የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ

ሙሉጌታ ሉሌ፡ ከቅድመ 1966 እስከ ድህረ 1983 የዘለቀ ጋዜጠኝነት

የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 9 መስከረም 2015

በመቅደስ ደምስ

ሙሉጌታ ሉሌ ሐምሌ 5 ቀን 1933 ከአባቱ አቶ ሉሌ ደስታ እና ከእናቱ ወ/ሮ ወርቅነሽ ጎሾ በምዕራብ ሸዋ ግንደበረት ተወለደ፡፡ ከንግድ ሥራ ከሚተዳደር ቤተሰብ የተገኘው ሙሉጌታ ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሸዋ፣ አምቦ ከተማ ማዕረገ ህይወት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በደብረብርሀን ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከዚያም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ በማታው ክፍለጊዜ ገብቶ ፖለቲካ ሳይንስና ሥነ-መንግሥት በማጥናት የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ሙሉጌታ ገና በታዳጊነት እድሜው ከፍ ያለ የንባብ ፍቅር ነበረው፡፡ በወጣትነቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ መጻህፍትን አንብቧል፡፡ ማንበብ ብቻ ሳይሆን እንደ ሐምሌት፣ ማክቤዝ እና ኦቴሎ የመሳሰሉትን የሼክስፒር መጽሐፍትን በቃሉ ያነበንባቸው ነበር፡፡ ጥሩ የጽሁፍ ክህሎትም ነበረው፡፡ አንዴ ካናዳዊ መምህሩ ያቀረበላቸውን የራሱን ጽሁፍ አይተው ‹‹ይህን ሌላ ሰው ጽፎልህ ይሆናል እንጂ እንዴት አንተ ልትጽፈው ትችላለህ?›› ብለው ተጠራጥረውት እንደነበር ራሱ ሙሉጌታ ተናግሯል፡፡ በኋላ እኚሁ መምህሩ ወደፊት ትልቅ ጸሐፊ እንደሚሆን ነግረውት ነበር፡፡

ሙሉጌታ የመጀመርያ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ወደ ናዝሬት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተቋም በማቅናት የስነ መለኮትና የቤተክርስቲያን ታሪክ ተማረ፡፡ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም በተማረበት ተቋም የታሪክና የአማርኛ መምህር ሆኖ ከ1955 እስከ 1956 አስተምሯል፡፡ በእነዚያ ዓመታት በሙያቸው እውቅና ያገኙ ሰዎችን አስተምሯል፡፡ ካስተማራቸውና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ ከነበራቸው መካከል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ. ዴሌቦ፣ አቶ ሌንጮ ለታ እና ሌሎችም በጊዜው በተቋሙ የተማሩ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡

ሆኖም መምህሩ በሙያው ከሁለት ዓመታት በላይ አልቆየም፡፡ በ1957 በኢትዮጵያ መብራትና ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን የሰራተኛ አስተዳዳር ክፍል ውስጥ ለአንድ ዓመት ሰርቷል፡፡ በኋላም ብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ተቀጥሮ ጋዜጠኛ ሆነ፡፡ ስራውንና ብዕሩን በአድናቆት የተመለከቱት ቀደምት ጋዜጠኞች ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲዘዋወር አግባብተው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲቀጠር አደረጉ፡፡

ሙሉጌታ አዲስ ዘመን እየሰራ በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ጽሁፎቹን ያወጣ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ሔራልድ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ድምጽ፣ መነን፣ የካቲት፣ ልሳነ ሕዝብ፣ እና አዲስ ሪፖርተር ጋዜጦች ላይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በርካታ ጽሑፎችን ያቀርብ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ላይ በረዳት አዘጋጅነትም ሰርቷል።

ከ1983 በፊት በስራ ላይ እያለ ወደ ተለያዩ አገሮች በመጓዝ ሙያዊ አቅሙን በሚያጎለብቱ አጫጭር የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎች ከመሳተፉም በላይ በየአገሮቹ በሚገኙ ትልልቅ መገናኛ ብዙሀን ውስጥ ከሚሰሩ ጋዜጠኞች ጋር የተግባርና የልምድ ልውውጦች አድርጓል፡፡ ከተጓዘባቸው አገሮች መካከል ህንድ፣ ሶቪየት ህብረትና በርካታ የቀድሞ ሶሻሊስት አገሮች ይገኙበታል፡፡

ሙሉጌታ ሉሌ የሶማልያና የኤርትራን የፖለቲካና ታሪክ ነክ ጉዳዮች በሚገባ አንብቦና ተንትኖ የሚያውቅ ባለሙያ ሲሆን ባልደረቦቹን እየሠራ ጭምር የሚያስረዳና የሚያማክር ሰው ነበር፡፡ ስለ አገሩና ዓለምአቀፍ ግኑኝነት ፖለቲካ ጥልቅ እውቀት ነበረው፡፡

ሙሉጌታ ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን›› በሚለው መጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደገለጸው በ1968 በልዩ የግዳጅ ሥራ ወደ ኤርትራ ተልኮ ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘችው ሳምንታዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በኋላም የሶማልያን ወረራ ለመመከት የሚያስችል ልዩ የፕሮፖጋንዳና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በማስፈለጉ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሬዲዮ ልዩ መመሪያ በ1970 ሲቋቋም ሙሉጌታ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ መምሪያውን እንዲመራ ተመደቦ ኃላፊነቱን በብቃት ተወጥቷል፡፡ በኤርትራ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት በበዓሉ ግርማ የተመራውን የጋዜጠኞች ቡድን በምክትልነት መርቷል፡፡ ከዚያም እስከ 1975 በኃላፊነት ወዳገለገለበት ኢትዮጵያ ሬዲዮ በማቅናት በፖለቲካና የቅስቀሳ ሥራዎች ብቻ ሳይወሰን፣ ተወዳጅ የሆኑ ማህበራዊና የመዝናኛ ዝግጅቶችን መርቷል፤ ጽሑፎችንም አበርክቷል፡፡ በኋላም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆኖ እስከ 1983 ድረስ ሰርቷል፡፡

የ1983 የመንግስት ለውጥ በሙሉጌታ የሙያ ህይወት ውስጥ ወሳኝ ለውጥ ያስከተለ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ከሥራ እንዲፈናቀል ተደረገ፡፡ መፈናቀሉ ግን ከመንግስት ብዙሃን መገናኛ ሥራ መፈናቀል እንጂ ከሙያው መፈናቀል አልነበረም፡፡ ገና በለውጡ የመጀመሪያ ዓመት ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን አጥቢያ ኮከብ አሳታሚ ድርጅትን በማቋቋም ‹‹ጦቢያ›› የተሰኘች ፖለቲካዊ ይዘት ያላት መጽሄት ጀመረ፡፡ በጦቢያ መጽሄት አምደኛነቱ ‹‹ጸጋዬ ገብረመድኅን አርአያ›› በሚል የብዕር ስም በሰላ ብዕሩ ይጽፋቸው የነበሩት መጣጥፎቹ ሙሉጌታን ታዋቂ አድርገውታል፡፡ በ1984 ‹‹አጥፍቶ መጥፋት›› የተሰኘ መጽሐፍ በዮሐንስ ሙሉጌታ ስም አሳተመ።

የግል መገናኛ ብዙሃንን ጫና መቋቋም ያልቻለው የወቅቱ መንግሥት በርካታ ጋዜጠኞችን በክስና እስራት ሲያጣዳፍ ሙሉጌታም ተደጋጋሚ ክሶች ተመስርተውበት ለእስር ተዳርጓል፡፡ ቢሮው በእሳት ጋይቶበታል፡፡ በመንግስት ደህንነት ሰዎች በመኪና ግጭት የመግደል ሙከራ ተደርጎበታል፡፡ ህይወቱ በተዓምር ተርፋ ሆስፒታል ተኝቶ ጭምር የደህንነት አባላቱ እየተከታተሉ ያስቸግሩት ነበር፡፡ ክትትሉን በመሸሽ ህክምናውን በመኖሪያ ቤቱ ተኝቶ በወዳጅ ሐኪሞች ለመከታተል ተገዶ ነበር፡፡ ‹‹እንኳን እጄን አልቆረጡኝ፣ ብዕር የምይዝበት እጄ እስካለ ድረስ ተርፌያለሁ›› እያለ ወዳጆቹን ያጽናና ነበር፡፡ ሁኔታው እየከፋ ሲመጣ በብርቱ የወዳጅ ጉትጎታና ድጋፍ አገር ትቶ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ በወቅቱ 16 የሚደርሱ ክሶች ተመስርተውበት ነበር፡፡

ከአገር ከወጣ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ በጦቢያ፣ ከዚያም በልሳነ ሕዝብ መጽሔቶች ላይ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ ቆይቶም ሁለቱም መጽሄቶች እንዲቆሙ ሲደረግ የልቡን ባያደርስለትም አልፎ አልፎ በተለያዩ ድረገጾች ላይ መጻፍ ቀጥሏል፡፡

ቆይቶ ከተወሰኑ ጋዜጠኞች ጋር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (ኢ.ቲ.ኤን)ን በማቋቋም በሥራ አስኪያጅነት አገልግሏል፡፡ በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ (ኢሳት) ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ፡፡ በኢሳት በትንታኔዎቹ ሚሊዮኖቹን አስተምሯል። ወጣት የጣቢያውን ጋዜጠኞች በአርአያነትና በሙያ በመግራት ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል አለመሆኑንም ይነገርለታል፡፡

ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር መስራች አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ እንደ ጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ (ሲ.ፒ.ጄ) ካሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሙያ አጋሮቹ መብት ጥብቅና ሲቆም ኖሯል። ለኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሙሉጌታ፤ ስለ እስር እንግልቱ ለምን በአደባባይ በብዛት እንደማያወራ ሲጠየቅ ‹‹ታዳጊ ጋዜጠኞችን ማስበርገግ ይሆናል›› የሚል መልስ ይሰጥ ነበር።

ሙሉጌታ ሉሌ ለ19 ዓመታት ያህል በአሜሪካ ቨርጅኒያ ግዛት በስደት ከቆየ በኋላ መስከረም 23 ቀን 2008  በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ እርሱ ከሞተ በኋላ ሴት ልጁ ኤዶም ሙሉጌታ በህይወት ሳለ ‹‹ልሳነ ሕዝብ›› እና ‹‹ጦቢያ›› መጽሔቶች ላይ ካስነበባቸው ጽሑፎቹ የተመረጡትን በማያያዝ ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን›› በሚል ርዕስ በስሙ መጽሐፍ አሳትማለች፡፡ ሙሉጌታ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበር፡፡

ምንጮቻችን፡-

  • ሙሉጌታ ሉሌ (2009) ሰው ስንፈልግ ባጀን. (ሦስተኛ እትም)፡፡ ፋር ኢስት ትሬዲንግ
  • ዋዜማ ሬድዮ (ነሐሴ 2008) ሙሉጌታ-ሉሌ፣ተመስገን-ደሳለኝና-ሌሎችም/                          https://wazemaradio.com/
  • ሪፖርተር- ‹‹ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ (1934-2008)›› መስከረም 26፣ 2008 https://www.ethiopianreporter.com/54161/
  • አዲስ አድማስ- ‹‹ያመነበትን ጽፎና ተናግሮ ያለፈ ጀግና!›› ህዳር 13፣ 2008 https://addisadmassnews.com/

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤት

Previous article

ሰለሞን ዴሬሳ፡ ዘርፈ ብዙው የሙያ ባለቤት

Next article

You may also like

Comments

Leave a reply