ይማሩ

ማኅበራዊ ሚዲያ እና የዜና ዘገባ

ይማሩ/ MIRH/ 17 ጥር 2022

በዴቪድ ብርወር የተፃፈ

ትርጉም በፍቃድ አለሙ

ማኅበራዊ ሚዲያ በዜና ዘገባ፣ አፃፃፍና ሥርጭት ላይ ትልቅ ለዉጥ ማምጣት የቻለ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነዉ፡፡ 

 ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚያቀርቧቸው አብዛኞቹ መረጃዎች በመደበኛ የኅትመት ወይም የብሮድካስት ሚዲያዎች ሽፋን የማይሰጣቸዉን ጉዳዮች ሲሆን የአሳብ ብዝሓነትን የሚያንፀባርቁ እና አዳዲስ እይታዎችን የሚያካትቱ በመሆናቸዉ በመደበኛ መገናኛ ብዙሃን አሠራር ላይም የራሳቸዉን በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ 

በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ የተለመደዉን የዜና መረጣም ሆነ አቀራረብ መስፈርት በአዲስ መልክ እንዲቃኙ እና በጋዜጠኝነት ሥነምግባርም ሆነ እሴቶች ላይ ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሲዉሉ የነበሩ አሳቦችንም እንደ አዲስ እንዲታዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ምክንያት ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ቀደም ሲል በመደበኛ ሚዲያ ሽፋን የማይሰጣቸዉ አሳቦችም ሆነ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሽፋን ስለሚሰጣቸዉ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች እና አሳቦች ግምት ዉስጥ በማስገባት አዳዲስ እይታዎችን እንዲያካትቱ ምክንያት መሆን ችለዋል፡፡ 

በተጨማሪም መደበኛ መገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት አዳዲስ የጉዳይም ሆነ የአድማጭ/ተመልካች ግብዓቶችን ለማግኘት እንደ ድልድይ ሊጠቀሙባቸዉ ይችላሉ፡፡ ይህም ሆኖ አንዳንድ መደበኛ ሚዲያዎች የማኅበራዊ ሚዲያዎችን ሚና በቀላሉ ሲመለከቱ እና ጠቀሜታቸዉንም ባለመረዳት ከማኅበራዊ ሚዲያ ሊገኝ የሚችለዉን ጥቅም ችላ ሲሉ ይታያል፡፡ 

የመገናኛ ብዙሃን በፈጣን እና ተከታታይ ለዉጥ ዉስጥ እያለፉ ይገኛሉ፡፡ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶች ታዳሚዎች ዜና የሚከታተሉበት፣ የሚረዱበት እና የሚያጋሩበት መንገድ እየተለወጠ በሄደ ቁጥር መደበኛ መገናኛ ብዙሃን አሠራራቸዉ ከጊዜ ጋር የሚሄድ መሆኑን እንዲፈትሹ ምክንያት ሆኗልና ነው፡፡ ከአዳዲስ ግኝቶች እና ሁኔታዎችን ተከትለዉ የሚያደርጓቸዉ ለዉጦች ተቋማዊ ትርፋማነታቸዉ እየታየ የሚከወን ሊሆን ይገባል፡፡ 

ባለፉት ዐመታት በተለይም ከቴክኖሎጂ እና ከታዳሚዎች አረዳድ ጋር በተያያዘ የመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ የለዉጥ ሂደቶች ዉስጥ አልፈዋል፡፡ እነዚህን የለዉጥ ሂደቶች የቀጥታ ተዋረድ ሞዴል፣ የዉስን ተሳትፎ ሞዴል፣ እና ተሳትፏዊ ሞዴሎች በሚሉ ክፍልፋዮች  እንመለከታለን፡፡ 

1. የቀጥታ ተዋረድ ሞዴል

የቀጥተኛ ተዋረድ ሞዴል መገናኛ ብዙሃን እራሳቸዉን እንደዋነኛ የመረጃ እና የእዉቀት ምንጭ በመቁጠር ታዳሚዎች ያለተጨማሪ አማራጭ በመደበኛ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መልዕክቶችን እንዳለ የሚቀበሉበት እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ለመወከል ወይም ይዘት ለማስተላለፍ ምንም ዓይነት እድል ያልነበረበትን ዘመን ይወክላል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚተላለፉ የመገናኛ ብዙሃን ይዘቶች የጋዜጠኞችን እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ፍላጎት እና አቋም የሚወክሉ እንጂ የታዳሚዎችን ግብዓት ያላካተቱ ነበሩ፡፡ 

ይህ ሞዴል በሚያንፀባርቃቸዉ ዉስን አሳቦች እና ለሰፊዉ ማኅበረሰብ ድምፅ በሚሰጠዉ እጅግ የተገደበ ቦታ የተነሣ ዉጤታማ ያልሆነ እና ጊዜዉ ያለፈበት ሆኗል፡፡ 

2. የዉስን ተሳትፎ ሞዴል 

ይህ ሞዴል ትኩረት የሚያደርገው መገናኛ ብዙሃን በተገደበ እና ተቋማዊም ሆነ ሙያዊ ፍላጎቶቻቸዉን በጠበቀ መልኩ ለታዳሚ ተሣትፎ ቦታ የሚሰጡበትን አሠራር ነዉ፡፡ የስቱዲዮ ዉስጥ ክርክሮች፣ ከጎዳና ላይ ከህዝብ የሚሰበሰቡ አስተያየቶች ወይም በኅትመት መገናኛ ብዙሃን የደብዳቤ አምዶች ይህንን ሞዴል የሚወክሉ ማሳያዎች ናቸዉ፡፡ በዚህ ዓይነት አሠራር ዉስጥ የታዳሚዎች ተሳትፎ በተቋማቱ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ገደብ የሚደረግባቸዉ እና በጋዜጠኞች ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረቱ ነበሩ ፡፡ ይህም አሠራር ዘመኑ እያለፈበት ያለ ሲሆን አብዛኛዉ ዓለም አሁን ወደ ተሳትፏዊ ሞዴል በመሸጋገር ላይ ይገኛል፡፡

3. ተሳትፏዊ ሞዴል 

  

ይህ ሞዴል የታዳሚዎችን ተሳትፎ እንደ ዋና የይዘት ምንጭ የመጠቀም እና በኤዲቶሪያል ፖሊሲዎች ዉስጥም የታዳሚዎችን ግብዓት በዋና ምንጭነት የሚደነግግ አሠራርን ይወክላል፡፡ ይህ አሠራር በመገናኛ ብዙሃን እና በታዳሚዎች መካከል ቅርበት ከመፍጠሩም በላይ በታዳሚዎች ግብዓት የዳበሩ እና በትርጉምም ሆነ በተአማኒነት የተዋጣላቸዉን ሥራዎች ለማቅረብ የሚጠቅም ነዉ፡፡ 

ጥቆማዎች

በአሁኑ ጊዜ ሁሉም መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ቢያንስ አንድ ማኅበራዊ ሚዲያ ኤዲተር ወይም የማኅበራዊ ሚዲያዉ ላይ በመደበኛንት የሚሠሩ እና ከመደበኛው የዜና ግብዓቶች ጋር የሚያጣምሩ ቅጥሮች ሊኖሩት ያስፈልጋል፡፡ 

 የማኅበራዊ ሚዲያ አርታኢዉ/ዋ ከሚከዉኗቸዉ ሥራዎች መካከልም፡

  • መደበኛ የዜና ክፍል ዉይይቶችን መካፈል
  • በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚደረጉ ዳሰሳዎች በመነሳት የታዳሚዎችን ፍላጎት ወይም ትኩረት በመመርመር በግብዓትነት ማቅረብ 
  • እንደ Hootsuite እና Tweetdeck የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን በመጠም የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎችን ፍረጃ እና የጉዳዮች ክትትል ማድረግ 
  • በማኅበራዊ ሚዲያ ቀድመዉ ይፋ የሚሆኑ ጠቃሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ለዜና ክፍሉ በፍጥነት መረጃ መስጠት 
  • የየእለቱን የዜና ትኩረቶች የተመለከቱ ዉይይቶችን ወይም ሌሎች መስተጋብሮችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መፍጠር 
  • በተፈጠሩት የማህበራዊ ሚዲያ መስተጋብሮች ላይ የተነሱ ቁልፍ ሃሳቦችን ወይም መረጃዎችን ለአዲስ የዜና ግብዓትነት ማቅረብ
  • የተቋሙ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን እና የማህበራዊ ሚዲያ ክንፎች ለህዝብ እንዲተዋወቁ በመደበኛነት መስራት 
  • ከታዳሚዎች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚላኩ (ተንቀሳቃሽ) ምስሎችን፣ ድምፅ ግብዓቶችን እንዲሁም ግራፊክ ምስሎችን መፈተሸ
  • በመደበኛ አዉታሮች የተላለፉ ዜናዎችን መሰረት አድርገዉ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚነሱ ሃሳቦችን በመፈተሸ እንደአስፈላጊነቱ ተከታታይ ዘገባዎች እንዲሰሩ መጠቆም ይገኙበታል፡፡  

መገናኛ ብዙሃን እዉነተኛ ሕዝባዊ ዉክልናን ማንፀባረቅ የሚችሉት ማኅበራዊ ሚዲያን እንደወሳኝ ግብዓት መጠቀም ሲችሉ በመሆኑ  የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ማኅበራዊ ሚዲያን በጥንቃቄ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊያዉሉ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጉልህ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን ተቋማዊ አዳዲስ የትርፍ ማግኛ ዘዴዎችን መመርመር እና ተገቢዉን የአሠራር ለዉጥ ማድረጋቸዉ የግድ ነዉ፡፡ 

Grant supports virtual reality in African storytelling

Previous article

MIRH content review and validation workshop

Next article

You may also like

Comments

Comments are closed.