ይማሩ

ስለ ሞባይል ጋዜጠኝነት ማወቅ ያለብን

ይማሩ /MIRH/ 04 ሀምሌ 2014 

በስንታየሁ አባተ 

ይህ ጽሑፍ ስለ ሞባይል ጋዜጠኝነት አጠቃላይ ስዕል ለማስጨበጥ ያለመ ነው፡፡ ስለ ምንነቱ፣ አስፈላጊነቱ፣ አንድ ሰው እንዴት የሞባይል ጋዜጠኛ መሆን እንደሚችል፣ መሳሪያዎቹና የወደፊቱ የሞባይል ጋዜጠኝነት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በመጠኑ ይዳስሳል፡፡

የሞባይል ጋዜጠኝነት ምንነትና እድገቱ

የሞባይል ጋዜጠኝነት ወቅታዊውን የዓለም ፈጣን ለውጥና የመረጃ ፍላጎትን የማስተናገድ ፍላጎት የፈጠረው የብዙሀን መገናኛ ሙያ ዘርፍ ነው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች በፍጥነትና በተከታታይ መስፋፋት ለዘርፉ መከሰት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ የሞባይል ጋዜጠኝነት ማለት የእጅ ስልክ በመጠቀም የዜና ወይም የመረጃ ስብሰባ ስራን ከመከወን እስከ ማሰራጨትና የሰዎችን ግብረመልስ በቀላሉ እዚያው ላይ ማግኘት እስከመቻል ያለውን አዲስ ልምምድ ያካትታል፡፡ ፎቶግራፎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስልክ ይቀረጻሉ፤ የጽሑፍ መረጃዎች እዚያው ላይ ይተየባሉ፣ የምስልና ድምጽ ውህደት ሥራዎችም እዚያው ላይ ያልቃሉ፡፡ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የተለመዱት ሳተላይት የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሳያስፈልጉ በሞባይል ስልክ ብቻ የቀጥታ ስርጭት በቀላሉ ይከናወናል፡፡

በተለይም በ21ኛ ክፍለ ዘመን እያስተዋልን ያለነው የዘመናዊ ስልኮች መበራከትና ዝማኔ፤ ላነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ትልቁን ሚና እየተወጡ ይገኛል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዘመናዊ ስልኮች ጋር እያደገ የመጣው የካሜራ ጥራት፣ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ፈጣን የመቀበል አቅም፣ የባትሪዎች ለብዙ ሰዓታት መቆየት፣ ከፍተኛ ምስል (ፋይል) የመያዝ አቅምና ሌሎችም ለሞባይል ጋዜጠኝነት ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆነ መምጣት ዋና ዋና ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ መተግበሪያዎች በየአገሩ መተዋወቃቸውም የዘርፉ ሚና እንዲጎለብት አግዘዋል፡፡ ስለሆነም ከነባሩ የጋዜጠኝነት አሰራር በተጓዳኝ በቀላሉና ሰዎች በኪሳቸው ይዘውት በሚንቀሳቀሱት የእጅ ስልክ መገልገያነት የሚሰራ የሞባይል ጋዜጠኝነት በሰፊው በመለመድ ላይ ይገኛል፡፡

የሞባይል ጋዜጠኝነት ጥቅም ምንድን ነው?

በነባሩ ጋዜጠኝነት የሥራ ሂደት ውስጥ አንድን የቴሌቪዥን ዜና ወይም ዘገባ ለማጠናቀር ሪፖርተር፣ የካሜራ ባለሙያ (አንዳንድ ጊዜ ረዳት ካሜራ ባለሙያንም ይጨመራል) እና ሹፌርን ከነተሟላ መሳሪያዎቻቸው ለቀናት ወይም ሰዓታት መጠቀምን የግድ ይላል፡፡

ወደ ሞባይል ጋዜጠኝነት ስንመጣ ግን አንድ ዘመናዊ የእጅ ስልክ ያለው ሰው ፎቶግራፎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መቅረጽና በደቂቃዎች ልዩነት ዓለምን መድረስ በሚችሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማሰራጨት ይችላል፡፡

ከዚህ አንጻር የሞባይል ጋዜጠኝነት ነባር ከሚባሉት የጋዜጠኝነት ሥራ ሂደቶች ጋር ሲነፃፀር ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ አንዱ ጥቅም ከካሜራና ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን መሳሪያዎች አንፃር ሲታይ በቀላሉ ሊገዙ በሚችሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚሰራ መሆኑ ነው፡፡ በአንድ የእጅ ስልክ ጥራት ያላቸው ምስሎችና ድምጾችን መቅረፅ መቻል፤ ከዚያም አልፎ የቅንብር ስራን ሰርቶ ለሚመለከተው አካል ማድረስ ወይም ማሰራጨት መቻል ከዋጋ አንፃር ሲሰላ በከፍተኛ ደረጃ ወጪ ይቆጥባል፡፡ አጋዥ የሚባሉ የተወሰኑ መሳሪያዎች ተገዝተው ቢጨመሩ እንኳ ነባሩ የጋዜጠኝነት ሥራ ከሚፈልገው ግብዓትና ከሚጠይቀው ወጪ አንፃር ከፍተኛ አዋጭነት አለው፡፡

በልማዳዊ ጋዜጠኝነት አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሳሪያዎችን የሚያንቀሳቀሱ ባለሙያዎችን ቁጥር በመቀነስም ሆነ በኪስ በሚያዝ የእጅ ስልክ በቀላሉ በመንቀሳቀስ መስራት መቻል ከፍ ያለ ጥቅም አለው፡፡ አንድ ሰው ብቻውን የሚሰራው መሆኑና ብዙ ሰራተኞችን የማስተባበር ድካምን ማስቀረቱ ለሞባይል ጋዜጠኛው የተለጠጠ ነፃነትና ምቾት ይሰጣል፡፡

ለጋዜጠኛው ደኅንነት መረጋገጥ የተለየ አበርክቶም አለው፡፡ ለምሳሌ ጦርነትና ግጭቶች ባሉባቸው ስፍራዎች የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ቡድን ገብቶ ሲሰራ የሚፈጠረውን ተተኳሪነት ይቀንሳል፡፡ አንድ ባለሙያ ሁሉንም መስራት የሚችል መሆኑ በባለሙያ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጥቃት የመቀነስ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ የእጅ ስልክ ለተጠቃሚው እንደ ጓደኛ ቅርብ በመሆኑ የበለጠ አስቻይ ነው፡፡

እንዴት የሞባይል ጋዜጠኛ መሆን ይቻላል?

አንድ ሰው የሞባይል ጋዜጠኛ ለመሆን ቢያንስ የቴክኖሎጂና የጋዜጠኝነት እውቀትና ክህሎቱ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህ የሚረዱ መሟላት የሚገባቸው 12 ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህም ዝግጁነት (ሁሌም ዜና ለመስራት ዝግጁ መሆን)፣ ዜና ለመስራት የሚያስችሉ መሳሪያዎች (ሞባይል፣ እንደ ማይክ፣ መብራትና ትራይፖድ ወይም ስቲክ ያሉ አጋዥ መሳሪያዎች) ሁሌም መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ ሞባይልን ጨምሮ ሌሎች መገልገያ መሳሪያዎች እንዴት እንደሚሰሩ ማወቅ፣ የእጅ ስልክ ባትሪ ሁሌም ሙሉ መሆኑን እርግጠኛ መሆን፣ ባትሪ እያለቀ ከሆነ ለመቆጠብ የበረራ አማራጭ (flight mode) ላይ ማድረግ፣ የሚሰራው ዜና ፕሮዳክሽን እስኪያልቅ የተቀረጹ ግብዓቶች ሁሉ እንዳልጠፉ ማረጋገጥ (የትኛውንም ፋይል አለማጥፋት)፣ ሁሌም ምቹ ከሆነው ስፍራና አውድ ወጥቶ መንቀሳቀስና አዳዲስ ነገሮችን መቃኘት፣ አለመደበቅ (በተቻለ መጠን ዘገባዎችና ቃለመጠይቆች ከስልክ ጥሪና የበይነ መረብ ግንኙነት ይልቅ በአካል ወይም የፊት ለፊት ቃለ መጠይቆች እንዲሆኑ ማድረግ)፣ ሁሌም ዓይንን ክፍት ማድረግ (አዳዲስ ነገሮችን ለማግኘት በማስተዋል ውስጥ መኖር ወይም የጋዜጠኛን አራት ዓይናነት መተግበር)፣ የተሰሩ ዘገባዎች ወይም ያልተሰበሰበ መረጃ ለሰዎች እንዴት ሊቀርብ እንደሚችል ማወቅ፣ ሁሌም የሥራው ሂደት በሚፈለገው መንገድ እየሄደ መሆኑን እርግጠኛ መሆን እንዲሁም ፈጣንና ትጉህ መሆን የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ቀጣዩ የሞባይል ጋዜጠኝነት ዕጣ ፈንታ

የሞባይል ጋዜጠኝነት ከዚህ በኋላ የመጥፋት እድል የለውም፡፡ ይህ ማለት ግን የቀደሙትንና ዛሬም እየተሰራባቸው ያሉ የጋዜጠኝነት ስልቶችን ሙሉ ለሙሉ ይተካል ማለት እንዳልሆነ ዘርፉ ላይ በጥልቀት እየተጻፉ ያሉ ትንታኔዎች ያመለክታሉ፡፡

ይልቁንም ‹‹መደበኛ›› ወይም ቀደምት የሚባሉት የጋዜጠኝነት ሂደቶችና ስልቶች ራሳቸውን ከአዲሱ ጋር እያዋሀዱና እንደየቅርጻቸው ለራሳቸው በሚመች መልኩ እየተጠቀሙበት ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በርካታ የዜና አውታሮች ከመደበኛው የብሮድካስት ወይም የህትመት ይዘት ሥራዎቻቸው ባሻገር ለሚከውኑት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የይዘት ስራ የሞባይል ጋዜጠኝነትን ጥቅም ላይ እያዋሉ ነው፡፡ በዚህ እሳቤ ሲኬድም ሁሉም የየራሳቸው መለያና የተለየ ጥቅም (እድል) አላቸው ማለታችን ነው፡፡

ጋዜጠኝነት የተደራጁና ትርጉም ያላቸውን መረጃዎች ማቅረብ የሚለውን ዋነኛ ይዘቱን ባይለቅም ቅሉ፤ አንዳንዶች ግን ይህን የዘመን ሰጠሽ የቴክኖሎጂዎች ጥቅም በተቃራኒው ተጠቅመው ሀሰተኛ መረጃዎችን በቀላሉ ሊያሰራጩበት እንደሚችሉ እያሰቡም መጓዝ ተገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በኃላፊነት መጠቀምና ራስን እያበቁ መሄድ ሥነምግባራዊ ግዴታ ነው፡፡

 

ምንጮቻችን፡

https://www.movophoto.com/pages/mojo-mobile-journalism

What is mobile journalism?

 

ሪፖርተር ጋዜጣ

Previous article

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply