የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ማዕረጉ በዛብህ: ጋዜጠኛ፣ መምህርና ዲፕሎማት

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 28 ጥቅምት 2015

በአቢ ፍቃዱ

ማዕረጉ በዛብህ ከአባቱ ከፊታውራሪ በዛብህ ይማምና ከእናቱ ከወይዘሮ ይምባወርቅ ሺበሺ በ1930 በወሎ ክፍለ ሀገር፣ በዋግ አውራጃ ኮረም ከተማ ተወለደ፡፡ ማዕረጉ ገና ሦስት ዓመት ሳይሞላው ፊታውራሪ በዛብህ ከፋሽስት ኢጣሊያ ጋር በአርበኝነት ሲዋጉ ተሰውተዋል፡፡

ማዕረጉ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በመቀሌና በአዲስ አበባ ነበር፤ በአጼ ዮሐንስ አራተኛ፣ በኮከበ ጽባህና በአስፋወሰን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተምሯል፡ ከዚያም ከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ቀጥሎ የመጀመሪያ ዲግሪውን በካፒታል ሳይንስ አግኝቷል፡፡

ማዕረጉ በመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድቤት በአስተርጓሚነት፣ ቀጥሎም በአማካሪነትና በማስታወቂያ ክፍል በትርጉም ስራ አገልግሏል፡፡ የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊው ከነበረ የታወቀ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ማርቲን ፍሌተር ጋር በመስራቱ የጋዜጠኝነት ሙያን ለመለማመድ እንዳስቻለው ይናገራል፡፡

በወቅቱ ዜና ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ መተርጎምን ጨምሮ አልፎ አልፎም በእንግሊዘኛ ጹሑፎችን እንዲጽፍ ከፍተኛ እገዛ ያደርግለት እንደነበረ ማዕረጉ ያስታውሳል፡፡ በጄኔራል ዊንጌት ቆይታው አማርኛ መምህሩ የነበሩት አቶ ክፍሌ ወርቁ ካሳደሩበት የሥነ-ጽሑፍ ፍቅር ጋር ተዳምሮ ማርቲን ፍሌተር የጋዜጠኝነት ሙያ ዝንባሌው እንዲያድግ ማድረጋቸውን ይገልጻል፡፡ ይህም መነሳሳት ገና በወጣትነቱ ለጋዜጦች መጣጥፎችን ለማበርከት አስችሎታል፡፡

ማዕረጉ በዛብህ የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ጣሊያን በማቅናት ኔፕልስ በሚገኘው ኢንስቱትዩት ኦፍ ኦርየንታይል ስተዲስ በመግባት አረብኛን ጨምሮ የሴሚቲክ ቋንቋዎችንና ባህሎችን ማጥናት ጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለትምህርቱ ብዙም ፍላጎት ሊያድርበት አልቻለም፡፡ ስለዚህ የሚፈልገውንና የሚወደውን ትምህርት ለማጥናት ሲያፈላልግ ቦሎኛ የሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መዳረሻው ሆነ፡፡ እዚያም በከፍተኛ ዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪ ጥናቱን አከናወነ፡፡ በዚያው በአውሮፓ ማዕረጉ  ሁለተኛውን ዓመት የማስተርስ ትምህርታቸውን ጄኔቫ  በሚገኘው  በዌብስተር ዩንቨርስቲ  አጠናቀው  በአለም አቀፍ ግንኙነት ለመመረቅ ችለዋል፡፡

ማዕረጉ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ሥራ ፍለጋ የመጀመሪያ ማመልከቻውን ያስገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር፡፡ ሆኖም መሥሪያ ቤቱ እሱን ለመቅጠር ክፍት ቦታ እንደሌለው አሳወቀው፡፡ ይህ ምላሽ ፊቱን ወደ ጋዜጠኝነት እንዲመልስ አስገደደው፡፡

