ይማሩ /MIRH/ 30 ነሃሴ 2014
በስንታየሁ አባተ
ወቅቱ ከመረጃ ተደራሽነት አንፃር ጋዜጠኝነት ተጠቃሚ የሚሆንበትና የሚፈተንበት ነው፡፡ ጥቅሙ በርካታ የመረጃ ጥንቅሮችን በቀላሉ ማግኘት፤ ፈተናው ደግሞ መረጃ የማጣራት ሂደት ይበልጥ ውስብስብ መሆኑ ነው፡፡ የዜጋ ጋዜጠኝነት (citizen journalism) ከመስፋፋቱና የመረጃ ልውውጡ እጅግ ከመስፋቱ ጋር ተያይዞ እውነትና ሀሰቱን የመለየቱ ሥራ በመደበኛው ጋዜጠኝነት ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ሀሰተኛ መረጃን የማጣራት ሥራ ውስብስብ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይም ሀሰተኛ የፎቶና ቪዲዮ መረጃ ጥንቅሮች ዛሬ ላይ በማጣሪያ መሳሪያዎችም ለመለየት ወደሚያስቸግር ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ሀሰተኛ መረጃ ወደ ጥልቅ ሀሰተኛ መረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ይህም ሰዎች ያልተናገሩትን እንደተናገሩ አድርጎ በምስልና ድምጽ እስከማቅረብ ተደርሷል፡፡ ይህም እውነተኛና ሀሰተኛ መረጃን የማጣራቱን ሥራ አወሳስቦታል፡፡
የመረጃ ልውውጥ የደረሰበት ደረጃ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥር 2013 ላይ የነበረው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን ተጠቃሚዎች ቁጥር 4.2 ቢሊዮን ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ጥር 2014 ላይ ቁጥሩ በ10 ነጥብ 1 በመቶ አድጎ 4 ነጥብ 62 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከዓለም አጠቃላይ ሕዝብ 58 ነጥብ 4 በመቶው በይነ መረብ ላይ የተመሰረቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚ ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ በአማካይ በየቀኑ 2 ሰዓት ከ27 ደቂቃ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ያሳልፋል፡፡
በዚህ ሂደት ቢሊዮኖች ለበይነ መረብ ገጾቻቸው የሚሆኑ ይዘቶችን ያዘጋጃሉ፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት አዳዲስ መረጃ ያሰራጫሉ፤ ይለዋወጣሉ፡፡ መደበኛ መገናኛ ብዙሀንም በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በኩል መረጃ በማሰራጨት በርካታ ተከታይ ማፍራት ችለዋል፡፡ በመደበኛና ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን መካከል የመረጃ ልውውጥ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ይህም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትና የማጣራት ሂደትን በተወሳሰበ አውድ ውስጥ የሚከወን ፈታኝ ተግባር እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በውስብስቡ አውድ ውስጥ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች የመረጃ ይዘቶች በሦስት ዋነኛ ፈርጆች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ እነርሱም
- Disinformation (ይሁን ተብሎ ተዘጋጅቶ የሚሰራጭ ሀሰተኛ መረጃ) የዚህ ሀሰተኛ መረጃ ግብር ይሁን ብሎ ማሳሳት ነው፡፡ የአሳሳቾቹ ዋና ዓላማ ሀሰተኛ መረጃው እውነተኛ መስሎ እንዲታይ በማድረግ በመረጃው ተደራስያን ዘንድ ፍላጎታቸውን የሚጠቅም የአስተያየት ለውጥ ወይም ምላሽ መፍጠር ነው፡፡ ዒላማ የሚያደርገው ግለሰቦችን፣ ተቋማትንና ሀገር ሊሆን ይችላል፡፡
- Misinformation- (በስህተት የሚፈጠር ሀሰተኛ መረጃ) መረጃው ሀሰተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ይሁን ተብሎ ታስቦበት የሚፈጠር ሀሰተኛ መረጃ አይደለም፡፡ አዘጋጅቶ የሚያሰራጨው አካል ይሁን ብሎና የማሳሳት ዓላማ ይዞ የሚፈጥረውና የሚያሰራጨው አይደለም፡፡ በማንም ላይ ጉዳት የማድረስ ዓላማ የለውም፡፡ አዘጋጅቶ የሚያሰራጨው አካል መረጃው እውነተኛ እንደሆነ ያስባል፡፡ ያልተታሩ ጭምጭምታዎች ወሬዎችን መቀበል የስህተቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
- Malinformation- (ጉዳት ለማድረስ ይሁን ተብሎ የሚሰራጭ እውነተኛ መረጃ) ዓላማው ሰዎችን፣ ድርጅቶችና ሀገርን መጉዳት ነው፡፡ መረጃው አንድ ቡድን በሌላው ላይ የፈጸመው ቂም በቀል ቀስቃሽ የግፍ ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም መረጃው እውነተኛ ቢሆንም ቢሰራጭ በግለሰቦች፣ በተቋማት፣ በማህበረሰብና በሀገር ላይ ሊያስከትል በሚችለው ጉዳት ምክንያት ተደራሽ እንዳይሆን ተጠብቆ የተያዘ ሊሆን ይችላል፡፡
ጥልቅ ውሸት /Deep fake/ከላይ የተጠቀሱትን የሀሰተኛ መረጃ ችግሮች ከዚህ በታች በተጠቆሙት የእውነት ማጣሪያ መሳሪያዎች በመታገዝ መፍታት ይቻላል፡፡ በተለይ ‹‹ጥልቅ ውሸት›› የሚባለው ሀሰተኛ መረጃ በቀላሉ ሀሰተኛነቱ ሊታወቅ ስለማይችል በእውነት ማጣሪያ መሳሪያዎች መታገዝን ይጠይቃል፡፡ በሂደቱ ውስጥ የመረጃ መዛባት ሥራውን ከባድ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ዋነኛው ነው፡፡
‹‹ጥልቅ ውሸት›› የሚሰሩ አካላት እውነትና ውሸቱን ለመለየት በሚያዳግት መልኩ የድምጽ፣ የምስልና የድምጽና ምስል ፈጠራዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በተለይም በተንቀሳቃሽ ምስል ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ሳይናገሩ እንደተናገሩ ተደርጎ ለማቅረብ በሚያስችል የድምጽና ምስል ማቀናበሪያ ቴክኖሎጂ ይገለገላሉ፡፡
ይህም ተደራሲያን እውነትና ውሸቱን መለየት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ እውነተኛና የተጣራ መረጃ ለህዝብ የማድረስ ኃላፊነት ላለባቸው መደበኛ መገናኛ ብዙኃን ፈተና ነው፡፡ ለሀሰተኛ መረጃ ተጋላጭ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ የመረጃ ትክክለኛነትን ለማጣራት የሚያደርጉትን ምርመራ የበለጠ ውስብስብ ያደርግባቸዋል፡፡
ለማኅበራዊ ትስስር ገጾች ያለን እምነት
በየካቲት 2014 በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የመረጃ ተዓማኒነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኬንያ ለተደረገ ጥናት https://www.statista.com/statistics/718019/social-media-news-source/ ምላሽ ከሰጡት ሰዎች መካከል 82 በመቶዎቹ ማኅበራዊ ትስስር ገጾችን እውነተኛ የመረጃ ማግኛ ምንጭ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ 40 አገራት መካከል መጨረሻ ላይ በተቀመጠችው ጃፓን 28 በመቶ ዜጎች ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚወጡ መረጃዎችን ሁሉ እውነት ነው ብለው ይቀበላሉ፡፡ ይህ ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አማኝ ተደራሽ ባላቸው ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ይሁን ተብሎም ሆነ በስህተት የሚሰራጩ ሀሰተኛ የመረጃ ጥንቅሮች ሊያደርሱ የሚችሉትን ቀውስ አመላካች ነው፡፡
የሀሰተኛ መረጃዎች አደጋ
ሀሰተኛ መረጃ የሚፈጠረውና የሚሰራጨው በአብዛኛው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሲሆን የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖም የሚናቅ አይደለም፡፡
ሰዎችን እውነትና ሀሰቱን እንዳይለዩ በማድረግ ለተሳሳተ ውሳኔ ይዳርጋል፡፡ በዚህም ሰዎች በሀሰተኛ መረጃ ተማረው “የምታነበውን ሁሉ አትመን” የሚል የተጋነነ ድምዳሜ ላይ ከደረሱ ሕጋዊ፣ ታማኝና መደበኛ የመረጃ ምንጮችን እምነት የሚያሳጣ ይሆናል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ የህልውና መሰረት መታመን መሆኑ ሲታሰብ አደጋው ልክ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ብዙ የሀሰተኛ መረጃ ጥንቅሮች በይሁንታ ጉዳት ማድረስን አልመው የሚሰራጩ ከመሆናቸውም በላይ አቀራረባቸው ስሜት ኮርኳሪ ይሆናል፡፡ ይህም ግጭትን፣ ሁከትንና ነውጥን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሰዎች በየጎጣቸው ገብተው ጽንፈኛ የሆኑ ትርክቶችን የሚያራቡበት መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ለአብነትም ኮቪድ-19 በተከሰተ ወቅት “በአምስተኛው ትውልድ የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (5G) አማካኝነት ይተላለፋል” የሚለውን ሀሰተኛ መረጃ ተከትሎ ዛሬም ሰዎች በጤናቸው ላይ የተሳሳተ ውሳኔ እየወሰኑ ይገኛሉ፡፡
ሀሰተኛ መረጃን እንዴት መለየት እንችላለን? (ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄ)
ሀሰተኛ መረጃ በስፋት በሚሰራጭበት ዘመን አንድ ጋዜጠኛም ሆነ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚ የሚመለከተውን መረጃ ሁሉ እውነት ነው ብሎ የሚቀበል የዋህ መሆን የለበትም፤ ይልቁንም የሚከተሉትን 10 ስልቶች በማገናዘብ ማጣራት አለበት፡፡
- ምንጩን ማጣራት– ከስያሜና ፊደል ጀምሮ የመረጃውን ምንጭ ትክክለኛነት ማጣራት፡፡ ለአብነት ዌብሳይት ከሆነ የመፈለጊያ ስያሜያቸው ላይ “.infonet” or “.offer” የሚጠቀሙ ከሆነ ብዙም እምነት አይጣልባቸውም፡፡ ገጹ ፌስቡክ ከሆነም ከራስ መግለጫ መረጃ ተነስቶ ትክክለኛ መሆኑን ለማጣራት መሞከር ይገባል፡፡
- ጸሐፊውን ማወቅ– በስማቸው ከዚህ በፊት የወጡ የመረጃ ጥንቅሮችን በማጣራት ታማኝነታቸውን መፈተሸ፤ በተገለጸው ስም የሚታወቅ እውነተኛ ማንነት መኖሩን በሌሎች የበይነ መረብ ፍለጋዎች ማረጋገጥ፤ ከጽሑፉ ይዘት ተነስቶ የጸሐፊውን ፍላጎት (ዓላማ) ለመረዳት መሞከር፣ የጻፈው ከሙያውና የዳራ ታሪኩ ጋር በሚገናኝ ጉዳይ ላይ ነው? ወይስ የተለየ አጀንዳስ አለው? ከሚሉት ጥያቄዎች አንጻር ምርመራ ማድረግ፡፡
- ሌሎች ምንጮችን ማጣራት– መረጃውን የሰሩ ሌሎች ታማኝ የዜና ምንጮች እንዲሁም በመረጃው ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ ምንጮች (ሰዎች) መኖራቸውን ማረጋገጥ፡፡
- ራስን መጠየቅ– አብዛኛው ሀሰተኛ መረጃ የሚሰራውና የሚሰራጨው ፍርሃትና ቁጣን ለመቀስቀስ በመሆኑ ይህ መረጃ ለምን ሊጻፍ ተፈለገ የሚለውን ጥያቄ ለራስ መጠየቅ ይጠቅማል፡፡
- ሀቆችን ማጣራት– እውነተኛ የመረጃ ጥንቅሮች በቁጥርና በተንታኝ (ምሁራን) ሀሳቦች ቀጥተኛ ማስረጃነት የሚደገፉ በመሆናቸው የሚጨበጥ ማስረጃ ያላከተተ መረጃን በጥርጣሬ ማየት ይበጃል፡፡ ሀሰተኛ መረጃዎች የተሳሳተ ቀን ሊጠቀሙ፣ በፊት ታትሞ የነበረን እንደ አዲስ አስመስለው ሊያትሙ ወይም ሊለጥፉ ስለሚችሉ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
- አስተያየቶችን መቃኘት– የተጋራው ይዘት ሕጋዊ (እውነት) ቢሆን እንኳ ከስር የተሰጡ አስተያየቶችን መመልከት ይገባል፡፡ ይህም ማለት እንደ ፌስቡክ ባሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ አንድ ይዘት ከተለጠፈ በኋላ አጀንዳ ለመስጠት በማለም ከስር የተናበቡ ሀሰተኛና አሳሳች አስተያየቶች በብዛት ስለሚለጠፉ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
- የራስን ግምት መከተል– ሰው ከፍላጎት እንደማይፀዳና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የየራሱ ፍላጎት እንዳለው አምኖ ይዘቶችን በሚዛኑ መቃኘት እንዲሁም ከአንድ ምንጭ ይልቅ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ በማሰባሰብ የተሻለ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይገባል፡፡
- ቀልድ መሆን አለመሆኑን መለየት– አንዳንድ ይዘቶችና ገጾች ሆን ተብለው ሳቅና ቧልትን ለመፍጠር ስለሚሰሩ እውነት ነው ብሎ ከመውሰድ የገጾቹን ባህሪይና የቀደመ ይዘት መመልከት ያስፈልጋል፡፡
- የፎቶዎችን እውነተኛነት ማረጋገጥ – ፎቶዎቹ ከዚህ በፊት የተለጠፉና መሆናቸውንና የተነካኩ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ (ከታች በምናያቸው መሳሪያዎች እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል እንመለከታለን)፡፡
- የእውነት ማጣሪያዎችን መጠቀም– ከሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ጋር በተያያዘ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን የየራሳቸው የእውነት ማጣሪያ የሥራ ክፍሎችን ሲያደራጁ፤ እውነትን የማጣራት ተግባርን ዋነኛ ሥራቸው አድርገው የተመሰረቱና በዓለም አቀፉ የእውነት ማጣሪያ ትስስር /the International Fact-Checking Network (IFCN)/ ውስጥ ተካተው የሚሰሩ ድርጅቶች (ተነሳሽነቶች-intaitives) አሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ሰው ጥርጣሬ ያደረበትን መረጃ በራሱ ማጣራት ወይም ደግሞ ለአጣሪ ድርጅቶች በመጠቆም እንዲያጣሩት ማድረግ ይችላል፡፡
የእውነት ማጣሪያ መገልገያዎች
ከላይ በጠቀስናቸው የጥንቃቄ መንገዶች ተጉዘን መረጃውን ከተጠራጠርነው InVID፣ Reverse Image Search (TinEye) ፣ Snopes.com፣ FindExif.com፣ Hoaxy፣ Wolfram|Alpha፣ twXplorer እና Factcheck.org የተሰኙት መገልገያዎችና ድርጅቶች እውነትን ለማጣራት ጥቅም የሚሰጡ ግብኣቶች ይሆኑናል፡፡
በእነዚህ መሳሪያዎች እውነትን ካጣራን በኋላ እንደግኝታችን ለመረጃው ደረጃ የምንሰጥ ይሆናል፡፡ ይህም ማለት መረጃው እውነት ነው ወይም ሀሰት ነው ብሎ ድምዳሜ ማስቀመጥን ይመለከታል፡፡
ለምሳሌ- InVID፣ Reverse Image Search ወይም TinEye የተሰኙትን የማጣሪያ መገልገያዎች ብንጠቀምና ለማረጋገጥ የፈለግነው ፎቶ ወይም ተንቀሳቃሽ መስል ትክክለኛ ምንጭ (የተቀረፀበት ጊዜና ቦታ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የተለጠፈ ከሆነም መቼት? የሚለውን) ለመመለስ ይረዱናል፡፡
አንድ ምሳሌ ወስደን እንመልከት- ከ420 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ ነሐሴ 8 ቀን 2014 “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ሞያሌን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ” በመግለፅ መረጃ አጋርቷል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም የመረጃውን እውነትነት ለማጣራት ምስሉ ላይ InVID ወይም Reverse Image Search (TinEye) ፍተሻ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ወታደሮቹ የለበሱትን ዩኒፎርም በአትኩሮት ከተመለከትነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረው ዩኒፎርም እንደሆነ ስለሚጠቁም ወደማጣራቱ ሂደት ይወስደናል፡፡
መሰል ጥርጣሬ ሲያድርብን በቀላሉ ምስሉን ወደ ስልክ ወይም ኮምፒውተራችን በማውረድ ካስቀመጥን በኋላ InVID ወይም Reverse Image Search (TinEye) የማረጋገጫ መገልገያዎችን በስልካችን ወይም ኮምፒውተራችን መክፈትና ምስሉን በሚያመጣልን የመጫኛ አማራጭ ላይ መጫንና ፈልግ የሚለውን ቁልፍ (upload and search) በቅደም ተከተል መጫን ይገባናል፡፡ በዚህም ምስሉ ከዚህ ቀደም የተጋራ ከሆነ ወይም በኤዲቲንግ አዲስ እንዲመስል ተደርጎ የተዳቀለ ከሆነ የማረጋጋጫ መገልገያዎቹ የስልክ ወይም ኮምፒውተር ስክሪናችን ላይ የፍለጋ ውጤታቸውን ያመጡልናል፡፡
በዚህ መሰረት ከላይ የጠቀስነው ገጽ የተጠቀመው ፎቶ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተለጠፈ ሲሆን ለአብነትም ኅዳር 7 ቀን 2013 “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም አቢ አዲ እንደርታ እና ማይጨዉን ነፃ አውጥቷል” በሚል ተለጥፎ ይገኛል፡፡ በዚህም ከሰሞኑ ሸኔ ሞያሌን ተቆጣጠረ በሚል የተሰራጨው የምስል መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
ምንጮቻችን፡
- Cherilyn Ireton and Julie Posetti. UNESCO 2018. Journalism, ‘Fake News’ & Disinformation. Handbook for Journalism Education and Training
- Dave Chaffey 01 Jun, 2022. Global social media statistics research summary 2022 (https://www.smartinsights.com/social-media-marketing/social-media-strategy/new-global-social-media-research/)
- ስታቲስታ ዶት ኮም የበይነ መረብ አውታር https://www.statista.com/statistics/718019/social-media-news-source/
- How to identify fake news https://www.kaspersky.com/resource-center/preemptive-safety/how-to-identify-fake-news
- INVESTINTECH.COM https://www.investintech.com/resources/blog/archives/9120-fact-check-tools-tips.html
Comments