ይህ መመሪያ በኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) የሥርዓተ–ፆታ እኩልነትና ሴቶችን የማብቃት ክፍል (UN Women) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ጋዜጠኞች በግጭት ወቅት የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮችን ለማካተት መከተል ስለሚገባቸው መርሆዎች በዝርዝር የያዘ መመሪያ ነው። በተጨማሪም መመሪያው መገናኝ ብዙሃን በግጭት ዘገባ ወቅት ወይም ደግሞ በመደበኛው ጊዜ ስለሴቶች በትክክለኛው መልኩ እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው በጥልቀት ያስረዳል፡፡ በተለይ በዘገባዎቻቸው ወቅት ማከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት እና ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ያትታል፡፡ በአጠቃላይ ይህ “ሥርዓተ ፆታን ያገናዘበ የግጭት ወቅት ዘገባ መመሪያ” ጋዜጠኞች በግጭት ወቅት በተቻለ መጠን ትክክለኛ ዘገባ እንዲሠሩ እገዛ ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ ነው።
የዚህ መመሪያ ዓላማ ምንድን ነው?
ይህ መመሪያ ጋዜጠኞች ግጭት ተኮር ዘገባ በሚያዘጋጁበት ጊዜ ሴቶች እና ወንዶችን በተገቢው ሁኔታ እና የጋዜጠኝነት ሥነ–ምግባር በተሞላበት መልኩ እንዲያቀርቡ እና እንዲወክሉ ለማገዝ ያለመ ነው። እንዲሁም መመሪያው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከግጭት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዘገባዎች በሚያጠናቅሩበት ጊዜ ስርአተ–ፆታ ላይ የተመረኮዙ ጅምላ ፍርጃዎችን፣ የተዛቡ ስርአተ–ፆታዊ አስተሳሰቦችን እና ስርዓተ–ፆታዊ አድልዎችን መቀነስ እንዲችሉ እገዛ ያደርጋል። በተጨማሪም ሥርዓተ–ፆታን ያማከለ የግጭት ዘገባ ምንነት እና አስፈላጊነት እንዲሁም ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የግጭት ዘገባ አቀራረቦችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ጠቃሚ ማብራሪያዎችን ይሰጣል።
ሙሉውን መመሪያ ከዚህ በታች ማግኘት ይችላሉ፡፡
Comments