ወዲያው በኢትዮፕያን ሄራልድ ጋዜጣ ልዩ ዘጋቢ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚታተመው በዚህ ጋዜጣ በልዩ ዘጋቢነት የያዘው ሥራ ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ከሚመጡ የተለያዩ የውጭ ልኡካን ቡድን አባላትና ዲፕሎማቶች ጋር እንዲቀራረብ አደረገው፡፡ በርካታ መሪዎችን፣ በዓለም የታወቁ የወጭ ዜጎችንና ኢትዮጵያውያንን የሚመለከቱ ጥልቅ ዘገባዎችን ሰራ፡፡ የደቡብ አፍሪካው የነፃነት ታጋይ ኒልሰን ማንዴላ፣ ዝነኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት ሙዚቃኛ ሚርያም ማኬባ ቃለ ምልልስ ካደረገላቸው መሀከል የሚጠቀሱ ናቸው|፡፡

ማዕረጉ ለኢትዮፕያን ሄራልድ በመስራት ላይ እያለ እንግሊዝ ሀገር ቶምፕሰን ፋውንዴሽን በሚባል የአርትዖት ጥናት ማዕከል የከፍተኛ ጋዜጠኝነት ስልጠና ተካፍሏል፡፡ በጊዜው የሳውዥ ዌል ኤኮ ለሚባል ጋዜጣ በርካታ መጣጥፎችን አበርክቷል፡፡ ከመጣጥፎቹም መካከል አጼ ኃይለሥላሴ በእንግሊዝ የስደት ዘመናቸው ስለነበራቸው ቆይታ የሚያትት ነበር፡፡ የእንግሊዝ ቆይታው ለጋዜጠኝነት የነበረው ፍቅር እንዲጨምር አደረገው፡፡

ሆኖም ማዕረጉ ከትምህርቱ መልስ ከጋዜጣው የልዩ ዘጋቢነት ስፍራው ተነስቶ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኑኝነት ሐላፊ ሆኖ በመመደቡ ከሚወደው ሙያው ተለያየ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ተዛውሮ እንደገና ከጋዜጠኘነት ጋር ተገናኘ፡፡ በቆይታው በርካታ ተራኪ ዘገባዎችን ለውጭ አድማጮች በማዘጋጀት እስከ የካቲት 1966 አብዮት ድረስ ቆየ፡፡

ማዕረጉ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለጋዜጠኝነት ሙያ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት ነበረው፡፡ በ1967 የንጉሱ ከስልጣን መውረድና በርካታ ጸረ-ፊውዳል እንቅስቃሴዎች መስፋፋታቸውን ተከትሎ ማዕረጉ ወደ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ተዛወረ፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ከሰራ በኋላም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አርታዒ ሆኖ ተመደበ፡፡ በሥራ መደቡ ላይ እስከ ተመደደበት 1980 የሰራው ማዕረጉ የተሻለ ጥራት ያላቸው ዜና ዘገባዎች እንዲሰሩ በማድረግ የጋዜጣውን ሙያዊ ደረጃ ከፍ አድርጓል፡፡

ከ1980 ጀምሮ የየካቲት መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነ፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛና ቋንቋዎች እየታተመ በየወሩ የሚወጣው የካቲት መጽሄት በፖለተካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ስነጽሁፋዊ ይዘቶች ላይ የሚያተኩር መጽሄት ነበር፡፡ መጽሄቱ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር፣ ስዩም ወልዴ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ መስፍን ሀብተማርያም፣ አስፋው ዳምጤና ሌሎችም ታዋቂ ጸሐፍት ይጽፉበት ስለነበር ከፍ ያለ ተወዳጅነት ነበረው፡፡ ማዕረጉም በጥናት ላይ የተመሰረቱ በርካታ መጣጥፎችን በመጽሄቷ ላይ አውጥቷል፡፡ የእለታዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለነበረው ማዕረጉ ወርሀዊ መጽሄት ማዘጋጀት የመስራት አቅምን የሚገድብ መሆኑና የበረታ የጽሁፍ ቅድመ ምርመራ ውስጥ መገኘቱ ሙያዊ መነሳሳትን የሚገድብ ቢሆንም የመጽሄቷን ደረጃና ተነባቢነት አሳድጓል፡፡

