የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ሰለሞን ተሰማ፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ስፖርት ጋዜጠኛ

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 10 መስከረም 2015

በመቅደስ ደምስ

በርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች ‹‹የሙያ አባታችን ነው›› ይሉታል። እንደ ተራራ የገዘፈን ውጣ ውረድ አልፎ ለስኬት የበቃ ታታሪ ባለሙያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት አባት ሰለሞን ተሰማ፡፡

ሰለሞን ተሰማ በጥር ወር 1926 በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ፡፡ እስከ 15 ዓመቱ ድረስ ላዛሪስት ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ለስፖርት ልዩ ፍቅር የነበረው ሰለሞን የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር። በአዲስ አበባ ሜዳዎች ላይ የሚደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ ታዳጊው ሰለሞን ስለግጥሚያዎቹ ዘገባ ያቀርብ ነበር፡፡ ዘገባዎቹም ከእድሜው አንጻር የሚደነቁና ታላላቆቹን ሳይቀር የሚያስደምሙ ነበሩ፡፡

 

ምስል አንድ፡- ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ

ሰለሞን በልጅነቱ ያሳለፈው ህይወት ፈተና የበዛበት ነበር፡፡ በታዳጊነት እድሜው አባቱን በሞት በማጣቱ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት ወደቀበት፡፡ እናም የስፖርት ጋዜጠኛ የመሆን ምኞቱን ትቶ በሬዲዮ ኦፕሬተርነት ክብር ዘበኛ ሰራዊት ውስጥ ተቀጠረ፡፡ በክብር ዘበኛ ለአምስት ዓመታት ያህል ከሰራ በኋላ ወደ ቴሌኮሙዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ተዘዋውሮ ለሰባት ዓመታት ያህል አገልግሏል። በእነኚህ ዓመታት ውስጥ ግን የስፖርት ጋዜጠኝነት ህልሙን የሚያሳካበትን መንገድ ከመፈለግ አልቦዘነም ነበር፡፡

በኋላም በአጋጣሚ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሲዘዋወር ሰለሞንና የልጅነት ሕልሙ ተገናኙ፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ታዋቂ የሆነባቸውን ስራዎቹን ማቅረቡን ተያያዘው። የሰለሞን ዘገባዎች በዘመኑ ጋዜጦች ይታተሙ ጀመር፡፡ ከጋዜጦቹ መካከል አንዱ በሆነውና በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ በሚነበበው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የ‹‹ስፖርት ፋና›› የተሰኘ አምድ ላይ ዘገባዎቹ ይቀርቡ ጀመር፡፡ በተመሳሳይ ‹‹ብስራተ ወንጌል የምስራች ድምፅ›› የሬዲዮ ጣቢያ ላይ የአየር ሰአት ተሰጥቶት ማራኪና በሳል ዘገባዎቹን ለአድማጭ ማድረስ ጀመረ፡፡ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን የስፖርት ፕሮግራም ስርጭት የተጀመረው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰለሞን አማካኝነት ነበር፡፡ በዘመኑ ለስፖርት ባይተዋር የነበረው ህዝብ የሰለሞንን ዘገባዎች በጉጉት ይጠብቅ ጀመር፡፡ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም ሰለሞንን የራሳቸው ሊያደርጉት ተፎካከሩ፡፡

ሰለሞን የየቅል ባህርያት ባሏቸው በህትመትና የአየር ሥርጭት ብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች ላይ በብቃት መስራት መቻሉ በርካቶችን ያስገርም ነበር፡፡ ልቡ ለስፖርቱ የተሰጠ ነውና ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎች ባልነበሩበት ዘመን ከወቅቱ የቀደመ ስራ መስራት ችሏል፡፡ ለስፖርትና ስፖርት ዘገባ የነበረው ፍቅር የስኬቱ ሁሉ መሰረት ነበር፡፡

ሙያዊ ፍቅሩን ከሚገልጹት አጋጣሚዎች መካከል የጋብቻው እለት ስታዲዮም መገኘቱ አንዱ ነበር፡፡ ሰለሞን ጋብቻውን በፈፀመበት ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር ያደረገውን ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡

ሌላው የሰለሞን ልዩ የሙያ ክህሎት የስፖርት ዘገባውን ልዩ አድርጎ ማቅረቡ ነበር፡፡ ዘገባው ስለ ስፖርት ብቻ አይሆንም፡፡ ከስፖርት ውጭ ያለው የስፖርተኞቹን ሕይወት ጭምር ይዳስሳል፡፡

ኢትዮጵያ ራሷ አዘጋጅታ ዋንጫውንም ያነሳችበትን ሦስተኛውን የአፍሪቃ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የድል ዜና በማራኪ አቀራረብ ለሕዝብ ያደረሰው ሰለሞን ተሰማ ነበር፡፡ ዘገባው ዛሬም ድረስ በብዙዎች ሕሊና ውስጥ እንዳለ አለ።

በአትሌቲክሱ ዘርፍ ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1952 ሮም ላይ በባዶ እግሩ አስደናቂ ገድል ሰርቶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የተደረገለት አቀባበል ተደጋግሞ ቢታይ እንዳይሰለች ያደረገው የሰለሞን ተሰማ ልዩ አቀራረብ ነበር፡፡ በዚህም ብዙዎች ‹‹የመረጃ ፍሰት ስርዓት ባልነበረበት ወቅት የስፖርት ጋዜጠኝነትን ጠንቅቆ የተረዳ ሰው›› በማለት ሰለሞንን ያሞካሹታል፡፡

ሰለሞን በርካታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ዘግቧል፡፡ ከዘገባው ባሻገር የስፖርት ሰዎችን በማበረታታት ስሙ በበጎ ይነሳል፡፡ በዚህ ረገድ በአትሌቲክሱ ታሪክ የማይረሳው ጉልህ ሚና ነበረው፡፡ በ1961 በተካሄደው የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ የማራቶን ውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን ሰለሞን በብስክሌት እየተከተለ ሲያበረታታው ነበር፡፡ ራሱ ማሞ ሰለሞን ለድሉ የነበረውን አስተዋፅኦ ሲናገር ‹‹ሰለሞን ከጀርባዬ በመሆን እየተከተለ ያበረታታኝ ነበር። ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደሚቀረኝና እንዴት መጨረስ እንዳለብኝ በመምከር ለድሌ ወሳኙን ድርሻ ተወጥቷል፡፡›› ብሏል፡፡ ሰለሞን ከማሞ በተጨማሪ በእነ አበበ ቢቂላና ምሩፅ ይፍጠር ድል ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደነበረው፤ ከኢትዮጵያ አልፈው ‹‹የአፍሪካ ስፖርት አባት›› እየተባሉ የሚጠሩት አንጋፋው ባለሙያ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መስክረውለታል፡፡

ሰለሞን ለኢትዮጵያ ስፖርት የዋለው ውለታ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎች ሀገራት ስፖርትና ስፖርተኞች ላይ የሚመለከታቸውን በጎ ነገሮች ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የሚጥር ሰው ነበር፡፡ ሰለሞን ከእርሱ በኋላ ወደ ሙያው ለመጡ እንደ አንጋፋውና ተወዳጁ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ላሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስፖርት ጋዜጠኞች መሰረታቸው የሆነ ባለሙያ ነበር። የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርም መስራች ነው፡፡

ሰለሞን በጋዜጠኝቱ ይበልጥ ይታወቅ እንጂ በኪነ-ጥበብ ዘርፍም እውቅና ያስገኙለትን ሥራዎች ሰርቷል፡፡ ግጥም እየጻፈ በሙዚቃው መድረክ አንቱ ለተባሉት ለጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሂሩት በቀለና ለሌሎች በርካታ ድምጻዊያን ሰጥቷል፡፡ ለአብነት ያክል የጥላሁን ገሰሰ ‹‹ሞናሊዛ›› እና ‹‹ቀጠሮ ይከበር››፣ የብዙነሽ በቀለ ‹‹የእናት ውለታዋ›› የሰለሞን ሥራዎች ናቸው፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ስለ ሰለሞን የጋዜጠኝነትና የግጥም ችሎታ ሲናገር ‹‹ …ሰለሞን…የሰውን ልብ እንደፈለገ በቃላት የሚሰቅልና የሚያወርድ ሰው ነበር …›› ብሎ ነበር። ድምጻዊያንና የሙዚቃ ባለሙያዎች የሚተዋወቁበት ‹‹እናስተዋውቃችሁ›› የተሰኘ መጽሔት በማሳተም አጫጭር የህይወት ታሪካቸውንና ምስላቸውን ያወጣም ነበር፡፡

ይህ ዘርፈ ብዙ የሙያ ባለቤት ብዙ መስራት በሚችልበት እድሜው ገና በ46 ዓመቱ በ1972 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ምንጮቻችን፡

 

 

 

 

 

ከፋለ ማሞ፡ የመብትና የነጻነት ተሟጋች ጋዜጠኛ

Previous article

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply