የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

በአሉ ግርማ: ጋዜጠኛው ደራሲ

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 18 ሐምሌ 2014

በመቅደስ ደምስ 

በአሉ ግርማ በ1932 በኢሉባቦር ክፍለሀገር ሱጴ በምትባል ትንሽ ከተማ ተወለደ። ወላጆቹ አንድ ህንዳዊ ነጋዴና ከአካባቢው ባለጸጋ ቤተሰብ የምትወለድ ሴት ነበሩ፡፡ በአሉ ከተወለደ በኋላ አባቱ ቤተሰቡን ወደ አዲስ አበባ ለመውሰድ ቢፈልግም ሀሳቡ በእናቱ ቤተሰቦች ሳይደገፍ በመቅረቱ ብቻውን ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሀገሩ ህንድ ጠቅልሎ ገባ፡፡ ሆኖም ለልጁ የሚያስፈልገውን ከማድረግ አልተቆጠበም ነበር፡፡

ከአባቱ ጋር ይህ ነው የሚባል የአባትና ልጅ ግንኙነት ያልነበረው በአሉ በአንድ ወቅት ለሥራ ጉዳይ ወደ ህንድ በተጓዘ ጊዜ አባቱን ለማግኘት ሞክሮ ሳይሳካለት ተመልሷል፡፡

አስር ዓመት ሲሞላው በጉዲፈቻ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የአባቱን ስም ግርማ በሚል አስቀየረው፡፡ ከእናቱ ወንድ አያት ጋር ስለነበረው ቅርበትና ስለ አንድ ጥሩ መምህሩ ከሚናገረው በስተቀር በኢሉባቦር ስለነበረው የልጅነት ጊዜ ብዙም አያወራም፡፡

ባህላዊና ሀይማኖታዊውን የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ካጠናቀቀ በኋላ ልእልት ዘነበ ወርቅ አንደኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በአሉ በትምህርቱ ጎበዝ ነበር፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርቱ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ በኢትዮጵያና እንግሊዝ መንግስታት ጥምረት ይተዳደር በነበረው ጄነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በአሉ ከጋዜጠኝነትና ጸሀፊነት የህይወት ጥሪው ጋር ተገናኘ፡፡ በትምህርት ቤቱ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች እንዴት እንደሚጻፉ ያስተምሩና ያበረታቱት የነበሩት ማርሻል የተባሉ የእንግሊዝኛ መምህሩን ተሰጥኦውን እንዲያውቅ ስለረዱት ያመሰግናቸዋል፡፡

በአሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ከፍተኛ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው የተማሪዎች የሀሳብ መድረክ ለነበረችው “ኒውስ ኤንድ ቪውስ” ጋዜጣ በርካታ ጽሁፎችን ከማበርከቱም በላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖም ሰርቷል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪውን በፖለቲካ ሳይንስና ጋዜጠኝነት ካገኘ በኋላ በጊዜው የመንግስት መገናኛ ብዙሀንን ያስተዳድር በነበረው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥሮ የእንግሊዘኛው እለታዊ ጋዜጣ ኢትዮፕያን ሄራልድ ዜና ዘጋቢ ሆነ፡፡ የዩኒቨርሲቲው “ኒውስ ኤንድ ቪውስ” ዋና አዘጋጅነቱንም ጎን ለጎን ቀጠለ፡፡ በአሉ ሁሌም የንጉሱን አገዛዛና ፖሊሲዎች የሚነቅፉ ጽሁፎችን ይጽፍ ስለነበር ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡

ቆይቶም አሜሪካ በሚገኘው የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርስቲ ሙሉ የነጻ ትምህርት እድል በማግኘቱ በፖለቲካ ሳይንስና ጋዜጠኝነት ሁለተኛ ዲግሪውን ያዘ፡፡ በ1955 ወደ አገሩ በመመለስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር የነበረው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ፡፡

ከ1957 እስከ 1966 በነበሩት ዓመታት ደግሞ የአዲስ ሪፖርተር እና የመነን መጽሄቶች፣ የኢትዮፕያን ሄራልድ እና የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ ፖለቲካዊ ትችቶችን ይጽፍ ለነበረው በአሉ እነዚያ ዓመታት በፈተና የተሞሉ ነበሩ፡፡ አንዴ አዲስ ሪፖርተር መጽሄት ላይ በጻፈው አወዛጋቢ ጽሁፍ ምክንያት ከዋና አዘጋጅነት ሥራው ታግዶ፤ ከቅጣት መልስ ደሞዙ ተቆርጦበታል፡፡

በአሉ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ጊዜ ከጋዜጠኝነት በተጨማሪ ለፈጠራ ድርሰት ጊዜ በመስጠት ከአድማስ ባሻገር እና የህሊና ደውል የተባሉ ሁለት ልቦለዶቹን በቅደም ተከተል በ1962 እና በ1966 አሳተመ፡፡ የጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት የመጨረሻ ዓመቱ በነበረው በ1966 በተከሰተው አብዮት ወቅት አዲስ ዘመን ብቸኛው ታማኝና የማያዳላ የዜና ምንጭ ሆኖ መቆየት ችሏል፡፡

1966 ከመጠናቀቁ በፊት በአሉ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ተሾመ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቋሚ ተጠሪነት ሹመት አገኘ፡፡ በዚያው ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፈጠራ ጽሑፍ አጻጻፍ ተጋባዥ መምህር ሆኖ አስተምሯል፡፡

ምስል አንድ፡ በአሉ ግርማ መካከል ላይ

ደራሲው እና የቀይ ኮከብ ጥሪ የተባሉ ልቦለድ ድርሰቶቹ በ1972፣ ሐዲስ እና ኦሮማይ ደግሞ በ1975 የተጻፉ ናቸው፡፡ ኦሮማይ የጊዜውን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የሚወክሉ ገጸ-ባህሪያት ፈጥሮ የወቅቱን ፖለቲካዊ ምስቅልቅልና ብልሽት በድፍረት የዳሰሰ በኋላም ለደራሲው ደብዛ መጥፋት ምክንያት ሊሆን የበቃ ደፋር ልቦለድ ነው፡፡

በአሉ በኦሮማይ ምክንያት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ፊት ቀርቦ «እንዴት የለውጥ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል መጽሐፍ ትጽፋለህ?» ተብሎ ግሳጼ ተቀብሏል፡፡ እሱ ግን ያለ አንዳች ፍራቻ ለሥራው ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ነበር የተናገረው፡፡ ወዲያውኑ መጽሐፉ ታግዶ ከገበያ ላይ እንዲሰበሰብ ቢደረግም ውስጥ ለውስጥ በስፋት መሰራጨቱን ቀጠለ፡፡ በአሉም «ለውጡን በመክዳት» በሚል ይሰራበት ከነበረው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ኃላፊነቱ ተነሳ፡፡

ይህ ከሆነ አምስት ወራት በኋላ በአሉ የካቲት 1976 አንድ ሐሙስ ዕለት አመሻሽ ላይ ከቤት እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ፡፡ ቤተሰቦቹ መኪናውን ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ደብረ ዘይት መንገድ ላይ አገኙት፡፡ የደርግ መንግስት በአሉን የጠፉ ሰዎች የሚል ዝርዝር ውስጥ ቢያካትተውም፣ ብዙዎች መንግስት ራሱ ጠልፎ ወስዶ እንደገደለው ያምናሉ፡፡

ከበአሉ መጥፋት 25 ዓመታት በኋላ በልጁ መስከረም በአሉ አማካኝነት ታላቁን ጋዜጠኛና ደራሲ የሚዘክር መቀመጫውን አሜሪካ፣ ሚቺጋን ያደረገ «በአሉ ግርማ ፋውንዴሽን» የተሰኘ ተቋም ተመስርቷል፡፡ በ2001 የተመሰረተው ይህ ተቋም በምስራቅ አፍሪካ ትኩረት የተነፈጋቸውን ባለተሰጥኦ ጸሀፍትና ጋዜጠኞችን ለማበረታታት ይተጋል፡፡ ሲጠፋ የ44 ዓመት ጎልማሳ የነበረው በአሉ ግርማ፤ ባለትዳርና የአንዲት ሴትና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበር፡፡

 

ምንጮቻችን፡

ብዙ ወንድማገኘሁ አለሙ:- በሁለት የፖለቲካ ዘመናት ውስጥ ያለፈ ጋዜጠኝነት

Previous article

የምርመራ ጋዜጠኝነት ምንነት

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply