የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 6 ሀምሌ 2014
በአቢ ፍቃዱ
የኢትዮጵያ ሬዲዮና የጀርመን ድምፅ (ዶቼ ቬለ) በነበራቸው የትብብር ስምምነት መሠረት በቀረበ ጥሪ ተወዳድራ ወደ ጀርመን በመሄድ ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር በላይ ሠርታለች፡፡ በዶቼ ቬለ ቆይታዋ፤ ‹‹የባህል መድረክ›› እና ‹‹ሳይንስና አካባቢ›› የተሰኙ ሁለት ፕሮግራችን እንዲሁም በየዕለቱ በዜና ዝግጅት እና በአንባቢነት ሠርታለች፤ ሰሎሜ ደስታ በላይ፡፡
ሰሎሜ ደስታ በአዲስ አበባ ከተማ በ1958 ተወለደች፡፡ በስብስቴ ነጋሲ ት/ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን፣ እንዲሁም በንፋስ ስልክ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ተምራለች፡፡ የከፍተኛ ትምህርቷን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነጽሁፍ ትምህርት ክፍል በመከታተል የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡
ሰሎሜ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች የአማርኛ ደብተሯ ላይ ‹‹ሳድግ መሆን የምፈልገው›› በሚል ርዕስ በተሰጣት የጽሁፍ የቤት ሥራ በልጅነት ብዕር ያስቀመጠችው አጭሯ ጽሁፍ ‹‹መሆን የምፈልገው ጋዜጠኛ ነው›› የሚል ነበር፡፡ የልጆቻቸውን ደብተር ሰብስበው የማስቀመጥ ልምድ የነበራቸው እናቷ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ኪዳነማርያም ባቆዩላት ደብተር ውስጥ በጽሁፍ ያሰፈረችው ያ ምኞት እንዴት እና ለምን እንደተጠነሰሰ ግን እስካሁን አታውቀውም፡፡
ሰሎሜ አባቷ ይገዟቸው የነበሩ በርካታ የአማርኛ መጻሀፍትን በማንበብ ነው ያደገችው፡፡ በትምህርት ቤት የአማርኛ ክፍለ ጊዜ ከመጽሀፍ ላይ የወደዳችሁትን ጽፋችሁ አምጡ ሲባል እራሷ የሞከረቻቸውን ግጥሞች ክፍል ውስጥ ታቀርብ ነበር፡፡ የሥነጽሁፍ ፍቅር ያደረባት ብትሆንም ‹‹ጋዜጠኛ›› እሆናለሁ ብላ ግን ራሷን አዘጋጅታ አታውቅም፡፡
የጋዜጠኝነት ተሰጥኦ አለሽ ብላ ኢትዮጵያ ሬዲዮ እንድታመለክት የገፋፋቻት ግን አሁን ኑሮዋን አሜሪካ ያደረገችውና የኦሮምኛ ክፍል ባልደረባ የነበረችው ፀሐይ ወዳጆ ነች፡፡ በአጋጣሚ በዩኒቨርስቲ ተመሣሣይ ኮርስ በሚወስዱበት ወቅት ስለዕቁብ፣ እድር እና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሕንጻ አሠራር፣ ስለ ጉልላቱ፣ የበሮቹ ብዛት፣ የውስጥ ክፍሎቹ ስያሜና ትርጉም አስመልክታ ስታቀርብ የተመለከተችው ፀሐይ ‹‹ድምፅሽ ለሬዲዮ ይመቻል፤ የሀሳብ ጥንካሬሽም ለሬድዮ የተመቸ ስለሆነ እባክሽ አመልክቺ›› እያለች ገፋፋቻት፡፡ ማስታወቂያ ሲወጣም አቅጣጫ ነግራ እንድትሄድ ያደረገቻት እሷ ነበረች፡፡ ከዚያም ድምጽና ብዕሯን አስፈትሻ የቀረበውን የፅሁፍና የቃል ፈተና በማለፍ በ1982 መጨረሻ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ባልደረባ ሆነች፡፡
ከተቀጠረችበት የስርጭት አስፈጻሚነት በተጨማሪ ሰኞ፣ ማክሰኞና ሐሙስ ይቀርብ በነበረውና ‹‹ማለዳ›› በተሰኘው ፕሮግራም፤ እንዲሁም በተለየ ሁኔታ በፍቅር ታዘጋጀው በነበረው የኪነጥበባት ምሽት ፕሮግራም ላይ ተመድባ መሥራት ጀመረች፡፡ ከሐምሌ 1984 ጀምሮ የተተከለውን የቅዳሜ ጠዋት ‹‹የሴቶች መድረክ››ም ታዘጋጅ ነበር፡፡
በ1986 የሬዲዮ ፕሮግራሞችና የዜና አቀራረብ እንዲሻሻል የሚያስችል የውሳኔ ሀሳቦች እንዲያቀርብ በተቋቋመውና በእውቁ ጋዜጣኛ ዳሪዮስ ሞዲ ሰብሳቢነት ሲመራ በነበረው ኮሚቴ ውስጥ ተመድባ የራሷን አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ በዚያ ጊዜ የቀረበው የፕሮግራም አቀራረብ ማሻሻያ እስከዛሬ ድረስ በአየር ላይ ያሉ ፕሮግራሞች የሚተገብሩት ሆኖ ዘልቋል፡፡
ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ፕሮግራሞች በሦስት ዘርፍ እንዲመደቡ ሲደረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሆና ተመደበች፡፡ በዘርፉ የተጠቃለሉ የሰባት ፕሮግራሞች አርታዒ ከመሆን በተጨማሪ በ‹‹በሕይወት ዙሪያና›› በሴቶች መድረክ ፕሮግራም ዝግጅት ትሳተፍ ነበር፡፡ በ1991 በተደረገው የአሠራር ለውጥ ደግሞ ፕሮግራሞች በመዝናኛና ትምህርታዊ ዘርፎች ሲከፈሉ 15 ፕሮግራሞችን የያዘውን ትምህርታዊ ዘርፍ ለሁለት ዓመት ገደማ ስትመራ ቆይታ ለሌላ ኃላፊነት ታጨች፡፡
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ታሪክ የመጀመሪያ ኤፍ.ኤም. ጣቢያ የሆነው ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 እንዲቋቋም ሲወሰን ከፕሮግራሞች ቀረጻ አንስቶ ጣቢያውን ግንቦት 27 ቀን 1992 በማስጀመርና ለሁለት ዓመት ያህል በማስተባበር ሠርታለች፡፡
ምሰል አንድ፡ ሰሎሜ ደስታ በስራ ላይ
ሰሎሜ የኢትዮጵያ ሬዲዮና የጀርመን ድምፅ (ዶቼ ቬለ) በነበራቸው ስምምነት መሰረት ለቀረበ ጥሪ ተወዳድራ ወደ ጀርመን በመሄድ ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር በላይ ሰርታለች፡፡ በ1997 ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ለአገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነበር፡፡ ወደ ኤፍ. ኤም. አስተባባሪነት እንድትመለስ ከሬዲዮ አመራር ከፍተኛ ግፊት ቢደረግባትም በጀርመን ያዳበረችውን ዜና የመሥራት ክህሎት የበለጠ ለማጎልበት ዜና ፋይል እንድትመደብ ያደረገቸው ውትወታ ተቀባይነት አግኝቶ ከመጋቢት 1997 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ሥራ ተመለሰች፡፡
ሆኖም የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ የመጣው የመገናኛ ብዙሀን አፈናና ከሙያ ሥነምግባር ውጪ በሚከናወኑ ተግባራት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆኗ በደረሱባት በርካታ ጫናዎችና ያለሥራ የመቀመጥ ቅጣት ሳቢያ በነሐሴ 1998 መጨረሻ መልቀቂያ ጠይቃ ከምትወደው ሥራዋ ተለየች፡፡
በ1999 ግንቦት ወር ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር በመግባት በአማርኛ፣ አፋርኛ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች ሲዘጋጁ የነበሩ ፕሮግራሞች አርታዒ ሆነች፡፡ ከከፍተኛ አርታዒነቷ በተጨማሪ ድርጅቱ በሚያሳትማቸው የሕትመት ውጤቶች እና ሲያዘጋጃቸው በነበሩ ተከታታይ የሬዲዮ ተውኔቶች ላይ ሙያዊ አስተያየት በመስጠትና በሌሎች ሥራዎች በመሳተፍ አገልግላለች፡፡
ሰሎሜ ምቹ የነበረውን የፖፕሌሽን ሚደያ ሴንተር የስድስት ዓመት ቆይታዋን የተወችው የተሻለ የሥራ ዕድል በማግኘቷ ነበር፡፡ በመላው ዓለም ቅርንጫፎች የነበረውና በጊዜው ኢትዮጵያንም 26ኛ አገር በማድረግ የመዘገበው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የግሎባል ሚዲያ ኢንስትቲዩት የኢትዮጵያ ኤዲተር ሆና ተቀጠረች፡፡ የድርጅቱ ዓላማ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሴቶች የራሳቸውን እና የህብረተሰባቸውን ታሪክ እንዲጽፉ ማድረግ ነው፡፡ የሚጻፉ ታሪኮችና ዜናዎችም በድርጅቱ ዌብሳይት ላይ ይጫናሉ፡፡ በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ባህር ዳርና አሌልቱ የሚገኙ ሴቶች ልጆችን ዒላማ ያደረገው ይህ ፕሮጀክት ከባህር ዳር ውጪ ባሉት ሦስት ከተሞች ስልጠና በመስጠት ወጣቶቹን ወደሥራ የማስገባት ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ ሰሎሜ እንደምትለው በነበረው አፋኝ ሕግ ምክንያት ድርጅቱ በብሮድካስት ባለስልጣንም ሆነ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገብ ባለመቻሉ የተጀመረው ፕሮጀክቱ በአጭር ቀርቷል፡፡
ለሰባት ወራት የቆየው የሰሎሜ ኮንትራት ከተቋረጠ በኋላ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር የተያያዙ የግል ሥራዎችን እስከ ታህሳስ 2012 ድረስ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከተጠቀሰው ጊዜ እስከ ሰኔ 2013 ድረስ ደግሞ መቀመጫውን ናይሮቢ ያደረገው የኢንተርኒውስ ተቀጣሪ በመሆን በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የሞኒተሪንግ ዳይሬክቶሬት ውስጥ በማማከር፣ በአርታዒነትና በቀጥታ ሥራ ላይ ተሳታፊ በመሆን አገልግላለች፡፡
ሰሎሜ በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ የበጎ ፈቃድ አስተዋጽኦ በማድረግ ትደሰታለች፡፡ በነበረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሕግ ምክንያት የተዘጋውና የመቀጠል እድል ቢገጥመው ከፍተኛ ሥራ ማከናወን ይችል በነበረው የኢትዮጵያ ኮንሱዩመር ፕሮቴክሽን አሶሴሽን ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና የቦርድ ሰብሳቢ ሆና ሰርታለች፡፡ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ተባባሪ አባል በመሆን በተለይ በሕጉ ምክንያት እንቅስቃሴው ሲስተጓጎል በሚያዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰብ ተግባራት ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡
ሰሎሜ ባለፉት አስር ዓመታት ጊዜዋን፣ ዕውቀቷንና ገንዘቧን በማፍሰስ የኢትዮጵያ ሴት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማኅበር ሳይዘጋ እንዲቆይ ካደረጉት አባላት መካከል አንዷ ነች፡፡ ከፍተኛ መስዋዕትነትን በመክፈል ከሰባት በላይ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በውጤታማናት አጠናቃ ለአዲስ የሥራ አመራር ቦርድ ያስረከበችው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር፡፡ ለሠብዓዊ መብቶችና ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት መከበር የሚሰራው የዓለም አቀፉ ሶሮፖቶሚስት የኢትዮጵያ ክለብም አባልና የቦርድ ጸሐፊ በመሆን በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ከክለቡ አባላት ጋር በመሆን በሚያዋጡት ገንዘብ እጅግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሴቶችና ልጃገረዶችን ይረዳሉ፡፡
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ ስልጠና በመውሰድ ከ25 በላይ ሠርተፍኬቶችን የሰበሰበችው ሰሎሜ ባለትዳርና በሥራ ዓለም የተሰማሩ የአንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ እናት ናት፡፡
የመረጃ ምንጭ
ከሰሎሜ ደስታ ጋር የተደረገ ቃለ- ምልልስ
Comments