ማዕረጉ በዚሁ ስራው ላይ እያለ የአራት ወራት የፖለቲካ ትምህርት ለመካፈል የገዢው መንግስት የርዕዮተዓለም ማስተማሪያ ተቋም ወደ ነበረው የየካቲት 1966 የፖለቲካ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ የስልጠው ተካፋዮች በልዩ ልዩ አገሮች የሚሰሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች፣ የመምሪያ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ ስልጠናው ሲያበቃ ሰልጣኞቹ በምን መስክ መስራት እንደሚፈልጉ የመምረጥ እድል ሲሰጣቸው ማዕረጉ ውጭ ጉዳይ መስሪያቤትን መረጠ፡፡

ለራሱም ባስገረመው በዚህ አጋጣሚ ማዕረጉ በዛብህ በስዊትዘርላንድ፣ ጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሚሲዮን የፕሬስ ሹም ሆኖ ተመደበ፡፡ በመቀጠልም በብሪታንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፕሬስ ሹም በመሆን በመሥራት ላይ ሳለ በ1983 ኢህአዲግ ወደ ስልጣን መጣ፡፡ ለውጡን ተከትሎ አምባሳደሮች ወደ ሀገር ቤት ሲጠሩ ማዕረጉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሏል፡፡

በዚሁ ወቅት በጄኔቫ ጀምሮት የነበረውን የዓለም አቀፍ ግኑኝነት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ የሁለተኛ ዲግሪው ጥናት “የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን በሦስተኛው ዓለም አገሮችን ገጽታ የማበላሸት ዘመቻን ከኢትዮጵያ አንጻር” የሚመረምር ነበር፡፡

በመቀጠል በአውሮፓ ህብረት መሥሪያ ቤት ለ12 ዓመታት በህዝብ ግንኙነት ሙያ ሰርቷል፡፡ ከአውሮፓ ህብረት በጡረታ ከተሰናበተ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት መምህርነት ሰርቷል፡፡

ከ1983 በኋላ ‹‹ሞኒተር›› በተሰኘ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በአዘጋጅነት ከመስራቱም በላይ የ‹‹ልሳነ-ሕዝብ›› መጽሔት የአርትዖት ቦርድ አባል ሆኖ አገልግሏል፡፡ በመጽሔቱ ላይ በኢትዮጵያ የሀያኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሰዎች የሕይወት ገጽታ የሚያሳዩ ጽሑፎችን አውጥቷል፡፡ ከሰዎቹም መካከል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደና አምባሳደር ዮዲት እምሩ ይገኙበታል፡፡

አቶ ማእርጉ በዛብህ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ ‹‹የሃሳብ እስረኛ›› የተባለ ልቦለድ መጽሐፍ፣ ‹‹የጋዜጠኝነት ሙያ፡ ንድፈ ሐሳቡና አተገባበሩ›› የሙያ ማስተማሪያ መጽሐፍ፣ እንዲሁም ‹‹አሽሙርና የኔ እንጉርጉሮ››  የተሰኘ የግጥም መድብል መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ በቅርቡ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ትኩረት የሚያደርግ መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ነው፡፡

የመረጃ ምንጮች

  • “Veteran Journalist and diplomat Mairegu Bezabih” May 25, 2015 Ethiopia Observer.
  • ማዕረጉ በዛብህ – ቃለ-ምልልስ፣ አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2014፡፡
  • ኢቲቪ ‹‹ፍለጋ›› ግንቦት 2011፡፡

“የመገናኛ ብዙሃን የሰላም አዘጋገብ በኢትዮጵያ”

Previous article

በዐዲስ አበባ ከተማ እና አካባቢው በሥርጭት ላይ የሚገኙ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች እነማን ናቸው?

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply