የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ሰለሞን ዴሬሳ፡ ዘርፈ ብዙው የሙያ ባለቤት

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 9 መስከረም 2015

በመቅደስ ደምስ

ሰሎሞን ዴሬሳ ውልደቱ በ1929 ወይም 1930 በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ አቅራቢያ ጩታ በተባለች መንደር ነው፡፡ ሰሎሞን የተወለደበትን ዓመትና ዕለት እቅጩን አያውቀውም። እናቱ ወይዘሮ የሺመቤት ዴሬሳ አመንቴ፤ አባቱ ደግሞ አቶ ደንኪ ሊንጊ ይባላሉ፡፡ ለእናቱ የበኩር ልጅ የሆነው ሰሎሞን መጠሪያውን ያደረገው በእናቱ አባት በብላታ ዴሬሳ አመንቴ ነው፡፡

ሰለሞን እውቀትን ፍለጋ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ግጥም የፃፈላትን የትውልድ መንደሩን የለቀቀው ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ይኖሩ ወደ ነበሩት ዘመዶቹ ከመጣ በኋላ ልእልት ዘነበወርቅ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ሰለሞን በታዳጊነቱ የትምህርት አቀባበሉ እምብዛም ነበር፡፡ በእድሜ በእጅጉ ከሚበልጡት ተማሪዎች ጋር መማሩና ቤተሰቡ ያላወቀለት የእይታ ችግር በትምህርቱ ደካማ እንዳደረገው ራሱ ይናገራል፡፡ ከዛም በላይ ፈሪና ድንጉጥ ነበር፡፡ ስለሆነም ከልእልት ዘነበወርቅ ትምህርት ቤት፣ ‹‹ባላባት›› ይባል ወደነበረው የአሁኑ መድሀኒዓለም ትምህርት ቤት ተዘዋወረ፡፡

 

ምስል አንድ፡- ሰሎሞን ዴሬሳ

የነበረበት ችግር ሊፈታ ስላልቻለ ትምህርቱን ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ቀየረ፡፡ በወቅቱ ብዙዎች ‹‹ትምህርት የማይገባው›› ይሉት ነበር፡፡ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መልካም መምህር ገጥመውት ፍርሀቱ እንደጉም ተነነ፡፡ ለእይታ ችግሩም መነጽር መጠቀም ጀመረ፡፡ ይሄኔ ሰሎሞን በአንድ ወር ከ15 ቀን ጊዜ ውስጥ አማርኛ ፊደል ማንበብ ቻለ፡፡

ቤተሰቦቹና መምህራኑ መሻሻሉን ሲያዩ ይማርበት ከነበረው አንደኛ ክፍል አስወጥተው ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ሰባተኛ ክፍል አስገቡት፡፡ ትምህርቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚሰጥበት ክፍል ያለእድሜና የትምህርት ደረጃው ስለገባ ትምህርቱ ከበደው፡፡ እንደ ደካማ ተማሪ ተቆጠረ፡፡ ከትምህርት ቤቱ የመባረር ስጋትም ተደቀነበት፡፡ ስለዚህ በተለየ ትጋት ማጥናት ነበረበት፡፡ በርትቶ አጠና፡፡ በኋላም ጥሩ ውጤት ማምጣት ቻለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፍልስፍናና ስነ-ጽሁፍ ማጥናት ጀመረ፡፡ ይህ ሲሆን ገና 16 ዓመቱ ነበር፡፡

በትርፍ ጊዜው በወቅቱ ሬዲዮ አዲስ አበባ ይባል በነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ በሙዚቃ ማጫወትና የእንግሊዘኛ ዜና አንባቢነት በ450 ብር ለሶስት ወራት ሰራ፡፡ ትምህርቱን እየተማረና በኢትዮጵያ ሬዲዮ እየሰራ እያለ ፈረንሳይ ሀገር የትምህርት እድል አገኘ፡፡

በኋላም ለአንድ ሰዓሊ ጓደኛው ሰርግ ሚዜነት አሜሪካ ሄዶ እዛው ቀረ፡፡ አሜሪካ ከሰራቸው ስራዎች መካከል  በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ አማርኛ ቋንቋ ማስተማር፤ በኒውዮርክ ከተማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፈረንሳይኛ ቋንቋ ወደ እንግሊዘኛ የመተርጎም ስራና በመንግስታቱ ድርጅት ራዲዮ ጣቢያ ማገልገል ይገኙበታል።

በእዚህ መሀል የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ከአሜሪካ ሀገር የቴክኒክ ባለሙያ ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣ፡፡ የቋንቋ ቸሎታ መሰረታዊ ስለነበርና ሰሎሞን አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን በመቻሉ አመልክቶ ተሳካለት፡፡ እናም ወደሀገሩ ተመልሶ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ መስራት ጀመረ፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ብዙ ልምድ ቀስሟል፤ ህዝብንም አገልግሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆኖም ሰርቷል፡፡

በተጨማሪም ሰሎሞን ለልዩ ልዩ የህትመት መገናኛ ብዙሀን ይጽፍ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል መነን፣ አዲስ ሪፖርተር፣ ኢትዮጵያን ኦብዘርቨር እና ሌሎች የአማርኛና የእንግሊዘኛ ህትመቶች ይገኙበታል፡፡ በጽሁፎቹም የጋዜጠኝነትና የስነ-ፅሑፍ ችሎታውን ይበልጥ ማስመስከር ቻለ፡፡ በተለይም በ1966 አብዮት ዋዜማ የነበረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አለመረጋጋት የሚመረምሩ ጽሁፎችን ከገዳሙ አብርሀም ጋር በጋራ በመሆን አዲስ ሪፖርተር መጽሄት ላይ ያወጣ ነበር፡፡ እነኚህ ፅሁፎቹ ብዙዎችን ያስደነቁና ሰሎሞን የተዋጣለት ሃያሲ መሆኑን ያረጋገጡ ነበሩ፡፡

ሰሎሞን በ1965 ዓለም አቀፍ የፀሃፊያን ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ አሜሪካ አይዋ ዩኒቨርስቲ ባቀናበት አጋጣሚ ከልጁ እናት ጋር ተዋውቆ ልጁ ገላኔ ተወለደች። የልጁ መወለድ ያቋረጠውን ትምህርት እንዲጨርስ እድል ሰጠው፡፡ ከዛም እዛው በተማረበት ሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ የኮምፓራቲቭ ሪሊጅን (የሃይማኖቶች ንፅፅር) አስተማሪ ሆነ፡፡ በበርካታ የትምህርት ተቋማትም አስተምሯል፡፡

ሰለሞን በ1965 ወደ አሜሪካ እንደተጓዘ በኢትዮጵያ የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ሀገሩ መመለስ ቢፈልግም በሁኔታዎች ምክንያት ባለበት መቅረትን መረጠ። በደርግ ስርዓት ወቅት ስለሀገሩ ከመገናኛ ብዙኃን ከሚሰማው በስተቀር ሀገሩን አይቶ የማያውቀው ሰሎሞን፤ ወደሀገሩ የመጣው ደርግ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ነበር፡፡ በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ ለአድናቂዎቹ ግጥሞቹን አንብቧል።

ሰለሞን ያለው የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ቢሆንም በማስተማሩ ውስጥ ራሱን እያስተማረ የመጣና የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ጭምር ያስተምርና ያማክር የነበረ ሰው ነው፡፡ በአሜሪካ ኑሮው ከስነ-ጽሁፍ ይልቅ ወደ ፍልስፍና ያደላ ነበር። የመምህርነትና ስነ-ጽሁፍ ስራውን አብሮ ማስኬድ አስቸግሮት ነበር፡፡

ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ የስነ-ጥበብ ሃያሲ፣ ተፈላሳፊ፣ መምህርና አማካሪው ሰለሞን ዴሬሳ በባህርይው ግልፅ፣ ከፍተኛ የማድመጥ ክህሎት ያለው፣ የንባብ ሰው፣ ጥያቄ የሚያጭር ማንነት ባለቤትና ሙግትና ተጠየቅን የሚወድ ሰው እንደነበር ይነገርለታል፡፡

እዛው በስደት በኖረባት አሜሪካ ለሰባት ወራት ታሞ አልጋ ላይ ከቆየ በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 2010 በሰማንያ ዓመት ዕድሜው አረፈ። ሰሎሞን በኋላ ላይ ከተለያት አሜሪካዊት ባለቤቱ አንድ ሴት ልጅ ስትኖረው ሌላ አንድ ልጅም አሳድጓል፡፡

ምንጮቻችን፡

ሰለሞን ዴሬሳ፣ የማይዳሰስ ውብ ቅርፅ

 

ሙሉጌታ ሉሌ፡ ከቅድመ 1966 እስከ ድህረ 1983 የዘለቀ ጋዜጠኝነት

Previous article

የሸዋሉል መንግስቱ፡ የትግል ዘመን ገጣሚና ደራሲ ጋዜጠኛ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply