የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ማሞ ውድነህ – ደራሲው ጋዜጠኛ

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 16 ነሐሴ 2014

በመቅደስ ደምስ

ማሞ ውድነህ ወሎ ውስጥ በዋግ አውራጃ በምትገኘው አምደወርቅ ከተማ በ1920ዎቹ መጀመሪያ ተወለደ፡፡ ፋሽስት ጣሊያን በ1928 ኢትዮጵያን ሲወር ማሞ ገና ታዳጊ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን የወራሪው ኃይል የጦር አውሮፕላኖች ሳይታሰቡ ደርሰው የነማሞን መንደር በቦምብ እንዳልነበር አደረጉት፡፡ በጥቃቱ ማሞ እናቱን ጨምሮ በርካታ ዘመዶቹን በሞት ተነጠቀ፡፡ እናቱንና ቤተሰቦቹን ከነጠቀው ጥቃት እሱ በእድል ነበር የተረፈው፡፡

የቤተሰቦቹን ሞት ተከትሎ ያለአሳዳጊ የቀረውን ማሞ ዘመዶቹ የቄስ ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡ አስራ አምስት ዓመት ሲሞላው ደሴ በሚገኘው ንጉስ ሚካኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር እድል አገኘ፡፡ ትምህርቱን ግን በትውልድ አካባቢው ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ በብርቱ ታሞ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ፡፡

በአዲስ አበባ ራሱን ማስተዳደር ስለነበረበት በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ የጉልበት ሥራ ሰርቷል፡፡ ትምህርቱን የመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም ሥራ የመሥራት ግዴታው የቀን እንዲማር አላስቻለውም፡፡ ስለዚህ ቀን እየሰራ ማታ መማር ጀመረ፡፡ በመካከሉ በአንድ የሴቶች ማህበር ውስጥ የማስተማር እድል አገኘ፡፡

በወቅቱ የማሞ ትልቅ ምኞት ተምሮ ጋዜጠኛ መሆን ነበር፡፡ ፍላጎቱ ያደረበት ገና በትውልድ አካባቢው የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ በጊዜው በሶስት ወር አንዴ ማሞ ወደሚኖርበት መንደር ይደርሱ የነበሩትን አዲስ ዘመንና ሰንደቅ አላማችን ጋዜጦች የወረዳው አስተዳዳሪ በገበያ ቀን ከፍታ ላይ ሆነው ለገበያተኛው ሲያነቡ ማሞ ይመለከት ነበር፡፡ ገበያተኞቹም ጽሁፎቹን የጻፉትን ጋዜጠኞች ሲያደንቁ ማሞ ይሰማል፡፡ ይህም ጋዜጠኛ የመሆን ምኞት አሳደረበት፡፡

አዲስ አበባ ቀን እየሠራ፣ ማታ እየተማረ፣ የሚያገኛቸውን መጻህፍት እያነበበ ስለ ጋዜጠኝነት ሲያስብ የጽሁፍ ተሰጥኦውን አጎለበተ፡፡ ተሰጥኦውም አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ክፍል በሆነው የዩናይትድ ስቴትስ የመረጃ አገልግሎት የኦዲዮቪዥዋል ሰራተኛ ሆኖ እንዲቀጠር ረዳው፡፡ ከቆይታ በኋላም አዲስ አበባ ወደሚገኘው የሶቪየት የባህል ማዕከል ለተመሳሳይ ስራ አቀና፡፡

አዲሱ ስራው ሲመኝ ከቆየው የጋዜጠኝነት ሙያ ጋር አገናኘው፡፡ የሶቪየት የባህል ማዕከል ውስጥ እየሰራ ስለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምስጢሮች ማወቅ ቻለ፡፡ ጣሊያኖች በልጅነቱ ያሳረፉበት የማይረሳ ቁስል ስለ ጦርነቱ የበለጠ እንዲያነብ ገፋፋው፡፡ ስለጦርነቱ የተጻፉ በርካታ መጻህፍትን እያነበበ ወደ አማርኛ በመተርጎም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ማውጣት ጀመረ፡፡ በወቅቱ መሰል ህትመቶች ስላልነበሩ ጽሁፎቹ በአንባቢያን ዘንድ ተወዳጅነት አተረፉ፡፡

አንድ ቀን ማሞ ከወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አምደሚካኤል ደሳለኝ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሰው፡፡ ንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጽሁፎቹን እንደወደዱለትና በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይስራ ማለታቸውን ሚኒስትሩ ነገሩት፡፡ ማሞም ሀሳቡን ተቀበሎ ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አመራ፡፡ ስራውም በርካታ ሀገራትን ተዘዋውሮ የማየት እድል አስገኘለት፡፡

ለአዲስ ዘመን እየሰራ ስለጦርነቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፉ መጻህፍትን ወደ አማርኛ ተርጉሞ ማሳተም ጀመረ፡፡ በተለይም የስለላ ታሪኮች ይስቡት ስለነበር ተከታታይ የትርጉም መጻህፍትን አዘጋጅቶ አሳትሟል፡፡ አዳዲስ መጻህፍትን ሲያሳትም ለንጉሱ ይዞላቸው በመሄድ በመጽሀፉ ላይ ይወያዩበት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ማሞ ከንጉሱ ጋር ጥሩ ቅርበት ነበረው፡፡ ወደ ቤተ-መንግስት መግቢያ ፈቃድ አገኘ፡፡

በ1953 መጀመሪያ ‹‹ፖሊስና እርምጃው›› ጋዜጣን እንዲያቋቁምና ተባባሪ ዋና አዘጋጅ እንዲሆን ተደረገ፡፡ በወቅቱ ጋዜጣው ከሌሎቹ ጋዜጦች በበለጠ ተነባቢ ነበር፡፡ ማሞም በጋዜጣው ለአምስት ዓመታት ሰራ፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያው የተለያዩ ችግሮችን ተጋፍጧል፡፡ እንዳይጽፍ እስከመታገድ ደርሷል፡፡ በ1958 ከአለቃው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ፖሊስና እርምጃውን ለቆ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተመለሰ፡፡ ወቅቱ ደግሞ የኢትዮጵያና ኤርትራ ፌዴሬሽን የፈረሰበትና በኤርትራ የተቃውሞ ንቅናቄ የተጀመረበት ነበር፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን መንግስት አቋም ለዓለም ለማሳወቅ ማሞ በኤርትራ መዲና አስመራ የሚገኘው የኤርትራ ፕሬስ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ፡፡

በማሞ አመራር ስር በአማርኛ፣ ትግርኛ፣ አረብኛና ጣሊያንኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ ‹‹ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ኅብረት››፣ ‹‹ዓልዓለም›› እና ‹‹ኤልኮቲዲያኖ›› የተባሉ አራት ጋዜጦች ነበሩ፡፡ ማሞ በአማርኛው ‹‹ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ላይ ይጽፋቸው የነበሩት ርእሰ አንቀጾች፣ ዘገባዎችና ሐተታዎች በየቋንቋው ተተርጉመው በሁሉም ጋዜጦች ላይ ይወጡ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ማሞ “የኤርትራ ታሪክ” የሚለውን መጽሀፉን ያሳተመው፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት የአስመራ ቆይታ በኋላ በ1967 ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ ውጥረት ላይ ለነበረው ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት በኤርትራ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የደርግ መንግስትም ስልጣን ሲቆጣጠር ሰሚ ባያገኝም ድምጹን ከማሰማት ወደ ኋላ አላለም ነበር፡፡ በግንቦት ወር 1990 በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል የባድመ ግጭት ሲከሰትም ማሞ ዝም አላለም፡፡ በወቅቱ በሁለቱ ሀገራት መሀከል ሰላም ለማስፈን ይሰራ በነበረውና የተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያክ በነበሩት አቡነ ጳውሎስ በሚመራው የሃይማኖት ኮሚቴ ውስጥ ለሰላም አስተዋጽኦ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ የዓለም አቀፍ የስነ-ምግባር ድርጅት አባልነቱን ተጠቅሞም ለግጭቱ መፍትሄ ይፈለግለት ዘንድ ብዙ ተማጽኗል፡፡

በ1978 ከመንግስት ስራ ጡረታ ሲወጣ ሙሉ ጊዜውን ለጽሁፎቹ፣ ለቤተሰቡና ለማህበራዊ ህይወቱ መስጠት ጀመረ፡፡ በስለላ፣ በታሪክ፣ በልቦለድና በተውኔት ላይ ያተኮሩት ከስድሳ በላይ የሚሆኑት ስራዎቹ ብዛት ከኢትዮጵያውያን ጸሀፍት ቀዳሚው አድርገውታል፡፡ ‹‹ዲግሪ ያሳበደው››፣ ‹‹ሂሩት አባቷ ማነው?››፣ ‹‹የኛ ሰው በደማስቆ››፣ ‹‹ሰላዩ ሬሳ››፣ ‹‹ማህበርተኞቹ›› እና ‹‹አሉላ አባነጋ›› ከድርሰቶቹ መካከል የተወሰኑት ናቸው፡፡

ማሞ በስነ-ጽሁፉና በማህበራዊ አስተዋጽኦው በውጭ ሀገር መጽሄቶች ሽፋን አግኝቷል፡፡ የተለያዩ አለም አቀፍ ሽልማቶችም ተበርክተውለታል፡፡ ከቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልም የምስጋና ደብዳቤ ተሰጥቶታል፡፡

በ1952 ከያዘው ትዳር ስድስት ልጆችን ያፈራው ማሞ ውድነህ፣ ባደረበት ህመም ምክንያት የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡

 

ምንጮቻችን፡

 

ነጋሽ ገብረማርያም፤ ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት ፋናወጊዎች አንዱ

Previous article

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply