቱን ትውልድ ማእከል ያደረጉ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ብዙ ሺሕ ወጣቶችን መሳብ እንደቻለ እየተነገረ ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ ዜና ማሰራጫዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቴክቶክ አካውንት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ከ18 እስከ 24 የዕድሜ ክልል የሚገኙ አሜሪካውያን ወጣቶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቲክቶክ ተጠቃሚ እንደሆኑ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ሆኖም አሜሪካ በቲክቶክ ላይ እገዳ ለመጣል እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት በአውሮፓ ከሚገኙ የሕዝብ መገናኛ ተቋማት መካከል የጀርመኑ ዶይች ቬለ ከሌሎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተሻለ ሁኔታ ቲክቶክን በመጠቀም ብዙ ውጣቶችን መሳብ እንደቻለ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ዮሃና ሩዲገር ለጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ፍራንሲስኮ ዛፍራኖ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ተናግራለች፡፡ የቃለ መጠይቁን ጭምቅ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የDW “በርሊን ፍሬሽ” (DW Berlin Fresh) የቲክቶክ ተሞክሮ

የ“በርሊን ፍሬሽ” በጀርመን የሕዝብ ብሮድካስቲንግ ተቋም የሆነው ዶይቸ ቬለ (DW) የመጀመሪያው የቲክ ቶክ ቻናል ሲሆን ዜናዎችን፣ አኗኗርን፣ ባህልን እና ሌሎችንም በማዋዛት የበርሊን ወጣት ዜጎች ለማስተማርና ለማዝናናት ታስቦ የተዘጋጀ አካውንት መሆኑን ዮሃና ሩዲገር ለጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ፍራንሲስኮ ዛፍራኖ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ አብራርታለች፡፡

የበርሊን ፍሬሽ ቲክ ቶክ ፕሮግራም 362,000 ተከታዮች እና 14.5 ሚሊዮን ገጹን የተወዳጁ ደንበኞች አፍርቷል። ስኬቱን ተከትሎ በDW የሚተዳደሩ ሌሎች አካውንቶች በመድረክ ላይ እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የዲ ደብሊዩ ዜና (DW News) ሌጎስ ለናይጄሪያ እና ምዕራብ አፍሪካ ዜናዎች፣ ዲ ደብሊዩ ስቶሪስ DW Stories በአጭር ደቂቃ የተመረጡ ርእሰ ጉዳዮችን ገለጻ የሚያደርግ እና DW በርሊን ቴል አቪቭ የበርሊን ትኩስ ይዘቶችን በዕብራይስጥ የትርጉም ጽሑፎች ያቀርባል። DW ከቢቢሲ፣ ቪኦኤ እና ፍራንስ 24 ጋር በመተባበር ከ90 በላይ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች በተለይም በቲክ ቶክ አማካኝነት ብዙ ሺሕ ወጣቶችን ተደራሽ ያደረጉ ፕሮግራሞችን በአጋርነት እየሠሩ መሆኑን ዮሃና ሩዲገር ትናገራለች፡፡

https://www.tiktok.com/@dw_berlinfresh?refer=embed  Berlin really does have something for everyone. 

DW በአሁኑ ሰዓት 25 የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ሲኖሩት ሁሉም ፕላትፎርሞች በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን እንዲደርሱ ማድረግ እና በተለይም ወጣት ታዳሚዎችን ማካተቱን ማረጋገጥ ዮሃና ሩዲገር ሥራዋ እንደሆነ ስታብራራ “በርሊን ፍሬሽ የዶይቸ ቬለ የመጀመሪያው የቲክ ቶክ መለያ ነበር። የጀመርነው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ነው። ያኔ ብዙ ሚዲያዎች እንዲህ ዓይነት ሥራዎች አልነበሩም። ዛሬ የሚዲያ ኩባንያዎች በቲክ ቶክ ላይ ከተጠቃሚዎች ጋር እንዴት መሥራት እንደሚቻል እያሰቡ ይገኛሉ” ብላለች፡፡

ዮሃና እንደምትለው “በርሊን ፍሬሽ” በአሁኑ ሰዓት የዶይቸ ቬለ መታወቂያ/መለያ ፕሮግራም እስከመሆን ደርሷል፡፡ ምክንያቱም ትላለች ዮሃና ከአውሮፓ እምብርት እና ከዋና ከተማዋ በርሊን አዲስ እይታን ስለምንፈልግ የአውሮፓ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ በተመለከተ ለአዲሱ ትውልድ በስፋት ለማስተማር፣ በህዝቦች መካከል መግባባትን ለመፍጠር እና የተለያዩ ባህሎች እና ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ ሃሳብና ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ እንዲኖር በማሰብ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ የቲክቶክ ይዘቶች በጣም ወጣት የሆኑ ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከ16 እስከ 24 አመት እድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች የቲክ ቶክ ተከታዮች ሆነዋል፡፡

በቲክ ቶክ የሚተላለፉ መረጃዎች ምን ዓይነት ቢሆኑ ይመረጣሉ?

የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች በብዛት ወጣቶች በመሆናቸው ምክንያት ለዜና ፍላጎት እንደሌላቸው ይሰማል፤ በእርግጥ ወጣቶች ዜናው በሕይወታቸው ላይ ምን ዓይነት ትጽእኖ ለፈጥር እንደሚችል ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ስለሆነም ከማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች አዝናኝ ጉዳዮች በተጨማሪ ዜና ነክ ጉዳዮችን ማስወገድ ሳይሆን ለቲክ ቶክ በሚመች መልኩ ከሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር ለምሳሌ ከጤና፣ ከአኗኗር፣ ከአመጋገብ እና ሌሎች ማኅበረ-ፖለቲካዊ ይዘቶች ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በአጭር በአጭሩ በደንብ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ማቅረብ ከተቻለ ወጣቶቹ ይቀበሉታል፡፡

የድምፅ ጥራት፣ የምስል ጥራት እና ታስቦበት የሚሠራ የይዘት ዝግጅት ሁል ጊዜ ተመልካች አለው፡፡ ወጣቶች ለቀለም፣ ለድምፅ ጥራት፣ ለውበት እና ለመቼት ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለቲክ ቶክ የሚዘጋጁ የምስል ወድምፅ ይዘቶች ከላይ ያነሳናቸውን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ያስገቡ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡

*****

ቃለ መጠይቁ ጋዜጠኛ ፍራንሲስኮ ዛፍራኖ በሚሰራበት በየሁለት ሳምንቱ በሚታተም Substack ጋዜጣ በመጋቢት ወር 2023 የወጣ ሲሆን አውዳዊ በሆነ ሁኔታ ወደ አማርኛ መልሰነዋል፡፡ ሙሉ ጽሑፉን ለማግኘት የሚከለተውን ማስፈንጠሪያ ተጭነው ያንብቡ https://mappingjournalism.substack.com/p/dw-tiktok-berlin-fresh?utm_source=substack&utm_medium=email

ነጋሪት ጋዜጣ (Negarit Gazeta)

Previous article

የዲላ ዩንቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሬድዮ ኤፍ ኤም

Next article

You may also like

Comments

Comments are closed.