የሚዲያ ባለሞያዎች መዝገብ / MIRH/ 18 ሚያዝያ 2022
በፍቃዱ ዓለሙ
ጋዜጠኛ፣ ሐኪም እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች
ዶ/ር መላኩ በያን ከአባታቸው ግራዝማች በያን እና ከእናታቸው ወ/ሮ ደስታ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ሚያዚያ 21 ቀን 1892 ዓ.ም ተወለዱ። ገና ሕፃን እያሉ ወላጆቻቸው ወደ ሐረር በመዛወራቸው ምክንያት በዘመኑ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አባት ራስ መኰንን የሐረር ገዥ ስለነበሩ በሐረሩ ቤተመንግሥት በወቅቱ ተፈሪ ይባሉ ከነበሩት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር አብረው እየተማሩ በጓደኝት አድገዋል፡፡
ተፈሪ ራስ ከተባሉም በኋላ በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸውም ዶ/ርመላኩ ቤተኛም ነበሩ። በዚህ ወቅት በርካታ የኢትዮጵያ አጐራባች ሐገሮችና ሌሎችም የአፍሪካ ግዛቶች በተስፋፊዎች እና በቅኝ ገዥዎች ቁጥጥር ሥር ነበሩ። ኢትዮጵያም እንደ ሌሎች ሀገሮች ዕጣ ፈንታው እንዳይደርሳት ምጥ ውስጥ ገብታለች። ከዚህ አስከፊ ችግር ይገላግላታል ተብሎ በብዙሃን ባለስልጣናት የታሰበው የተማሩ ልጆች እንዲኖሯት ነበር። መላኩ በያንም ትምህርት ከተማርን ሀገራችንን ከማንኛውም ጥቃት እንከላከላታለን የሚል እምነት ነበራቸው።
በዚህ ምክንያት በ1913 ዓ.ም 21 ዓመት በሆነው ጊዜ ከኹለት ወንዶችና አንዲት ሴት ጋር ለሕክምና ትምህርት ወደ ሕንድ ሀገር ተላኩ፡፡ ይሁንና ደ/ር መላኩ በያን በሕንድ ሀገር ያለው የብሪታኒያ አገዛዝ እና የትምህርት ኹኔታ ስላልተስማማው ብሎም አብረውት ለትምህርት ከሄዱት መካከል ሴቷ በመሞቷ ምክንያት የሕንድ ኑሮው ሊያስደስተው አልቻለም፡፡ ከዚያም ከቀሪዎቹ ሁለት ወንድ ጓደኞቹ ጋር በመርከብ በመሳፈር ወደ አሜሪካ ተጓዘ።
እ.ኤ.አ. በ 1922 ኦሃዮ በሚገኘው ማሪዬታ ኮሌጅ ተመዝግቦ ትምህርቱን ተከታትሎ ሲጨርስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። ከአሜሪካ የኮሌጅ ዲግሪ ያገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ይታመናል። በወቅቱ አፍሮ አሜሪካን የሚባለው ጋዜጣ እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር በመስከረም 14,1925 ባወጣው እትሙ “… በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያዊ ዲግሪ ተሠጠ።…” በማለት ተጽፎለታል። መላኩ በመቀጠል የሕክምና ትምህርቱን በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በ19 28 ጀመረ። ከዚያም ከአንድ አመት በኋላ እዚያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመቀራረብ በሚል ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ለመዛወር ወሰነ።
መላኩ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሴት ልጅ ጋር የነበራቸውን ጋብቻ በይፋ ከሰረዙ በኋላ ዶርቲ ሃድሌይ ከተባለች አፍሪካ አሜሪካዊት እና በራሷ መብት ለኢትዮጵያ እና ለመላው አፍሪካውያን የምትቆረቆር ታላቅ አክቲቪስት ጋር ተጋባ። መላኩ በትዳርና በእውቀት ሕይወቱ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ባሉ የአፍሪካ ዳዮስፖራ መካከል ዐዲስ ትሥሥር መፍጠር ፈልጎ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ጓደኞቹ መስክረዋል።
በ1935 ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ወራራ በመፈጸሟ ምክንያት መላ ኢትዮጵያውያን እምብኝ አሻፈረኝ በማለት የሀገሬው አርበኛ ለእናት ሀገሩ በሚዋደቅበት ጊዜ መላኩ ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወዲያው ከባለቤቱና ከልጃቸው ከአቶ መላኩ ኢ. ባዬን ጁኒየር (Melaku E. Bayen, Jr.) ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ አዲስ አበባ በአሜሪካ ሚሽን ሆስፒታል ሥራ ቢጀምርም ጦርነቱ እየተባባሠ በመሄዱ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልን ተቀላቅለው በምሥራቅ ግንባር የቆሰሉትን ረድተዋል። እናም በዚያው አመት በሰሜናዊ ግንባር በማይጨው ጦርነት የዓፄ ኃይለሥላሴ ሐኪም በመሆን ሌሎች የተጎዱ አርበኞችን በማከም አገልግለዋል። በግንቦት ወር 1936 የጣሊያን ጦር አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ደ/ር መላኩ ንጉሠ ነገሥቱን ተከትሎ ወደ እንግሊዝ ተጓዘ። ብዙም ሳይቆይ ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ ዘመቻ ለማድረግ ከቤተሰቡ ጋር ወደ አሜሪካ ተመለሰ።
እ.ኤ.አ. በ1937 ዶ/ር መላኩ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካሪቢያን እና በአውሮ ቅርንጫፎች ያሉት ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ድርጅት የሆነውን የኢትዮጵያ የዓለም ፌዴሬሽንን መመስረት ከኢትዮጵያ አልፎ የካሪቢያን ቅርንጫፍ የራስታ ንቅናቄን ርዕዮተ ዓለም መሠረት ለማጠናከር ረድቷል።
በዚያው አመትም ዶ/ር መላኩ የኢትዮጵያ የዓለም ፌዴሬሽን እና የአፍሪካ ጉዳዮችን ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ጋዜጣ “The Voice of Ethiopia” ፤ “የኢትዮጵያውያን ድምፅ” መሥራች ነው፡፡ ጋዜጣው “ከባርነት ሞት ይሻላል” የሚል መሪ ቃል ነበር፡፡ በጋዜጣው የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የሕዝቡን ሕይወት፣ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግልን እና ሌሎች አፍሪቃዊ ጉዳዮችን እየጻፈ የኢትዮጵያ ድምፅ በዓለም አሰምቷል፡፡ ጋዜጣው ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ ለማላቀቅ በሚደረገው ትግል በአለም ዙሪያ ተበታትነው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካአሜሪካውያን እንዲተባበሩ ሲያሳስብ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር መላኩ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ “ምኒልክ ክበብ” የተባለ ድርጅት በማቋቋም ገንዘብ ለማግኘት ሲል የኢትዮጵያን ምስል ያለበትን ቴምብር እያሳተመ በእያንዳንዱ ሠው ቤት እየዞረ በመሸጥ ገንዘብ አሰባስቧል።
ስለዚህ ታላቅ ሰው ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ሲጽፍ እንዲህ አለ “መላኩ በያን በብዙዎች ዘንድ ያልታወቀ ስሙን በሚያውቁት ዘንድም ቢሆን ምን ታሪክ እንዳልው ያልተገለጸለት ለኢትዮጵያ ታላላቅ ሥራ እየሠሩ ከተረሱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው፡፡
እኔም ብሆን ታሪኩን በሙሉ እጽፈዋለሁ ለማለት ሳይሆን በመጠኑ ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡” በማለት በአጭር ጊዜ እድሜ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን እና አፍሪቃውያንን በአንድ አሰልፎ የሠራቸውን ድንቅ ሥራዎች በማዘከር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1939 “የጥቁር አፍሪቃውያን እንቅስቃሴ፡ ኢትዮጵያ ትመራለች” በሚል ርዕስ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡
ዶ/ር መላኩ ከሀገር ቤት እስከ ምድረ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ቤት ለቤት ሲዘምትና ሲባዝን ባጅቶ ባደረበት የሳንባ ምች በሽታ በኒውዮርክ ከተማ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ከሕመሙ ሳይሻለው ቀርቶ በ40 ለጋ እድሚያቸው አጠረ፡፡ የነጻነት ተማጋቹ፣ የጥቁሮች ኅብረት አነቃቂው ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ወቅቱ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1940 ዓ.ም ኢጣሊያኖች በኢትዮጵያ ሊሸነፉ አንድ ዓመት ሲቀረው በመሆኑ በእርግጠኝነት የጣሊያን ቅኝ ግዛት በኢትዮጵያ እንዲከስም ያላሰለሰ ዘመቻው አስተዋጾ አድርጓል ማለት ይቻላል።
ምንጮቻችን
The Quest for Press Freedom: One Hundred Years of History of the Media in Ethiopia,በመሠረት ቸኮል (ደ/ር), 2013 G.C
ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ ያልታተመ ጽሑፍ
Comments