የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 13 ሚያዚያ 2022
በፍቃዱ ዓለሙ
በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ (ብሮድካስተር)
በኢትዮጵያ የብሮድካት ሚዲያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሮማን ወርቅ ካሳሁን ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ ሮማን ወርቅ ትውልዳቸው አዲስ አበባ ሲሆን በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት በመማር የዕውቀትን አለም ተቀላቀሉ፡፡ ቀጥሎም በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብተው የተማሩ ሲሆን በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው በጣም ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ በወቅቱ ሲያስተምሯቸው የነበሩ መምህራን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የዘመናዊ ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው በንባብ እና በጥናት የተፈጥሮ ችሎታቸውን ካዳበሩ በኋላ በ1939 ዓ.ም በወቅቱ የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ መሥሪያ ቤት ይባል በነበረው መንግስታዊ ተቋም የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ፡፡
ሮማን ወርቅ ካሳሁን በሀገራችን ብዙም ሴቶች ይሳተፉበት ባልነበረው በዚያ ዘመን የጋዜጠኛነት ሙያ ፈር ቀዳጅ በመሆን ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በሬድዮ ዘርፍ በዋናነት የሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ፣ በዜና አንባቢነት የሠሩ ሲሆን ከሬዲዮ በተጨማሪ በኅትመት መገናኛ ብዙሃን ዘርፍም የሴቶችን ጉዳይ በተመለከተ ለመነን መጽሔት እና ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን አበርክተዋል።
ሮማን ወርቅ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆኑ ደራሲም ነበሩ። ሦስት ድርሰት ሥራዎቻቸውን ለአንባቢያን አበርክተዋል፡፡ ከሥራዎቻቸው መካከልም “ትዳር በዘዴ”፣ “ማኅቶተ ጥበብ” እና “የሕይወት ጓደኛ” የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኅትመት ብርሃን ካዩላቸው ሦስት ሥራዎቻቸው በተጨማሪ በሴቶች ዙሪያ፣ በትዳር እና በኢኮኖሚክስ መሰል ጉዳዮች የሚያተኩሩ ሌሎች ዐሥር የሚጠጉ ያልታተሙ የጽሑፍ ሥራዎችን ትተው እንዳለፉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከንባብና ከጽሑፍ ጋር ተዋደው ኖሩት ጋዜጠኛ ሮማን ወርቅ አብዛኛውን የጐልማሳነት ሕይወታቸውን ያለሕይወት አጋር ማሳለፋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሮማን ወርቅ ካሣሁን ከጋዜጠኝነታቸው እና ከደራሲነታቸው በተጨማሪ የሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት እና YWCAን ጨምሮ በተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ በዚህም በጋዜጠኝነት እና ከደራሲነት በተጨማሪ በሕይወት ዘመናቸው ላስመዘገቧቸው ስኬቶች ኹለት ታላላቅ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል። ከዚህም ሌላ በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንደገና መንግሥት የወርቅ ሜዳሊያ የሸለማቸው ሲሆን በ1956 ዓ.ም እንዲሁ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ለሕትመቶቻቸው እውቅና በመስጠት የብር ሜዳሊያ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት የህትመት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ለበርካታ ሴት አጋሮቻቸው አርአያ የነበሩት ሮማን ወርቅ ካሳሁን ጥር 23 ቀን 1964ዓ.ም በ50 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው በቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ምንጮቻችን
- The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia,በመሠረት ቸኮል (ደ/ር), 2013 G.C
- ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ ያልታተመ ጽሑፍ
Comments